ሰበር ዜና (Breaking News)
በ04/02/2014 ማክሰኞ ዕለት አባ ግርማ ከበደ፤ ሁለት ሌሎች ካህናትና እንዲሁም ሌሎች ኢትዮጵያውያን ከሁለት የውጪ ሰዎች ጋር በመሆን ለንደን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ውስጥ ረጅም ሰዓታትን የፈጀ ስብሰባ ማካሄዳቸው ታወቀ።
በኤምባሲው ጽ/ቤት ውስጥ የተካሄደውን ስብሰባ የመሩት አንባሳደሩ ሲሆኑ በስብለባው ላይ የተገኙትም አባ ግርማ ከበደ፤ ሁለት ሌሎች ካህናት፤ አቶ ግርማ ወ/ማርያም (በቅጽል ስሙ ግርማ ቡፋው/ ውሸታሙ)፤ የእነ አባ ግርማ ጠበቃ ነኝ የሚለው አቶ ስምረትና ሌሎች ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በድምሩ 12 ኢትዮጵያውያንና ሁለት ፈረንጆች ነበሩ።
ስብሰባው የተካሄደው ከቀኑ 1pm ጀምሮ አስከ አመሻሹ ድረስ መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል።
ስብሰባው ያተኮረበትም በUK ኗሪ የሆነው ስደተኛ ኢትዮጵያዊ ጥሮና ግሮ ያቆማትንና ለከፍተኛ የዕድገት ደረጃ ያበቃትን ርዕሰ አድባራት ለንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያንን አስተዳደሯንና ንብረቷን ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያው አገዛዝና በደጋፊዎቹ ቁጥጥር ሥር ለማዋል ከበላይ አካል የመጣውን መመሪያ በመግለጽና የተጀመረውን ሥራ ለማሳካት የሚያስችሉ ነጥቦች አንስቶ በመምከር ላይ ነበር።
መላው በUK የምትኖሩ ኢትዮጵያዊ ስደተኛ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ሁሉ።
ዛሬ የኢትዮጵያው አገዛዝ በኤምባሲው አማካኝነት ጥራችሁና ግራችሁ ሃብትና ጉልበታችሁን በማስተባበር የገዛችሁትን ቤተ ክርስቲያናችሁን ለመንጠቅ አይኑን አፍጥጦ ጥርሱን አግጥጦ መጥቶባችኋል!!
ዛሬ ይህችን የስደተኛው ኢትዮጵያዊ አንጡራ ሃብት የሆነችውን ቤተ ክርስቲያን ከኢትዮጵያው አገዛዝ ጣልቃ ገብነት ለማትረፍ በቁርጠኝነት ተነስታችሁ ካልታገላችሁ፤ በቀጣዩ የኮሚኒቲ ማዕከላት፤ ከዛም አገዛዙ ድምጽ አልባ ላደረገው የኢትዮጵያ ሕዝብ ድምጽ ሆነው ለመከራከር የሚጥሩ የፓለቲካም ይሁን የሲቪክ ማህበራትና የጽዋ ማህበራት ሳይቀሩ በአገዛዙና በደጋፊዎቹ ቁጥጥር ሥር ከመዋል አይተርፉም።
ይህም ብቻ አይደለም ይህ የሰብዓዊ መብት ረገጣ ባህርን ተሻግሮ መጥቶ በነጻነት ሃገር እግር መትከል ከጀመረ በመጨረሻ የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ስደተኛ ቤት በር እየተንኳኳ የኢትዮጵያውን አገዛዝ የማትደግፍ ከሆነ አሳርህን ትበላለህ እየተባለ በነጻነት ሃገር የባርነት ኑሮ ለመኖር የሚገደዱበት ደረጃ ላይ ሊደርስ እንደሚችል አበክሮ መገንዘብ ይገባል።
በነፃነት ሃገር እየኖረ ቤተ ክርስቲያኑንም ሆነ ራሱንና ቤተ ሰቡን ከሰብዓዊ መብት ረጋጭና አንባ ገነን መንግሥት ነጻ ማውጣት ያልቻለ ህብረተሰብ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ሕዝቤን ከአገዛዙ የጭቆና ቀንበር ነጻ ለማውጣትና ሰብዓዊ መብቱን ለማስከበር እታገላለሁ እያለ ቢለፍፍ በራስ ከመቀለድ ያለፈ ቁም ነገርነት ሊኖረው አይችልም፤ ምክንያቱም ራሱን ነፃ ያላወጣ ሌላውን ነፃ ሊያወጣ ከቶ አይቻለውምና!!
ይህም በመሆኑ ዛሬ ነገ ሳትሉ ለንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያንን ለማዳን በጽናት ቆመው ከሚታገሉ ኢትዮጵያውያን ወንድምና እህቶቻችሁ ጋር በቁርጠኝነት በመሰለፍ የሕግ የበላይነት ባለበትና ነጻነትና ዲሞክራሲ በሰፈነበት ሃገር እንደተቀረው ህብረተሰብ ሁሉ በነፃነት የመኖራችሁን ዋስትና ታረጋግጡ ዘንድ በእመቤታችን ስም ጥሪ እናቀርባለን።
ርዕሰ አድባራት ለንደን ደብረ ጽዮን ቤተ ክርስቲያንን እናድን!!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!