(በነፈሰበት መዝመም በጣል ቀላሉ ተግባር ነው። ትክክለኛ ነው በሚሉት መንገድ ነፋሱን ለመጋፈጥ መነሣት ካባድ ነው። ለሀገር ጉዳይ ከባዱን ለመጋፈጥ ወደኋላ አልልም።) አንዱ ዓለም ተፈራ - ታህሣሥ ፲ ፬ ቀን ፳ ፻ ፭ ዓመተ ምህረት
አጨብጭቡ የሚለው አታሞ ከላይ እስከታች ይደለቃል። ፈንጥዙ ተብለናል። ደግፉ የሚለው አዋጅ ከየማዕዘኑ ይለፈፋል። እነ ማዴቦ ከኢሳያስ ጋር ሆነው ነፃ ሊወጡን ነውና፤ ኪሳችሁን እየዳሰሳችሁ ለኛ ገብሩ የሚለው ዜማ አየሩን ሞልቶታል። በእውነት፤ ጠመንጃ ዠልጦ ለመፎከር፤ መሠረቱ ምንድን ነው። ይኼ ለኔ፣ ላንቺ፣ ላንተ፣ ለሁላችን ምን ማለት ነው። ከየትኛውም ወገን ለሚመጣ፤ ረጋ ላለ ውይይት ዝግጁ ነኝ። በጭፍን እኛ ስላልነው ትክክል ነው ለሚል ድንፋታ፤ ጀሮዬን አልሠጥም። ወያኔን በግንቦት ሰባት ለመተካት ነው? ወይንስ ግንቦት ሰባት “ከወያኔ የተለዬሁ ነኝ” ብሎናልና አምነን እንከተለው ነው? ቀልዱ ቆሞ መቼ ነው ሀገራዊ ውይይት የምናደርገው? ግንቦት ሰባት ማንና የማን ነው? "አንተ ካልተነሳህ፤ ሌሎቹ ሲነሱ እንቅፋት መሆን የለብህም" የሚሉ አሉ። ይቺ ሀገር እኮ የኔም ሀገር ናት። ማንም ሲጨፍርባት ዝም ብለህ እይ የሚለኝ የለም። ከወያኔ ሌላ ያሻላል የሚለው ደግሞ ወሃ አይቋጥርም። አዎ የሚሻል ይኖራል። ለሚሻል ሳይሆን፤ ለትክክለኝ ነው መታገል የያዝኩት። ሀገራችንን ነፃ ሊያወጣ የተነሣን መመርመርና ማወቅ ግዴታችን ነው እላለሁ።
ወያኔን እናውድም የሚለው ባዶ ቃል ብቻ የትም አያስኬድም። የሃምሳ ዓመታት ትምህርት አሁንም በነፈሠበት መንጋጋት ከሆነ፤ የምለው ቢኖር፤ “ሊታይ አይደል!” ነው። እኛን የተቃወመ የወያኔ ደጋፊ ነው ለሚሉት የተለመደ “እኔ አዋቂ፣ እኔ ፈራጅ ነኝ” ባዮች፤ ቀጥሉበትና ካላችሁበት ፈቀቅ ስትሉ አያለሁ እላለሁ። የወታደር ልጅ ሆኜ በወታደር ሠፈር ውስጥ ነው ያደግሁት። በኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ሠራዊት አባል ሆኜ፣ ጠመንጃ አንግቼ፣ ደጋግሜ በመቁሰል ስድስት ዓመት ታግያለሁ። ወያኔ ከትግራይ ምድር ዘልቃ፣ ተከዜን ተሻግራ ወልቃይት ስትገባ፤ ጦርነት ገጥመን የቀኝ እጄ ቅልጥምና መጋጠሚያ ድቡልቡል አጥንቱ ተቦድሶ፤ አሁን ድረስ የተሸከምኩት ሰባራ አጥንት አለኝ። ሕዝብን ነፃ አውጥቶ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን የሚመሠርት ሠራዊት፤ ከሀገራዊ ውይይቱ የመነጨ ይሆናል። ሕዝብን ነፃ አውጥቶ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን የሚመሠርት ሠራዊት፤ በሕዝባዊና ሀገራዊ ሁሉን አቀፍ ድርጅት ይመራል። በግትርነትና በምኞት ሀገር አቀፍ ትግል አይካሄድም። ግንቦት ሰባት የግንቦት ሰባትን አጀንዳ አራማጅ እንጅ የኢትዮጵያዊያንን አጀንዳ አራማጅ አይደለም። እኔ ስለ ግንቦት ሰባት ከማናችሁም ያነሰ እንጂ የላቀ እውቀት የለኝም። ከኤርትራ ጋር ያላቸው ቁርኝት ያሳስበኛል።
ባሁን ሰዓት የወያኔ ቡድን በሚያካሂደው ወያኔያዊ ግዛታዊ አስተዳደር፤ ሀገራችን ብዙ ችግሮች ገጥመዋታል። በወያኔ እስር ቤቶች የታጎሩት ኢትዮጵያዊያን፣ የተዛባዉ አስተዳደራዊ ልማት፣ የሠራዊቱ አወቃቀርና የሥልጣን አመዳደብ፣ የብሔር ብሔሮች ጥያቄ፣ የነፃ አውጭዎች ጋጋታ፣ የውጭ መሬት ተቀራማጮች እውነታ፣ የደንበሩ መሠጠት፣ የኤርትራ ጉዳይ፣ የወያኔ ሥልጣናትና ከሕዝብ የዘረፉት ንብረት፣ ከደቡብ ኢትዮጵያ የተባረሩት አማራዎችና የተገደሉባቸው ዘመዶቻቸው፣ በዓለም የተበተነው ስደተኛ ኢትዮጵያዊና ሀገራዊ ጥማቱ፣ ወያኔ በመሸጥ ላይ ያለው የሕፃናት ዓለም አቀፋዊ ብተና፣ በመካከለኛው ምሥራቅ የሚሰቃዩት እህቶቻችን፣ ወዘተ. . . ለእነዚህ ጥያቄዎች የምንሠጣቸው መልሶች፤ ያስተባብሩናል ወይንም ያለያዩናል። ከዚህ ተነስተን ደግሞ፤ ጠንካራ ድርጅት ሊመሠረት የሚቻልበትን መንገድ በኅብረት እናበጃለን። እንዲያው በወያኔ ላይ ጦር ያነሳውን ሁሉ እንደግፍ ለሚሉ፤ የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባር አለላችሁ፣ የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጪ ግንባር አለላችሁ፣ ኢሳያስ አፈወርቂ አለላችሁ ሌሎችም ሞልተዋል። በነኚህ ወገኖች መካከል ልዩነታቸው፤ ምን ይከተል? በሚለው ላይ ነው። እኔን ከሌሎች ታጋዮች ጋር የሚያስተባብረኝ፤ ምን ይከተል የሚለው ነው። ይኼ አይደለም ለምትሉ፤ መልካሙን እመኝላችኋለሁ። አብሬያችሁ ግን ልዘፍን አትጠብቁ።
ድቅድቁን የሀገራችን የፖለቲካ ጨለማ እኔ ብቻ ነኝ ትክክለኛ፣ ለሀገሪቱ እኔ አውቃለሁ ወይንም የምላችሁን ስሙ የማዛችሁን ሥሩ የሚለው ቅኝት፤ ቢያንስ በኛ ደረጃ አልፎበታል። ተማክረን እናደርገው። ሀገራዊ ውይይት ይቅደም። ሀገርን ሰብስቦ ውይይት ይደረግ የሚል ብዥታ የለኝም። ከሞላ ጎደል ግን፤ በዬተገኘው መድረክ፤ ግልፅ መውጣት ያለባቸውን ሀገራዊ ጉዳዮች ማንሳት አለብን። መልሱ በሁላችንም ዘንድ አንድ ይሁንና እንነሳ።
ይኼን ትግል አንዳንዶች የትግሬዎችና የቀሪዎቹ ኢትዮጵያዊያን ጠብ አድርገው ያዩታል። ሌሎች ደግሞ የነፃ አውጪዎችና የሀገር ወዳዶች አድርገው ያዩታል። ቀሪዎች ደግሞ ከውጭ ሀገር ባነበቡትና ባገኙት ተመክሮዎች አጣብቀው ትርጉም ሊሠጡት ይፈልጋሉ። የተወሰነው ክፍል ደግሞ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባርና የኢትዮጵያዊያን የጨቋኝና ተጨቋኝ አድርገው ያቀርቡታል። ከሀገራችን የምጣኔ ሀብት ሥምሪትም አንፃር የሚመለከቱትና፤ የሀገራችን ሀብት በአንድ ቡድን ተጠፍርቆ መያዙና ለመመዝበሪያ መንገዱ የሆነውንም ሥልጣን ጨምድደው መያዛቸው ያስቆጣቸው አሉ። ወያኔ የሠጣቸውን ተቀብለው ሌላም ይገባናል፤ አንሦናል ባዮችም አሉ። ጥያቄው፤ የጠመንጃ አንሽዎቹ መሠረት የት ላይ ነው የወደቀው? ነው።
እጃችንን አጣጥፈን እንቀመጥ የሚል ካለ የወያኔ ወገን ነው። እኔ ይኼን እየሰበክሁ አይደለም። ለመፍትሔው፤ ሕዝብ፣ ሕዝብ ስልም፤ ሕዝቡ እንደሚነሳ፤ እምነት ስላለኝ ነው። አንዳንዶቻችን ታዲያ ሕዝቡ ለምን አይነሳም? እያልን የምንደነፋ አለን። እስኪ ረጋ ብለን ራሳችንን እንጠይቅ! ማነው ከመካከላችን በሕዝቡ መካከል ገብቶ፣ ችግራቸውን አብሮ ተካፍሎ፣
ከሕዝቡ ጋር ሆኖ መፍትሔ ምንድን ነው? የሚለውን ከሕዝቡ ተምሮ ቅመሙን ይዞልን የመጣ? ይኼ አዎ! ድካምን ይጠይቃል። ታዲያ የሕዝብ ትግል ማለት፤ ሕዝቡ ማዕከል የሆነበት ማለት አይደለም እንዴ? ወይንስ ነፃ አጭዎቹ ከውጭ እስክንመጣለት ሕዝቡ እዬጠበቀን ነው የሚለውን እኛ አቡክተን እኛው ጋግረን ያስቀመጥነውን እንጀራ እየበላን ነው?
“የጦር ቡድን ተመስርቶ አንድ ከተማ ቢይዝ፤ ወታደሩ ተገልብጦ ወደኛ ይመጣል” የሚል ዜማም እዬተቀኜ ነው። ከተኛንበት እንንቃ። ትግሉን እንደጋቢ ከላይ ላይ ደርበን እንሂድ ቢባል፤ ሲሞቅና ሲበርድ የሚለበስና የሚጣል የውጭ አካል ይሆናል። ትግሉ የሚሳካው፤ ትግሉን ሕይወት ብለው ሲይዙትና ትግሉን ሲሆኑት ነው። በግንቦት ሰባት ጠመንጃ ነፃነት የሚመጣበትን መንገድ ሳስበው፤ ተስፋዬ መነመነ። በነፃ አውጪ ድርጅት መሪዎች አዳራሽ ነው የምንንፈላሠሠው ወይንስ ነፃ እንዲወጣ “በሚታገሉለት” ሕዝብ እውነታ? የሚለው ከፊቴ ተደቀነ።
ይህ ትግል የእኔ፣ ያንተ ወይንም ያንቺ የግል ትግል አይደለም። ይህ ትግል የኢትዮጵያዊያን በአንድነት ትግል ነው። ኢትዮጵያዊያን ደግሞ ከወያኔ ጋር በሀገራቸው በትንንቅንቅ ላይ ነው ያሉት። በመሪነትና በታጋይነት ማዕከለኛውን ቦታ መያዝ ያለበት፤ ሕዝቡ ነው። ዓለም አቀፉ የፖለቲካ ሀቅና የሀገራችን የፖለቲካ እውነታ፤ የተወሰኑ የታጠቁ ታጋዮች ከገጠር ተነስተው እንደወያኔ እየበረሩ አዲስ አበባ የሚገቡበት ክፍት ክስተት የትናንት ሆኗል። በኔ ግምት፤ ትግሉ ሕዝቡ ባለበትና በከተማ ውስጥ ነው። ትክክለኛ ድርጅት ከተመሠረተ፤ ባጭር ጊዜ ውስጥ የወያኔ ቡድን ይቀበራል። ሕዝቡን በያለበት የሚያስነሣ ድርጅት አጭር ትግል ነው የሚኖረው። ሕዝቡን የሚያስነሣ ድርጅት ደግሞ ሕዝባዊ ነው። አንድ ወገንተኛ ሳይሆን አብዛኛውን ያቀፈ ነው። አብዛኛውን አቀፍ ድርጅት ደግሞ፤ ማዕከላዊ ለሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች፤ አብዛኞችን ያካተተ መልስ በግልፅ ያስቀምጣል። ሀገር ቤት ያለውን እውነታ ያላካተተ፣ ሀገር ቤት ያለውን ታጋይ ያላስቀደመና በዚያ ያልተመራ ድርጅት፤ ጉልቻን ከመቀያየር የተለዬ የሚያመጣው ፋይዳ የለም። ከኤርትራ ተነሥቶ አዲስ አበባ የመግባት እቅድ ላለው፤ ያለፈው ይበቃ እላለሁ። ለኔ፤ ኢሳያስ አፈወርቂ ማለት የኤርትራዊያን ጠላትና ብሎም የኢትዮጵያዊያን ጠላት ነው። ኤርትራዊያን ከኢሳያስ ነፃ ለመውጣት በትግል ላይ ናቸው።
አንዱ ዓለም ተፈራ