Sunday, April 28, 2013

ግንባር፣ ትስስረ-ትውልድ እና የኢትዮጵያ ስነ-አስተዳደር የቀጠለ


ምን ይከተል?
 የመቀናጆ በሬ ሲመሽ ወደ ቤቱ ይስባል

ካለፈው መማርና ወደፊት ሊያገለግለን የሚችለውን መውረስ ይጠቅመናል። በመሠረቱ ከግንባር ምሥረታው በፊት መጤን ያለበት፤ ለምን ይመሠረታል ለሚለው መልስ መሥጠት ነው። ባሁኑ ሰዓት ምን ዓይነት መንግሥት በሀገራችን አለ? የሚለውን መመለስ አለብን። የዚህን መንግሥት ምንነት በምንገልፅበት ጊዜ፤ በትክክል ጠቅላላ ማድረግ ያለብንን ማየት እንችላለን። በደፈናው ትግል መደረግ እንዳለበት መቀበሉ ብቻ በቂ አይደለም። የምን ትግል? ለምን እስከዛሬ ድረስ ትክክለኛ ግንባር አልፈጠርንም? ያገደን ምንድን ነው? ከባህላችን ነው ወይንስ ከግለሰብ ማንነታችን? ይህ የሚመለሰው በሀገራችን ያለውን የስነ-አስተዳደር ሀቅ ስንረዳ ነው። አሁን የሚደረገው ትግል የዴሞክራሲያዊ መብቶችን ለማስከበር አይደለም። አሁን የሚደረገው ትግል፤ ከሌሎቹ እኔ የበለጠ ትክክለኛ ነኝ እያልን እርስ በርሳችን የምንወዳደርበት አይደለም። የኢትዮጵያ ሕዝብና ሀገራችን ኢትዮጵያ ያለችበት ሀቅ፤ የነፃነት ማጣት ጉዳይ ነው። መጀመሪያ ሀገራችን ነፃ ወጥታ ነው ሌላው የሚከተለው። የትስስረ-ትውልዱ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ሀገራችንን እየገዛ ያለው፤ እንደባዕድ ሆኖ፤ በኢትዮጵያዊነትና በኢትዮጵያዊያን ላይ በመዝመት ነው። እናም ከዚህ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነፃነት መፈለጉ ሀቅ ነው። ለዚህ የኛ ሚና፤ አንድ ሀገራዊ አስተባባሪ አካል መመሥረትና፤ ጥረታችንን በሙሉ በአንድነት ማቀናጀት ነው።

ይኼን ከተቀበልን፤ ትግሉና ትግሉ የሚጠይቀው ድርጅት ግልፅ ነው። ሀገርን ነፃ ለማውጣት አንድ ድርጅት ብቻ ነው መኖር ያለበት። ሀገርን ከአንድ በላይ በሆኑ ድርጅቶች ነፃ ለማውጣት መነሳት፤ ሀገሪቱን ለመከፋፈል ወይንም ቆይቶ ሌላ ጦርነት ለማንሳት ማቀድ ይሆናል። እናም ሀገርን ነፃ ለማውጣት አንድ ድርጅት ብቻ ነው መኖር ያለበት። አንድ ድርጅት ደግሞ አንድ ሠልፍ፣ አንድ ራዕይ፣ አንድ ተልዕኮ፤ አንድ ግብ ነው ያለው። ወገናችን ከአምባገነኑ ጥፍር ራሱን ለማላቀቅ በሚያደርገው ትግልና አንዷን ሀገራችን ነፃ ለማውጣት፣ እንያንዳንዳችን ኢትዮጵያዊያን፤ በሀገር ቤት የምንኖርም ሆነ ከሀገር ውጪ ያለን፤ በአንድነት የምንሠለፍለትና የምንሠለፍበት አንድ ድርጅትና አንድ ዓላማ መጨበጥ አለብን። ይኼ እስካልሆነ ድረስና ሌላውን አማራጭ ከወሰድን፤ ያለው ገዢ ቡድን እንኳ ቢወገድ፤የእሬያ ታጥቦ ጭቃነትነው ጉዟችን። ከላይ እንደተጠቀሰው ጨልሞ ማየት የማይቻልበት ጊዜ ገና ቢሆንም፤ መሽቷልና ወደ ቤታችን እናምራ።

የትስስረ-ትውልድ አምባገነን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥትን ለማስወገድ፤ እንደገና አሁንም አንድ ድርጅት ብቻ መመሥረት አለበት። የዚህ ድርጅት ዓላማ፤ የአምባገነኑን መንግሥት አስወግዶ፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩን ተረክቦ፣ ሕዝቡ በፈቃዱ የሚወክለውን መንግሥት እንዲያቋቁም ማስተናገድ ነው። ይህ አንድ ድርጅት የሚመሠረተው፤ የትስስረ-ትውልዱ አምባገነን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት መወገድ አለበት። ብለው፤ በሰላማዊ አመፅ እንታገላለን፣በትጥቅ ትግል እናስወግደዋለን፤ በሀገር ቤት እንታገላለን፣ ከሀገር ውጪ እንታገላለን፣ በሕጋዊ መንገድ እንታገላለን፣ በሕቡዕ እንታገላለን፣ በአምባገነኑ ድርጅቶች ውስጥ ሆነን እንታገላለን ከሚሉት ሁሉ የተውጣጣ መሆን አለበት። ጉዳዩ ሀገር ማዳንና የሕዝቡን ነፃነት የሚመለከት ስለሆነ፤ የግለሰቦች ሆነ የድርጅቶች ታሪክና ጥንካሬ የተለዬ ቀዳሚ ቦታ አይሠጠውም።ለማንኛውም ግለሰብ ሆነ ድርጅት መለኪያው፤ ለትግሉ በምን መንገድ አስተዋፅዖ ያደርጋል የሚለው ብቻ ነው። በተለይም የስነ-አስተዳደር ድርጅቶች፤ ሀገር ነፃ ሲሆን፤ መርኀ ግብራቸውን ለሕዝቡ በማሳወቅ ተቀባይነት ሊያገኙ ይችላሉ። ከዚያ ወዲህ ግን በብልጣ ብልጥነት ራስን ማደላደል ከያዙ፤ የሕዝብ ወገን አይደሉም። የሀገር መኖር ከሁሉም በፊት ግድ ነው።

የዚህን አንድ ድርጅት አወቃቀር በሚመለከት ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ አለበት። በመቅድሙ እንደተገለፀው፤ይኼን የተመሰቃቀለ የስነ አስተዳደር ሂደት ለማለፍ፤ ጥራት ያለው ድርጅትና ጥንቃቄ የተሞላበት ዝግጅት ማድረግ ግዴታችን ነው። ጠላታችን ዝም ብሎ አይመለከትም፤ የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ ነውና! ለዚህ ነውሲሮጡ የታጠቁት ሲሮጡ ይፈታልያሉት የቀደሙ አያቶቻችን።

እናም ከላይ የተዘረዘሩትን አጢነን፤ በአንድ ድርጅት ሥር ተሰባስበን፤ ግልፅ የትግል ግብ፣ የጠራ የትግል መስመር፣ ተግባራዊ የሚሆን እቅድ ነድፈን ወደፊት እንሂድ። ኢትዮጵያዊያን በአንድነትየኛየምንለው ድርጅት ሊኖረን ይገባል። ይህ በምኞት አይመሠረትም። መገንባት አለበት። አንዴ ለተሰባሰብንበት ድርጅት፣ ለተሰማራንበት የትግል ግብ፣ ላመንበት ዓላማና ቃል ኪዳን ለገባንበት የትግል መስመር፤ እስከመጨረሻ የሚጠበቅብንን ለመክፈል ዝግጁ መሆን አለብን። ያመንበትን ለማራመድ፣ የተጋረጠብንን ለመጋፈጥ ቅንጣት ፍራቻ አይኑረን። ዘረኛውን አምባገነን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ለማውረድና መሪዎቹን ለፍርድ ለማቅረብ፤ ሽንጣችንን መገተር፣ ወገባችንን ማጥበቅ አለብን። ወገንና ሀገር ወዳድነታችን የሚፈተነው አሁን ነው። አሁን ለተደረገው ጥሪ መልስ መስጠት አለብን። በተቃዋሚ ጎራ የተሠለፍነው በሙሉ፤ ድል የሚጠይቀውን ተግባር ለመፈፀም፤ መነሳት አለብን። እኛ ካልሆን ማን?

ነፃነታችን የሚመጣው፤ ዋጋውን ከፍለንለት፣ መስዋዕት ተደርጎለት እንጂ አባብለንና ለምነን፣ ጉቦ ከፍለን ወይንም ቁጭ ብለን ጊዜ በመጠበቅ አይደለም። ጠላታችንን በደንብ መለየት፣ ወዳጆቻችንን በቅርብ መያዝና ግባችንን ከፊታችን ገትረን መጓዝ ምንጊዜም ጉዳያችን በማድረግ ነው። ወዳጆቻችንን በሚመለከት፤ የምንመሳሰለው ምን ላይ ነው? የምንለያየው በምንና በምን ላይ ነው? ልንስማማባቸው የምንችለው በምን ላይ ነው? ይህ ግልፅ መሆን አለበት? መገንጠልን ዋና ዓላማቸው አድርገው ከተነሱ ነፃ አውጪ ድርጅቶች ጋር ውሎ ማደር አይኖርብንም። ከትስስረ-ትውልዱ አምባገነን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር በምን ይለያሉ? በዚህ አምባገነን ጉያ ተቀምጠው፤ በሱ ትዕዛዝና ፈቃድ መሠረት ለሚንቀሳቀሱተቃዋሚድርጅቶች፤ ከበሬታ ሊኖረን አይገባም። የውጭ መንግሥታትም፤ ምን ጊዜም ከራሳቸው ጥቅም ሌላ፤ ለኛ ብለው ወይንም ዴሞክራሲን በዓለም ለማንገሥ በማሰብ፤ የሚሰነዝሩት ጣት ወይንም የሚነቅሱት ቅንድብ የላቸውም።

ሌላው ትልቁ በታጋይች ሠፈር ያለው ችግር፤ ከላይ እንደተጠቀሰው መሪዎች፣ የመሪዎች የሥራ ድርሻና የኃላፊነት ልኬታ ገድብ አለመሠጠቱ ነው። የመሪዎች ሚና የሚናቅ አይደለም። መሪ ግን ድርጅት አይደለም። መሪዎቻችንን በደንብ ማወቅ አለብን። መቆጣጠሪያ መንገድም መኖር አለበት፤ በሕግ የሠፈረና የሚተገበር! በሕገ ደንቡ ውስጥ የሠፈሩ ማንኛውም አንቀፆች፤ ተፈፃሚነታቸው፣ የጊዜ ማኅተማቸውና ተጠያቂ አካላቸው፤ በሠፈረው መሠረት መፈፀም አለባቸው። ቀያሪ አካሉ በግልፅ መሥፈር አለበት። ንጉሥች ሳይሆን ለተወሰን ወቅት ኃላፊነትን የሚቀበሉ ሰዎች ናቸው በየቦታው መመደብ ያለባቸው።

የኛ ትስስረ-ትውልድ ተጎድቷል ወይንም ተጠቃሚ አልሆነም በማለት የየራሳቸውን የትስስረ-ትውልድ የስነ-አስተዳደር ድርጅት መመሥረት፤ የትስስረ-ትውልዱን አምባገነን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ዓላማ ማራመድ ነው። በርግጥ ይህ አምባገነን የአማራ፣ የኦሮሞ፣ የደቡብ፣ የሶማሌ፣ የአፋር፣ የቤንሻንጉል፣ የአኙዋክ፣  የትስስረ-ትውልድ የስነ-አስተዳደር ድርጅቶች አቋቁሟል። የነዚህ መቋቋም አንድም ግዴታ፤ ሌላም ትክክለኛ አያደርጋቸውም። ትክክለኛ ላለመሆናቸው፤ ራሳቸው ወከልናቸው ላሏቸው ተጠሪ አለመሆናቸው በቂ ማስረጃ ነው። በትንሽ አካባቢ የሚፈፀመው ተግባር፤ በትልቁ ሀገር አቀፍ ደረጃ የሚፈፀም መሆኑን ማወቅ አለብን። በተናጠል የሚደረግ ጉዳይ የለም።

መዝጊያ፤

ባሁኑ ሰዓት እያንዳንዷን በግል የምትነካንን ጉዳይ ብቻ አንጠልጥለን በየቦታችን ከሮጥን፤ በመካከላችን ያለውን መቀራረቢያ ክሮች እንዲበጠሱ እያከረርን፣ በተናጠል እያደርን እየቀጨጭንና ሕዝቡንም በተስፋ አስቆራጭ መንገድ እየመራን፤ የትግሬዎችን ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት እድሜ ማራዘም ብቻ ነው ሂደታችን። ከዚህ መውጣት አለብን። አዎ የአማራው ጉዳይ ከባድና አደገኛ ነው። ይኼን ለአማሮች ብቻ አንተወውም። የእስልምና ተከታዮች ጉዳይ ከባድ ነው። ይኼን ለእስላሞች ብቻ አንተወውም። የቤንሻንጉል፣ የደቡብና የኦሮሚያ ለም መሬቶች ለውጭ ሀገርና የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር አባላት በርካሽ መሠጠቱ ለነኚህ አካባቢዎች ነዋሪዎች ብቻ አንተወውም። የድንበሩን ለሱዳን መሠጠት ጉዳይ ለደንበሩ ነዋሪዎች ብቻ አንተወውም። በየቦታው የኢትዮጵያዊያ ነፃ ጋዜጠኞችን መጎሳቆል ለቤተሰቦቻቸው ብቻ አንተወውም። ኢትዮጵያዊያን ነጋዴዎች በሆነ ባልሆነው መበዝበዛቸውን ለነሱ ብቻ አንተወውም። በገፍ የኦሮሞ ልጆችመታሠራቸውን ለኦሮሞዎች ብቻ አንተወውም። ኢትዮጵያዊያን እንዲሰደዱ ለመገዳድቸው፤ ለተሰዳዶች ብቻ አንተወውም። ሀገራቸው ተመልሰው እንዳይገቡ በውጭ የሚኖሩትን ኢትዮጵያዊያ ጉዳይ ለተሰደዱት ብቻ አንተወውም። ይህ ሁሉ የሁላችን ኢትዮጵያዊያን ጉዳይ ነው። ይህን በአንድነት የኔ ብለን መነሳት አለብን። የዚህ ሁሉ ተጠያቂው የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ነው። ይኼ ቡድን መወገድ አለበት። ይኼ ቡድን ከነስነ-አስተዳደር ፍልስፍናውና የአስተዳደር መመሪያው መወገድ አለበት። እናም ይህን ማስወገድ የሁላችን የአንድነት ግዴታ ነው። ኢትዮጵያዊ ሆነን መቆጠር አለብን።ኢትዮጵያዊ ሆነን ብቻ ነው ይኼን ልናደርግ የምንችለው። ዛሬ በውጭ ሀገር መረቡን ዘርግቶ፤ በያለንበት የመከፋፈል እኩይ ተግባሩን ለማከናወን ክንዱን እያረዘመ ነው። እስከመቼ እንጠብቃለን?

የመንግሥት ለውጥ ብቻ ሳይሆን የሥርዓት ለውጥ መደረግ እንዳለበት ሁላችን ተረድተናል። በሀገር ውስጥ ያሉት ባገኙት ቀዳዳና ባላቸው አቅም እየተዋደቁ ነው። በውጭ ያለነው የታጋዩ አካላት፤ በመጀመሪያ ሀገራዊ ውይይቱን አድርገን፤ መሰባሰብ አለብን። ምንም እንኳ የትስስረ-ትውልዱ አምባገኑ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ኃይለኛና አይበገሬ መስሎ ለጊዜው ቢታይም፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ አቸናፊ ሆኖ መውጣቱን መጠራጠር የለብንም። ይኼን ገሀድ ለማድረግ ደግሞ፤ ይኼን ቡድን በደንብ ማጥናት፣ የሚጠብቀን ምን እንደሆነ መረዳትና ጥንካሬና ድክመታችን መመርመር አለብን።

ሀገርን ነፃ ለማውጣት አንድ ድርጅት ብቻ ነው መኖር ያለበት። አንድ ድርጅት ደግሞ አንድ ሠልፍ፣ አንድ ራዕይ፣ አንድ ተልዕኮ፤ አንድ ግብ ነው ያለው። ወገናችንን ከአምባገነኑ ጥፍር ለማላቀቅና አንዷን ሀገራችን ነፃ ለማውጣት፣ እንያንዳንዳችን ኢትዮጵያዊያን፤ በሀገር ቤት የምንኖርም ሆነ ከሀገር ውጪ ያለን፤ በአንድነት የምንሠለፍለትና የምንሠለፍበት አንድ ድርጅትና አንድ ዓላማ መጨበጥ አለብን። ለምንሰባሰብበት ድርጅት፣ ለምንዋደቅለት የትግል ግብ፣ ለምናምንበት ዓላማና ቃል ኪዳን ለምንገባለት የትግል መስመር፤ እስከመጨረሻው የሚጠበቅብንን ለመክፈል ዝግጁ መሆን አለብን። ያመንበትን ለማራመድ፣ ለተጋረጠብን ለመጋፈጥ ቅንጣት ፍራቻ አይኑረን። የዚህ ድርጅት ዓላማ፤ የአምባገነኑን መንግሥት አስወግዶ፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩን ተረክቦ፣ ሕዝቡ በፈቃዱ የሚወክለውን መንግሥት እንዲያቋቁም ማስተናገድ ነው። በሂደቱ የኢትዮጵያን የሕዝብ አንድነትና ሉዓላዊነት፣ የኢትዮጵያን ሀገራዊ ዳር ደንበርና ሀገራዊ ስፋት፣ የግለሰብ ኢትዮጵያዊያንን ዴሞክራሲያዊ መብቶችና በኢትዮጵያ የሕግ የበላይነትን በሕግ ማስፈር፣ ማስከበርና ለዘላቂነታቸው መሠረት መጣል ይሆናል። እኒህ ናቸው የመታገያ ዕሴቶቻችን። እኒህ ናቸው የምናቋቁመው ድርጅት ተግባራት።