Wednesday, September 4, 2013

የሙስናው ጉዳይ

በተንጣለለ ቪላ ውስጥ ከበድ ያሉ እንግዶች "ጸዳ" ባሉ ምግብና መጠጦች እየተስተናገዱ ነው። ታዋቂ ግለሰቦች፤ ባለስልጣናት እና አርቲስቶች የቀረበላቸውን ብፌ በልማታዊ ወጋቸው እያወራረዱ ሳሉ አንድ እንግዳ ነገር በመሃላቸው ተከሰተ። ሞቅ ባለው የአይቴ ነጋ ገብረእግዚአብሄር ድግስ ላይ ያልተጋበዙ ሁለት ሰዎች ዘው ብለው ከግብዣው ክፍል ገቡ። የፌዴራል ፖሊስ አባላት ነበሩ።

በዚህ ያልተለመደ ክስተት የአቶ ነጋ እንግዶች አልተደናገጡም ነበር። ይልቁንም የፌዴራል ፖሊሶቹ ለተጨማሪ ጥበቃ የመጡ ነበር የመሰላቸው። አንድ ብርጌድ ያህል ጦር አስከትለው የመጡት ፖሊሶች ግን አቶ ነጋ ገብረእግዚአብሄርን አስጠሯቸው። አቶ ነጋም ለጥሪው እንደወትሮው በመወጣጠርና ፍጹም ትእቢት በተሞላበት አነጋገር ምላሽ ሰጡ። በፖሊስ አባላቱ እና በአቶ ነጋ መካከል የሃይለ-ቃል ልውውጥ ተጀመረ። እሰጥ እገባው አንድ፣ ሁለት እያለ ሄደና በመጨረሻ ተካረረ። በዚህ ሰዓት አቶ ነጋ ስልክ መደዋወል ያዙ። ከፍተኛ የሚባሉ ባለስልጣናትና ምኒስትሮች ደወሉ። ከዚያም በመቀጠል፣ ጀነራሎች ደወሉ... የጦር መኮንኖች፣ የፓርቲ ባለስልጣናት...ሁሉም ተደወለ። የባለስልጣናቱ ምላሽ ግን ጥሩ እንዳልነበር ከአቶ ነጋ ፊት ላይ ይነበብ ነበር። ወዳጆቻቸው ሁሉ እንደ ቱኒዚያው ቤን አሊ በአንድ ጊዜ ከዷቸው።

"በል - - ውጣ!" አለ አንደኛው የፖሊስ አባል፣ የስልኩን ሽርጉድ በጥሞና ከተከታተለ በኋላ።

"ምን ማለትህ ነው? እኔኮ ነጋ ነኝ። ነጋ ታሪኩ!" አሉ። አነጋገራቸው የጀምስ ቦንድን ይመስል ነበር። በዚህ ጊዜ ታዲያ እጃቸውም አላረፈም። ከጎን ያሸጎጡትን መሳርያ ለማውጣትም ዳዳቸው።

በቅጽበት ግን ፌዴራል ፖሊሱ ቀደማቸው። በድንገት "!" የሚል ድምጽ አዳራሹን አናጋው። የፖሊሱ አይበሉባ የግራ መንጋጭላቸው ላይ ሲያርፍባቸው ጊዜ፤ አይቴ ነጋ ነገር አለሙ ተደበላለቀባቸውና እጅ መስጠትን መረጡ። ግብር ሊያበሉ በጠሯቸው የክብር እንግዶቻቸው ፊት፣ ከዚህ በላይ መዋረድ አልፈቀዱም። ሁለት እጃቸውንም ወደ ፖሊሱ በመዘርጋት ለብረት ማሰርያው
ራሳቸውን አመቻቹ። እጃቸው የኋሊት ከተጠፈረ በኋላም አቶ ነጋ እንዲህ አሉ። "በቃ! ህወሃት አበቃለት!"

"ባለሃብቱ" በዚህ ሁኔታ በፖሊስ መኪና ተጭነው ወደ እስር ቤት ሲሄዱ፣ ተጋባዥ እንግዶቹም እግሬ-አውጭኝ እያሉ ከስፍራው አፈተለኩ። ይህ ታሪክ ድራማ ሊመስል ይችላል። ግን በእውን የተፈጸመ ሃቅ ነው። ታሪኩን ያጫወተኝ ሰውም እዚያ ግብዣ ላይ ግብር ሊበላ ተገኝቶ ነበር። እንደ አግራሞቱም "ይህ መቼም የፈጣሪ ስራ ነው።" ከማለት ውጪ ስለ ጉዳዩ እንድምታ የሰጠው ማብራሪያ የለም።

ነጋ ገብረእግዚአብሄር የነፃ ትሬዲግ ኃላፊነቱ የተወሰነ (ሰዎች ያልተወሰነ ይሉታል) የግል ማህበር ባለቤት ነበሩ። ድርጅታቸውም እንደስሙ ከሁሉም ነገር ነጻ ነበር። ከግብር ነጻ፤ ከቁጥጥጥር ነጻ፤ ከፍተሻም ነጻ። በመቶዎች የሚቆጠሩ የጭነት መኪናዎች እቃ ጭነው በየኬላው ሳይፈተሹ እንዲያልፉ የተሰጠ ልዩ መብት ሁሉ እንደነበራቸው ይነገራል። ዛሬ ፈጣሪ ሲፈርድባቸው በኢፍትሃዊ መንገድ ቢልየነር ያደረጋቸው ስርዓት፤ ያው ስርዓት ሰለባ አደረጋቸው... ነጋ ገብረእግዚአብሄር ለአቶ መለስ ዜናዊ እና ለባለቤታቸው ለወ/ አዜብ መስፍን ቅርብ - በጣም ቅርብ ነበሩ። ለጉምቱ ባለስልጣናት ይሰጡት የነበረው እጅ መንሻ ከዚህ አይነት ውርደት እና እስራት ሊያድናቸው አልቻለም። በትግራይ ውስጥ 40 ሚሊየን ብር በላይ አውጥተው በስማቸው ያሰሩት የቴክኒክ ኮሌጅም እንደ ውለታ አልተቆጠረላቸውም።...

ይህችን አጭር መጣጥፍ ለመጫር እንደተቀመጥኩ አንድ ዜና በኢሜይል ደረሰኝ። የዜናው ርእስ "ጀነራል ባጫ ደበሌ የአዋሽ ባንክ ሰራተኞችን ከሥራ እንዲባረሩ አደረጉ!" ይላል። ባጫ ደበሌ የባንክ ሰራተኞቹን ያባረሩዋቸው ‘’እኔ ጀነራል ባጫ ደበሌን እንዴት አታውቁኝም?’’ በሚል በሰራተኞቹ አለመታወቃቸው አበሳጭቷቸው ነበር። ወደ ፌስ ቡክ ጎራ ስልም አንዳንዶች በዜናው ላይ ሲወያዩ አስተዋልኩ። ይህ እኮ አዲስ ክስተት አይደለም። ለብዙ ጊዜ የሚደጋገም እና የተለመድ ነገር ዜና ሊሆን አይችልም። ውሻ ሰውን ሲነክስ ዜና አይሆንም። በተቃራኒው ግን ሰው ውሻን ከነከሰ ዜና ይሆናል። እንዲህ አይነቱ ክስተት ስር የሰደደ የስርዓቱ ባህርይ ነው። ባጫ ደበሌ እነዚያን ሰዎች ማስገደል የሚያስችልም ስልጣን እና መብት ያላቸው የአዜብ ሰው መሆናቸውን አንዘንጋ። ጀነራል ባጫ በተልእኮ ትምህርት ከአንድም ሁለተኛ ዲግሪ እንዲገዛላቸው ካደረጉ በኋላ፣ ለምርቃታቸው ስነ-ስርዓት፣ ሰንጋዎች ጥለው፣ የሙዚቃ ባንድም አስመጥተው፣ መንገድ ሁሉ እንዲዘጋ አድርገው ሲያበቁ፤ በተለመደው ብሬክ ዳንሳቸው መንደሩን የቀወጡ ሰው ናቸው። በብርሃን ፍጥነት ከኪነት ጓድነት ወደ ጀነራል የተሸጋገሩት ባጫ ደበሌ በመደበኛ የስራ ጊዜያቸው ጫት ይነግዳሉ። በትርፍ ጊዜያቸው ደግሞ በዜጋው ላይ እንዲሁ እንደዋዛ እየቀለዱ እስካሁን አሉ። የነገውን አንድዬ ብቻ ነው የሚያውቀው። የፍትህ ሳይሆን የግለሰቦች የበላይነት የሰፈነበት ሃገር ስልጣንን ያላግባብ መጠቀም ሙስና ሊደንቀን አይገባም። የፍትሃዊ ስርዓት መጥፋት ነው ሙስና።

ፕሮፌሰር አል ማርያም ባለፈው መጣጥፉ ስለሙስና ሲጽፍ ከሙስና ሁሉ በላይ ሙስና የሚሆነው የፍትህ መጓደል እንደሆነ አስነብቦናል። የፍትህ መጥፋት ስብእናን፣ ነጻነትንና ንብረት ማጣትን ያስከትላልና። In my view, denial of due process (fair trial) is the highest form of corruption imaginable in the “justice sector” because it results in the arbitrary deprivation of a person’s life, liberty and property. (Al Mariam)

ከሰሞኑ ደግሞ ስልጣንን ያለአግባብ በመጠቀም ምንጩ ያልታወቀ ሃብት አፍርተሃል በመባል ተወንጅሎ ወህኒ የወረደው የወልደስላሴ ወልደሚካኤልም ዜና በስፋት እየተሰራጨ ነው። ወልደስላሴ ሌላኛው የአዜብ መስፍን የቅርብ ሰው ነበር። በዚህ ጉዳይ ላይ ዳዊት ከበደ በስፋት ትንታኔ ስለሰጠበት እዚህ ላይ አልደግመውም። ወልደስላሴ ግን ከህወሃት የጫካ ትግል ጀምሮ ቀልፍ ቦታዎች ላይ ተመድቦ የሰራና - የመለስ ቀኝ እጅ የነበረ ሰው ነው። ታማኝ አገልጋይም ስለነበረ በህወሃት ውስጥ ወሳኝ ቦታ ነበረው።

ከወልደስላሴ እስር በኋላ ብዙዎች በህወሃት ውስጥ ውጥረት እንዳለ መናገር ጀምረዋል። ውስጥ ለውስ እየተንከባለለ ያለው ውጥረትማ ከከረረ ትንሽ ዘግየት ያለ ይመስላል። በውጥረቱ የተነሳም በባለስልጣናቱ መካከል እርስ በርስ መተማመን ከጠፋ ቆየ። አንድ ውስጥ አዋቂ ስለዚህ ሁኔታ ሲያጫውተኝ አባላቱ በምሽት ሲወጡ እንደ ጅብ ጎን ለጎን ነው የሚሄዱት። ጅብ ስለሚፈራ ብቻውን አይሄድም። ሁሌም ተጠራርቶ በቡድን ይሄዳል። ከባልንጀራው ጋር አብሮ ሲሄድ ደግሞ ጎን ለጎን መሆን አለበት። ፊትና ኋላ ከሆኑ እርስበርስ ይበላላሉ።

በአሁኑ የህወሃት አሰላለፍ ግን አንደኛው ወገን ከኋሊት መጥቶ የቀደመ ይመስላል። ከፊት ያለው የኋላውን መብላት ጀምሯል። ተገላቢጦሽ የሆነው ይህ አስገራሚ ክስተት ነው ውጥረቱን ይበልጥ ያከረረው። የአዜብን ቡድን የማጥፋቱ ሂደት ላይ ግን ከፍተኛ ጥናት ሳይደረግ አልቀረም። የፖለቲካ ሃይል አሰላለፉ ላይ ሚዛን የደፋው አንደኛው ቡድን ከደሙ ንጹ ባይሆንም የሙስናውን ወንጀል ለብቀላ መጠቀምያ ማድረጉ የአደባባይ ምስጢር ነው።

አንዳንድ የዋሆች ታዲያ ይህ የጸረ-ሙስና ዘመቻ አቶ መለስን ለማሳጣት እየተደረገ ያለ ድራማ እንደሆነ ይናገራሉ። አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝንም የሚያመሰግኑም አልጠፉም። አቶ ሃይለማርያም ብዙውን ክስተት እንደ ተራው ሰው በዜና እንደሚሰሙ የሚያውቁት በቅርብ ያሉት ሰዎች ብቻ ናቸው። ለነገሩ እሳቸውም አስቀድመው "የእኔ ስራ ከፊትም ሆነ ከኋላ የሚሰጠኝን ትእዛዝ እየተቀበሉ ማስፈጸም ብቻ ነው።" ብለዋል። ከፊትና ከኋላ ብቻ ሳይሆን ከላይና ከታችም መመርያ እየተቀበሉ ያስፈጽማሉ። በሙስናው ስም የሚካሄደው ጨዋታ ከሳቸው ራዳር ውጭ ያለ መሆኑን ለመረዳት የፖለቲካ ጥበብን አይጠይቅም።

አቦይ ስብሃት በአንድ ቃለ-መጠይቅ ላይ ስለዚህ ጨዋታ ሲናገሩ 10 ሚሊዮኑ ዘራፊ ቁጭ ብሎ 10 ሺው መታሰር የለበትም ብለው ነበር። አቦይ ስብሃት በሙስና ወንጀል ዋናው ተጠያቂ እንደሆኑ ቢታወቅም እውነት ብለዋል። ከሌላው ጋር ሲነጻጸር ከአቶ ገብረዋህድ ወልደጊዮርጊስ ቤት ተገኘች ተብላ በኢቲቪ ጭምር ስትታይ የነበረችው 26 ኢሮ ኢምንት ናት። Global Financial Integrity (GFI) በመባል የሚታወቀው አለማቀፍ የገንዘብ ግልጸኝነት ተቋም 2001 እስከ 2010 ብቻ ከኢትዮጵያ ተዘርፎ ወደውጭ የወጣው ገንዘብ 16.5 (አስራ ስድስት ነጥብ አምስት) ቢሊየን ዶላር ነው ሲል መረጃውን ከነማስረጃው ይፋ አድርጓል። ይህ ድርጊት ደግሞ በሙስና ከዘቀጡ ሃገራት ኢትዮጵያን በመጀመሪያው ደረጃ ላይ አስቀምጧታል። ልብ በሉ! 16.5 ቢሊየን ዶላር ከአራት በላይ "ህዳሴ" ግድቦችን ያሰራል። ከሁለተኛው አለም ጦርነት በኋላ መላው አውሮፓን ከውድቀት ያስነሳው የማርሻል ፕላን በጀት 20 ቢሊየን ዶላር ነበር። ከኢትዮጵያ በስምንት አመታት ጊዜ ውስጥ ብቻ የወጣው 16 ቢሊየን ዶላር ደግሞ አፍሪካ ካለችበት ውድቀት ሊያስነሳት የሚችል ገንዘብ እንደሆነ የኢኮኖሚ ጠበብት ይናገራሉ።

.. ኢንተርናሽናል የተባለው የማድሪድ ጋዜጣ / አዜብ መስፍን በአንድ ቀን ግብይት ብቻ ለልብሷ 1.5 ሚሊዮን ዶላር እንዳወጣች ዘግቧል። አዜብ መስፍን ባለፈው የህወሃት ስብሰባ ላይ ተገኝታ ስትናገር ግን የአቶ መለስ የወር ደሞዝ 250 ዶላር እንደሆነ ነበር የተናገረችው። አዜብ 1.5 ሚሊዮን ዶላር ልብስ በአንዲት ምሽት ስትሸምት መንግስት ድጎማ አድርጎላት ከሆነ ይኸው በይፋ ይነገር። 250 ዶላር የወር ገቢ በሚሊዮን ዶላር ወጪ ማድረግ የሚቻልበት ሚስጥር የአባባ ታምራት ገለቴ ምትሃት ካልሆነ ታዲያ ምን ሊሆን ይችላል? ይህንን መራራ ሃቅ የጸረ-ሙስናው ኮሚሽንን የሚነዳው ቡድን እንዴት ችላ ሊለው ቻለ? በዚህ ጉዳይ ላይ በርካታ ታዛቢዎች የሚሰጡት አስተያየት የሚያስኬድ ይመስላል። ቡድኑ በቅድሚያ ወደ እነ አዜብ ሰፈር የሚወስደው መንገድ ላይ ያሉ ከእንቅፋቶችን ሁሉ ማጥራት አለበት።

በዛሬይቱ ኢትዮጵያ እንደ ቀልድ የሚነገሩ አንዳንድ እውነታዎች ለማመን የሚከብዱ ናቸው። አንዱ 'ልማታዊ ባለሃብት' በሪል ስቴት ስም የተመራው ቦታ ሲሰላ ከጅቡቲ የቆዳ ስፋት በልጦ ተገኘ። ይህ ሰው ትንሽ ቆይቶ ህገ-መንግስታዊ መብቱን በመጠቀም የመገንጠል ጥያቄም ሊያነሳ ይችላል እያሉ ያወሩ ነበር - በዚያ የቀኑት ባልንጀራዎቹ። በመጨረሻ ግን "ባለሃብቱ" በሙስና ታሰረና ይዞት የነበረው መሬት ለነ ቱሬ ዘመዶች በሄክታር ሁለት ብር ሂሳብ ተቸበቸበ። ለነገሩ 3.5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ከዜጋው እየተቀማ ለውጭ ዜጎች በተቸበቸባት ሃገር ይህ ምንም ላይደንቀን ይችላል።

የሙስና ሰለባ የሆነው የሌላኛው ባለስልጣን ቤት ሲበረበር ደግሞ ብሄራዊ ባንክ ይመስል ነበር። እዚያ ቤት ውስጥም የአለም መገበያያ ገንዘብ ተገኘ። ዶላር፣ ኢሮ፣ ድራም፣ የን፣ ፓውንድ፤ ክሮን፤ ፍራንክ፣ ዲናር፣ ረንቢኒ ... እንዲያውም የኤርትራ ናቅፋ በገፍ ነበር። ከአቶ ገብረዋህድ ወልደጊዮርጊስ 26 ዶላር ተጋንና በቲቪ ስትቀርብ የዚህኛው ንግድ ፈቃድ የሌለው ባንክ በግል እጅ ሲገኝ ሜዲያም ዝም ማለትን መረጠ። በዚህ ጊዜ ነበር የአሳሪው ቡደን ሃላፊ የኮሎኔል መንግስቱን ንግግር የተጠቀመው። "ደፍረውናል፣ ንቀውናል።.. ብታምኑም ባታምኑም በቁም ሞተናል።"

አነጋገሩ ለምን ሃገር ተዘረፈ ሳይሆን እኛ ታግለን ለዚህ የደረስን የቁርጥ ቀን ታጋዮች ቁጭ ብለን እንዴት ከኋላ የመጣው ሊበልጠን ቻለ ለማለት ነበር። የሙስናው ዘመቻ ድራማ ቁልፍ እዚህ ላይ ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ ወደፊት በሰፊው እሄድበታለሁ። ለአሁን ግን በአቶ ኤርምያስ አመልጋ የሚደነቅ ታሪክ ጽሁፌን ልቋጭ።

በዚያ ሰሞን የአክሰስ ሪል ስቴት ሥራ አስኪያጅና የቦርድ ሰብሳቢ የነበሩት አቶ ኤርምያስ ጠቅል አመልጋ፣ በተለይ በውጪ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለመኖሪያ ቤት ግንባታ 1.4 ቢሊዮን ብር በላይ ከሰበሰቡ በኋላ፣ ከሃገር መጥፋታቸው ተዘግቦ ነበር። ታዲያ አቶ ኤርምያስን የሚረግሙ ጌጃ ዲያስፖራዎች እንዳሉ ሁሉ እሳቸውን የሚያደንቁም አልጠፉም። ስለአቶ ኤርምያስ በቀልድ እየተመሰለ ብዙ ነገር ይወራል። የተከበሩ ሎሬት አፈወርቅ ተክሌን እና አቶ ኤርምያስን የሚያመሳስላቸው ነገር ቢኖር ሁለቱም የተዋጣላቸው ሰአሊያን መሆናቸው ነው ተብሏል። ለላሜ ቦራው ዲያስፖራ እንዲሰሩ ገንዘብ የተከፈለባቸው ቤቶች ሁሉ ባማሩ ስዕሎች በወረቀት ላይ ዱቅ ብለዋል። በንዴት ገንዘቡን ሊያስመልስ የሚሄደው ሁሉ በስእሎቹ እና በአቶ ኤርምያስ ምትሃታዊ ንግግር እየተማረከ እንዲያውም ለሁለተኛና ሶስተኛ ቤት የከፈለው ዲያስፖራ ቁጥር ትንሽ አይደለም። አቶ ኤርምያስ በአንድ በኩል በሙስና ክስ እየተፈለጉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ከሃገር በቦሌ አድርገው እንዲወጡ የተደረጉ "ጀግና" ባለሃብት ናቸው።

ለፖለቲካው እንግዳ ለሆኑ ሰዎች፤ እነዚህ ሁሉ ፈጠራ ሊመስሉ ይችላሉ። ግን የኢትዮጵያ ህዝብ የእለት ተለት ገጠመኞች ውስጥ አንድ እጅ እንኳን የማይሞሉ እውነታዎች ናቸው።

ክንፉ አሰፋ


Tuesday, September 3, 2013

የአብዮቱ የምፅአት ቀን ምልክቶች!

‹‹በአፍሪካ ትልቁ አምባገነን›› የሚል ተቀፅላ የተሰጣቸው የሊቢያው ኮሎኔል መሀመድ ጋዳፊ እና የግብፁ ሆስኒ ሙባረክ በህዝባዊው እምቢተኝነት ከስልጣን መነሳታቸው በመሰል አገዛዞች ስር ያደሩ ሕዝቦችን ለለውጥ ማነቃቃቱ የሚጠበቅ ነው፡፡ በተለይም ከራሳቸው መንግስት ተኳርፈው አስተማማኝ የዲሞክራሲ ተቋማትን በገነቡ የምዕራብ ሀገራት በብዛት የሚኖሩ ዜጎች ላሏት ኢትዮጵያ ንቅናቄው የፈጠረው ተመሳሳይ መነሳሳት ቀላል ባለመሆኑ ኢህአዴግን ሊወጣው ከማይችለው ቅርቃር ውስጥ ከቶታል፡፡ የዚህ ተጠየቅም ቀድሞ እንዲህ አይነት ችግሮች ሲፈጠሩ ድርጅቱ ‹እሳት ማጥፊያ› ያደርጋቸው የነበሩ አጀንዳዎቹ ያለፈባቸው (Expired) መሆናቸውን ማሳየት ነው፡፡

ሰባቱ ‹‹ቀኖና››ዎች
ስርዓቱ ከሃያ ሁለት ዓመታት በላይ በስልጣን የመቆየቱ ምስጢር ከሁለት ምንጭ የሚቀዳ ነው፡፡ አንዱ የታዘዘውን ሁሉ ያለ ምንም ማንገራገር የሚፈፅመው ጠመንጃ አንጋቹ (መከላከያ ሰራዊት፣ ፌደራል ፖሊስ እና የደህንነት መዋቅሩ) ሲሆን፤ ሌላኛው ደግሞ ከፖለቲካው ፍልስፍና የሚወረሱ አጀንዳዎቹ ናቸው፤ ይሁንና ለጊዜው የታጠቀውን ኃይል ወደ ጎን ብለን ስርዓቱ ‹‹የፖለቲካዬ መገለጫዎች›› ብሎ እንደ ቀኖና ይዟቸው የነበሩትን ሰባት ጉዳዮች በደምሳሳው ብንቃኝ የመቃብር አፋፍ ላይ የቆመ ስርዓት ስለመሆኑ የማመላከት አቅም አላቸው ብዬ አስባለሁ፡፡

፩. የገጠር ፖሊሲ
ኢህአዴግን የሶስት ፓርቲዎች ግንባር አድርጎ በመመስረቱ ሂደት የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው፣ በሀገሪቱ ከሚገኙ የገጠር ከተሞች ከሽሬ ጋር በሚዋሰነው ‹‹ደደቢት በርሃ›› ላይ የተመሰረተው ህወሓት ሲሆን፣ መስራቾቹም ሆኑ አብዛኛው አባላቱ ከአርሶ አደሩና የገጠር አካባቢዎች የወጡ ናቸው፡፡ የህወሓት የታሪክ ንባብ እንደሚያረጋግጠው ትጥቅ ትግል ያስፈለገበት ዋነኛ ምክንያቶች ሁለት ነበሩ፤ የብሄር
ጭቆናን እና የትግራይ አርሶ አደር ለአስከፊ መከራ ተዳርጓል የሚል፡፡

ድርጅቱ ለትግል ካሰለፋቸው አባላቱ ሁለት ሶስተኛው ከእርሻ ሥራ በቀጥታ የተቀላቀሉ ስለመሆናቸው ድርሳናቱ ያወሳሉ፡፡ በወቅቱ በተድበሰበሰ መልኩ የቀረፁት የፖለቲካ ፕሮግራም በመሬትና በብሄር ጥያቄ ላይ የተንጠለጠለ እንደነበር ይታወቃል፤ ይሁንና ከትምህርት ገበታ ተሰውረው፣ በረሃ የገቡት ወጣቶች ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ምናልባትም ‹‹‹መሬት የመንግስት ነው› የሚለው ፖሊሲያችን የሚቀየረው በመቃብራችን ላይ ነው›› ወደሚል ኦሪታዊ የፖለቲካ አቋም (ቀኖና) የተመለሱት የኢትዮጵያ ተማሪዎች የ‹‹መሬት ላራሹ››ን ትግል ጠልፎ ወደስልጣን የመጣው ደርግ፣ ህወሓት በተመሰረተ ልክ በአስራ አራተኛው ቀን የካቲት 25 ቀን 1967 ዓ.ም መሬትን በተመለከተ መሬትን ያራሹ ባደረገው አዋጅ የሰጠው ምላሽና ያገኘው ድጋፍ ሌላ አማራጭ የነፈጋቸው ይመስለኛል (ህወሓት የተመሰረተው የካቲት 11 ቀን 1967 ዓ.ም መሆኑን ልብ ይሏል) በነገራችን ላይ ለኢትዮጵያውያን ፖለቲከኞች መሬት ከኢኮኖሚ ይልቅ ፖለቲካዊ ጠቀሜታው እንደሚበልጥ በርካታ ማሳያዎች አሉ፡፡

የሆነ ሆኖ ከኢህዴንና ኦህዴድ ጋር ተጣምሮ ኢህአዴግን የመሰረተው ህወሓት በ1983 ዓ.ም ለመንግስታዊ ስልጣን መብቃቱን ተከትሎ ራሱን ‹የኢትዮጵያ አርሶ አደር ነፃ አውጪ› አድርጎ አስተዋውቋል፡፡ በተጨማሪም ‹‹በቅዱስ መፅሀፌ ‹አብዮታዊ ዲሞክራሲ› መርህ መሰረት የቀመርኩት›› የሚለውን ‹‹ገጠርን እና ግብርናን ማዕከል ያደረገ የልማት እስትራቴጂ›› በፖሊሲ ደረጃ ከማውጣቱም በተጨማሪ በተለያየ ጊዜ ባሳተማቸው መጻህፍት እና ጥናቶች የአርሶ አደሩን ህይወት በከፍተኛ ደረጃ እየቀየረው እንደሆነ ለማስረዳት ሞክሯል፡፡ በአናቱም ሀገሪቱ ያላት ሀብት የሰው ኃይልና መሬት መሆኑ ለሚከራከርበት ንድፈ-ሃሳብ ቅቡልነት አስተዋፅኦ ያደረገ ይመስለኛል፡፡

በቀዳሚዎቹ ሶስት ሀገር አቀፍ ምርጫም አፅንኦት ሰጥቶ የተሟገተው ‹‹ለአርሶ አደሩ የምታገል ፓርቲ ነኝ›› እና ‹‹አርሶ አደሩ ይደግፈኛል›› የሚል እንደነበረ ይታወሳል፡፡ ይሁንና በምርጫ 97 በከተሞች በደረሰበት ያልተጠበቀ ሽንፈት እንዲያ ከበሮ የደለቀለትን ‹‹ገጠርና ግብርናን ማዕከል ያደረገ የልማት ስትራቴጂ›› ለድንገቴ (አልቦ ቅድመ-ዝግጅት) ለውጥ ይዳርገ ዘንድ መገደዱን የሚጠቁሙ ምልክቶች እየታዩ ነው (የትራንስፎርሜሽን እቅዱ፣ የአባይ ግድብ፣ የመከላከያ ኢንስዱትሪ እና የኮንዶምኒየም ቤቶች ግንባታ የተበጀተላቸው ባጀት ስርዓቱ በአዋጅ የነገረንን የገጠር ልማት ፖሊሲ፣ ያለኮሽታ መቀየሩን ያመላክታል) የአብዮቱን የምፅአት ቀን
ካቃረቡት ዋነኛ ምክንያቶች አንዱ ነው፡፡

፪. የብሔር ጥያቄ
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝየህወሓት መስራቾች በርሃ ለመግባት ሌላኛው ዋና ምክንያት ‹‹ነፃ የትግራይ ሪፕብሊክ››ን ለመመስረት ቢሆንም በጊዜው በአቅራቢያቸው የሚንቀሳቀሰው ኢህአፓ ይህንን ሴራ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነትን ለሚያስቀድመው የአካባቢው ህዝብ በማጋለጥ ትልቅ የፖለቲካ ኪሳራ ስላደረሰባቸው የ‹‹ነፃነት›› ጥያቄያቸውን ወደ‹‹የብሄር ጭቆና›› እንዲቀይሩ መገደዳቸውን በጉዳዩ ዙሪያ የተዘጋጁ በርካታ ድርሳናት አጋልጠውታል፡፡ ከድርጅቱ በተለያዩ ምክንያቶች የወጡ የአመራር አባላትም በፃፏቸው ‹ገድሎች› እንደአተቱት ከዚህ በኋላ ነው ‹‹በሀገሪቱ የአንድ ብሄር የበላይነት ነግሷል›› የሚለው ተረታ ተረት በማርክሲዝምና ሌኒንዝም አስተምህሮ ተተንትኖ በማጎን የድጋፍ መቀስቀሻ የተደረገው፡፡ የሆነ ሆኖ ለህወሓት መደርጀት ዋናው ምክንያት ተጋኖ የተቀነቀነው የጎጠኝነት ፕሮፓጋንዳ ሳይሆን፣ የወታደራዊው ደርግ ጭካኔ የተሞላበት ጭፍጨፋና አፈና ያስመረረው በሙሉ በቅርብ ያገኘውን የፋኖዎች ድርጅት መቀላቀል መምረጡ እንደነበር ከጊዜው ንባብ መረዳት ይቻላል፡፡

ከድል በኋላ ኢህአዴግ የቀድሞውን ‹‹አሀዳዊ መንግስት›› በብሔር ላይ ወደ ተመሰረተ የ‹‹ፌደራል መንግስት›› ያስቀየረኝ መግፍኤ ‹‹በኢትዮጵያ አስከፊ የብሄር ጭቆና መንበሩ ነው›› የሚለው መከራከሪያውን ዛሬም ድረስ እንደ በቀቀን ሲደጋግመው ይደመጣል፡፡ የግንቦት ሃያ ድልን ተከትሎ ሀገሪቱን የአፍ መፍቻ ቋንቋን መስፈርት ባደረገ ቀመር በዘጠኝ ክልላዊ መንግስት እና በሁለት ራስ ገዝ ከፍሎ ማስተዳደሩ ለብሄር ጭቆና የማያዳግም መፍትሄ ቢያስመስለው፣ ዛሬም ድረስ በምርጫ ቦርድ ተመዝግበው በሰላማዊ መንገድ ከሚታገሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል አርባ አራቱ ‹‹የብሄራችን ጥያቄ ገና አልተመለሰም›› በሚል ሀቲት በብሄር የተደራጁ መሆናቸው፤ በኦሮሚያ፣ በሶማሊያ እና ጋምቤላን መሰል አካባቢዎች ደግሞ ጠመንጃ ያነሱ የብሄር ድርጅቶች መኖራቸው ስርዓቱ በብሄር ጥያቄ ረገድ የታሪክ ፈተናን ማለፍ እንደተሳነው መረዳት ይቻላል፡፡

በኢትዮጵያ ሰማይ ስር የብሄር ጥያቄ ‹ዳግም ላይነሳ መልስ አግኝቷል› ትርክት ምፀት የሚሆነው በሀገሪቱ ከሚገኙ ክልሎች በብዙ እጥፍ ያነሰ የህዝብ ቁጥር ያለው ሐረሪ፣ የኢህአዴግ አጋር የሆነው ‹‹የሐረሪ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት-ሐዲድ››ን ጨምሮ ‹‹የሐረሪ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ-ሐሕዴፓ›› እና ‹‹የሐረሪ ብሔራዊ ሊግ-ሐብሊ›› የተሰኙ የፖለቲካ ድርጅቶች መኖራቸው ነው (በአፋርም አራት ህጋዊ የፖለቲካ ድርጅቶች አሉ) እነዚህ እውነታዎች ለስርዓቱ ክሽፈትና የአብዮቱ የምፅአት ቀን በጣም የተቃረበ ለመሆኑ በቂ ምልክቶች ናቸው፡፡

፫. የኢኮኖሚ ዕድገት
ኢህአዴግ ስልጣን ላይ በወጣበት የመጀመሪያዎቹ ዓመታት የቀድሞ ሊቀ-መንበሩ ‹‹ህዝባችን በቀን ሶስቴ እንዲበላ እናደርጋለን›› ብሎ በአደባባይ ቃል መግባቱም ሆነ ‹‹በአጭር ጊዜ ውስጥ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት ተርታ ያቆመኛል›› በሚል ሽፋን ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን የደፈጠጠበት የ‹‹ልማታዊ መንግስት›› ጩኸቱ አለመሳካት ሌላኛው የአደባባይ ተቃውሞን የሚጋብዝ ነው፡፡ የስራ አጥ ቁጥር አለቅጥ መጨመር እና የዋጋ ንረትን መቆጣጠር አለመቻሉም የምፅአት ቀኑን መቃረብ አብሳሪ ‹ሰይጣን› ከአንዳች ሸለቆ መቀሰቀሱ አይቀሬ ነው፤ የዶ/ር መረራ ጉዲና ‹‹የሚበላውን ያጣ ህዝብ መሪዎቹን ይበላል›› ትንቢትም የሚያመላክተው ይህንኑ ነው፡፡

፬. የእስልምና እምነት
በሀገሪቱ ከፍተኛ ተከታይ ካላቸው ዋነኛ ኃይማኖቶች መካከል እስልምና አንዱ ነው፡፡ እንደኃይማኖቱ ልሂቃኖች ምስክርነት ኢህአዴግ የእምነቱን ተከታዮች መብት ለማክበር ከቀድሞ አገዛዞች የተሻለ ውጤት አለው፡፡ ይሁንና በምትኩ ከምዕመኖቹ ያገኘው ጠንካራ የፖለቲካ ድጋፍ ብቻውን ያረካው አይመስልም፡፡ ምክንያቱም ከተባባሪዎቹ የመጅሊስ መሪዎች ጋር በመመሳጠር ኃይማኖቱን ‹አጋር ፓርቲ› አድርጎ እስከ መቁጠር ደርሷልና፡፡

በርግጥ አብዛኛው ሙስሊም ያለፉትን አራት ሀገር አቀፍ ምርጫዎች ግንባሩን ከመምረጥ አልፎ በየመስጂዱ ከሶላትና ፀሎት በኋላ ‹‹ኢህአዴግን ምረጡ›› የሚሉ ድምፆች በርክተው እንደነበር ዛሬ በአገዛዙ ላይ የመረረ ተቃውሞ ከሚያሰሙ ምዕመናን አረጋግጫለሁ፡፡

…‹ታሪክ ራሱን ይደግማል› እንዲሉ የዘርፉ ምሁራን አገዛዙ እንደነገስታቱ ዘመን በእስልምና አስተምህሮት ላይ ጣልቃ በመግባቱ ከ2003 ዓ.ም ታህሳስ ወር ጀምሮ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የእምነቱ ተከታዮች ‹‹መንግስት በሃይማኖታችን ጣልቃ መግባቱን ያቁምልን!›› በማለት ላቀረቡት ጥያቄ ምላሹ በታጠቀው ኃይል በመሆኑ ለከፋ መስዋዕትነት ተዳርገዋል፡፡

ይህ አይነቱ መንግስታዊ ሽብርተኝነት ከቀን ቀን እየሰፋና እየጠነከረ በመሄድ ላይ ነው፡፡ እውነታውን የሚያብራራ አንድ ገጠመኜን እዚህጋ ላንሳ፡፡ ይኸውም ባለፈው ቅዳሜ (ነሐሴ 14 ቀን 1967 ዓ.ም) ከጠዋቱ አራት ሰአት ተኩል አካባቢ የቤቴ በር ጠንከር ባለ መዳፍ ተደጋግሞ ሲቆረቆር ከፈትኩት፤ የፖሊስ መለዮ ከለበሰ ወጣት ጋር ተፋጠጥን፤ ‹‹ምን ነበር?››

‹‹የቤቱ ባለቤት አንተ ነህ?››
‹‹አይ! እኔ ተከራይ ነኝ››
‹‹የሚሞላ ፎርም ስለያዝኩ ጥቂት ጥያቄዎችን ላቀርብልህ ነው!››‹‹ግባ!›› ገብቶ ከተቀመጠ በኋላ ስለመጣበት ጉዳይ ከማውራቱ በፊት እንዲህ አለኝ፡-‹‹አንድ ነገር ልምከርህ፤ የደንብ ልብስ የለበሰውን በሙሉ መታወቂያ ሳታይ አመነህ ወደ ቤትህ አታስገባ!›› ‹‹ለምን?››
‹‹አክራሪዎቹ የፖሊስ ልብስ ለብሰው ወንጀል እየፈፀሙ ነው››

…በጣም አዘንኩ፤ ይህ አገዛዙ ከእስልምና ውጪ ያለውን ህዝብ በእምነቱ ላይ በጥላቻ እንዲነሳሳ (እርስ በእርስ እንዲበላላ) ምን ያህል ዕርቀት እየተጓዘ እንደሆነ የሚያሳይ ሀላፊነት የጎደለው ድርጊት ነው፡፡ …ሁሉም ጉዳይ ጊዜው ያለፈበት መሆኑ በጀ እንጂ፣ የባለስልጣናቱ ፍላጎት ግልፅ ነው፡፡ ኩነቱ ግን ለግንባሩ መዳከም ከፍተኛ አስተዋፅኦ ሲያደርግ፣ ለለውጥ ፈላጊው ደግሞ ታላቅ ድል መሆኑ ነው፡፡

፭. የምዕራብ ሀገራት ድጋፍ
በ1980ዎቹ መጨረሻ አካባቢ የአሜሪካ ዲፕሎማቶች መለስ ዜናዊን እና ኢሳያስ አፈወርቂን ‹‹አዲሱ የአፍሪካ መሪዎች ትውልድ›› የሚል ካባ ይደርቡላቸው የነበረበት ያ ‹‹ደግ›› ዘመን እንደዋዛ አልፏል፤ ኢህአዴግ፣ የሻዕቢያን ያህል ከምዕራባውያኑ ጋ ወደለየለት ጠላትነት ደረጃ ባይደርስም፣ እንደቀድሞ ባደናቀፈው ቁጥር ‹‹እኔን!›› ብለው በሚነጠፉለት አይነት ‹ፍቅር› ላይ አለመሆኑ ግን እርግጥ ነው፤ በተለይም የ1997ቱን ድህረ ምርጫ ተከትሎ ከቅንጅት አመራርና አባላት ጋር የተከሰተው አለመግባባት የፈታበት መንገድ፣ ሀገራቱ በኢትዮጵያ ላይ የሚከተሉትን የግንኙነት ፖሊሲ ቆም ብለው እንዲከልሱ አድርጓቸዋል፡፡ የአውሮፓ ህብረት፣ ስዊዲንና ኖርዌይ ደግሞ ጠንከር ያለ አቋም እንዲይዙ አስገድዷቸዋል፡፡ ይህ ሁኔታ ኢትዮጵያን በመሰለ ነጭ ደሀ ሀገር ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ‹በሌላ መንገድ እቀርፈዋለሁ› ወይም ‹ራሴ እወጣዋለሁ› የሚሉት አይነት አይደለም (ከባጀቱም አብዛኛው በእነርሱ እርዳታ እና ብድር ላይ የተመሰረተ መሆኑ ሳይዘነጋ ማለት ነው)

ከአንድ ወር በፊት በአውሮፓ ህብረት ፓርላማ ‹‹የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ንዑስ ኮሚቴ››ን ወክለው በኢትዮጵያ ከሰብዓዊ መብት መጣስ ጋር ተያይዘው የሚሰሙ ችግሮችን ለመፈተሽ የአራት ሀገራት ተወካዮች ያሉበት አንድ የልዑካን ቡድን መጥቶ ነበር፤ ይህ ቡድን ከመንግስት ባለስልጣናት ጋር በተወያየበት ጊዜም ለፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር አንድ ጥያቄ አቀረበ፡፡ ‹‹ቃሊቲ ማረሚያ ቤት የሚገኙ የህሊና እስረኞችን መጎብኘት እችላለሁን?›› የሚል፡፡ ጥያቄውም ተቀባይነት በማግኘቱ ቡድኑ ወዳዘው አመራ፤ ይሁንና ቃሊቲ ያሉ የፖሊስ ባለስልጣናት የልዑኩን ቡድን ጉብኝት እንዳያደርግ በመከልከል ‹ኩም› አድርገው በመጣበት እግሩ መልሰውታል፡፡ በሁኔታው በእጅጉ የተበሳጩት የቡድኑ አባላትም ዕለቱኑ በሂልተን ሆቴል ‹‹›› በሚል ርዕስ በበተኑት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ በስርዓቱ ተፈፅመዋል ያሏቸውን ወደ ስምንት የሚደርሱ አንኳር ችግሮች ከዘረዘሩ በኋላ፤ በእስር ላይ የሚገኙት ጋዜጠኞች፣ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላት፣ እንዲሁም ከሀይማኖት ጋር በተያያዘ የታሰሩ ሰዎች እንዲፈቱ ጠንከር ባሉ ቃላት ጠይቀዋል፡፡ ይህ ሁኔታም ከአሜሪካ ጋር
የነበረው የሲሲሊያ ማፊያ ‹‹የጡት አባት›› አይነት ግንኙነቱ ወደ መናፈቅ እየተቀየረ ለሄደበት ስርዓት ፍጻሜውን ለማቅረብ መልካም የሚባል አጋጣሚ ይመስለኛል፡፡

፮. የዲሞክራሲ ተቋማት ያለመኖር
ዲሞክራሲን ባህል ባደረጉ ሀገራት የሚኖሩ ህዝቦች ለደህንነትም ሆነ ለህግ የበላይነት ዋስትና የሚያገኙት በምርጫ ካርድ ውስን ለሆነ ጊዜ በስልጣን ላይ የሚፈራረቁ ፓርቲዎች ሳይሆን ቀድመውንም ተደላድለው በታነፁ የዲሞክራሲ ተቋማት ነው፡፡

በኢትዮጵያ አስቸጋሪ ጉዳዮች አንዱ በዚህ በኩል የተሰራ ሥራ አለመኖሩ ነው፡፡ ኢህአዴግ ለዲሞክራሲ ተቋማት ያለመታከት እየሰራ እንደሆነ ለማደናገር ይሞክርበት የነበረው መክራከሪያው መክሸፉን ለማረጋገጥ፡- ህገ-መንግስቱን ራሱ በጠራራ ፀሀይ ደጋግሞ መገርሰሱ፣ ነፃ የፍትህ ስርዓት አለመኖሩ፣ ራሱ የፈጠረውን ነፃ ፕሬስ መልሶ መብላቱ፣ የነፃ ምርጫ ቦርድ እጦት፣ እያቆጠቆጠ የነበረው የብዙሃን ፓርቲ ስርዓት በ2002ቱ ምርጫ በአውራ ፓርቲ መተካቱ፣ የሲቪክና ሙያ ማህበራት ከተፅእኖ ነፃ መሆን አለመቻል… ከበርካታ ማሳያዎቹ ጥቂቶቹ ናቸው (በነገራችን ላይ አገዛዙ ድሮውንም በአንደበቱ እንጂ በልቡ ግራ ዘመም በመሆኑ እነዚህ ተቋማት ‹አስፈላጊ ናቸው› ብሎ ሊያምን የሚችልበት ምክንያት አይኖረውም፤ ምዕራባውያንን ሲሸነገል ካልሆነ በቀር ማለቴ ነው፤ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ሀሳዊ- መሲሂነቱ በመጋለጡ ለእንዲህ አይነት ጉዳዮች ብዙም ሲጨነቅ አይታይም)

፯. የመለስ ህልፈት
መቼም የመለስ ዜናዊ ህልፈት ለኢህአዴግ፣ አቦይ ስብሃት ነጋ እንዳሉት ‹‹በቀለ መጣ፣ በቀለ ሄደ፤ ፋጡማ መጣች ፋጡማ ሄደች፤… አይነት ፖለቲካ ነው›› ብሎ የሚያምን የዋህ የሚኖር አይመስለኝም፤ እኛ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳንሆን፣ የፖለቲካ ጉዳዮቻችንን የሚከታተሉ የሌላ ሀገር ዜጎች በሙሉ መለስ ለድርጅቱ ሁሉም ነገር እንደነበር ጠንቅቀው ያውቃሉ፤ በስልጣን ላይ ባሳለፋቸው ሃያ አንድ ዓመታትም የውስጥንም ሆነ የውጪን ተቃውሞ እና ጫናን ያለ ኪሳራ እንዴት መፍታት እንዳለበት ተክኖታል፤ ከምዕራቡ ሲኳረፍ ወደ ምስራቅ ምን ይዞ እንደሚሄድ ያውቃል፤ የሰጣቸውን ትዕዛዝ ያለአንዳች ማመንታት የሚቀበሉ እልፍ አዕላፍ ታጣቂዎቹንም የግል ታዛዦቹ ማድረግ ችሎ ነበር፤ ባልተመረጠበት አካባቢም የድምፅ ቆጠራው እንዴት እንደሚስተካከል ጠንቅቀው የተረዱ ‹‹ምርጫ አስፈፃሚዎች››ን ከጎኑ ማሰለፉ ተሳክቶለታል፤ ፍትህን እንዴት ማዛባት እንደሚችሉ የገባቸው ስፍር ቁጥር የሌላቸው ዳኞችም አሰልጥኗል፤… ግና! (ምናልባትም ኢትዮጵያን አምላኳ ሲታደጋት) እነዚህን ሁሉ አንድ ላይ አጣምሮ የሚቆጣጠር እርሱን መሳይ ተተኪ አላስቀመጠም፤ ይህ ነው ሶስተኛውን አብዮት (ሕዝባዊ ንቅናቄ) የተሳካ ከሚያደርጉ (መደላድል እንደተፈጠረ ከሚያመላክቱ) ቁልፍ ጉዳዮች አንዱ፡፡ የፓርቲው ቀሳውስትና ዲያቆናትም ‹የምፅአት ቀኑን በአርማጌዶ ዘመቻ ለመቀልበስ ማን ይመራናል?› የሚለው ጥያቄ ዕብሪት ያደነደነውን መንፈሳቸውን አልፈስፍሶታል፡፡

በጥቅሉ ከላይ የተጠቀሱት ሰባቱ የስርዓቱ ‹‹የማዕዘን ድንጋይ›› በነበሩበት አለመገኘት ወይም የማጭበርበሪያ አጀንዳ መሆናቸው ተጋልጠው ከአገልግሎት ውጪ መሆን የለውጡን አብዮት የህዝብን ፍላጎት በመጨፍለቅ ሊገድብ የሚችል ኃይል እንዳይኖር ያደረገው ይመስለኛል፡፡ አገዘዙ እንደለመደው ዛሬም ‹አርሶ አደሩ መረጠኝ›፣ ‹ብሔር ብሔረሰቦች አከበሩኝ› ‹የሃይማኖት ነፃነትን አስከብሪያለሁ›፣ ‹ሀገሪቱን በልማት ባቡር አከነፍኳት›… የመሳሰሉት ለተጭበረበረ ምርጫ መከራከሪያ ሆነው የሚቀርቡት ‹ካርዶች› ተበልተውበታል፡፡

የነፃነቱ ደውል
ከዚህ በኋላ በኢትዮጵያ ጠረቤዛ ላይ የተቀመጠው አማራጭ አንድ ብቻ ነው፤ በጥቂት ወራት አሊያም በአንድና ሁለት ዓመት ውስጥ ውጤቱን አስቀድሞ ማወቅ ከማይቻልበት ህዝባዊ ንቅናቄ የሚፈጥረው አብዮት ጋር መፋጠጥ ወይም ህዝብንና ህግን በማክበር የ2007ቱን ምርጫ ተዓማኒና ተቀባይነት ባለው መንገድ አካሄዶ ከታሪክ ጋር ማበር፡፡ በእኔ እምነት ሁለተኛው መንገድ በምንም መልኩ ከየትኛውም አማራጭ ጋር ሊነፃፀር አይችልም፡፡ ሀገሪቱን ማረጋጋት የሚችለውም ሆነ በእውነተኛው የለውጥ ባቡር የሚያሳፍረው ይህ ነው፡፡

እርግጥ ነው እንዲህ አይነት ጉዳዮችን ደፍሮ በአደባባይ መነጋገሩ ከስርዓቱ በኩል እንደተለመደው ‹አመፅ ናፋቂ› ወደሚል ጠርዝ ያስገፋል፣ አገዛዙን አግዝፈው በሚያዩት ደግሞ ከምኞት የሰረፀ ባዶ-ተስፋ መምሰሉ አይቀሬ ነው፤ ይሁንና ኢህአዴግ እንደማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት ከታሪክ ዑደት ውጭ ሊሆን የሚችልበት ተዓምር አለመኖሩን ወይም ‹የምመጣበት ቀን አይታወቅምና ተዘጋጅታችሁ ጠብቁኝ› እንደሚለው የመፅሀፉ ትእዛዝ አይነት ድንገቴ በሚፈጠሩ ኩነቶች መፃኢ ዕድሉ የሚወሰን አይደለም ብሎ መከራከሩ ብዙ አያስኬድም፤ ምክንያቱም እንደ መንግስት ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በስልጣን ላይ ስለቆየ ኃይል ነውና የምናወራው፡፡ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር በአንድ ወቅት በምክር ቤት ውስጥ ‹‹መንግስት ማየት የተሳነው አይደለም ያያል፤ መስማት የተሳነው አይደለም ይሰማል›› ሲል እንደተናገረው ሁሉ መንግስትም በግልባጩ ከስሩ ባደረ ህዝብ ይመዘናል፣ ይፈተናል፣ ውጤቱም በሰራው ልክ ይሆናል፡፡ ዘመኑን የኢህአዴግ የመጨረሻ ወቅቶች እንድለው የሚያስገድደኝ ከዚህ ግምገማ የተነሳ ነው፡፡

የሆነ ሆኖ የዲሞክራሲን መሰረት የሚጥለው የአብዮት ምዕራፍ መከፈቻው ዕለት በጣም ተቃርቧል፤ የነፃነቱ ደውልም በጥሪው የተኙትን ሊያነቃ ከደጅ ደርሷል፤ በሀገሬ ተራሮችና ኮረብቶች የነፃነት ጅረት ያለ ከልካይ የሚፈስበት ያች የተቀደሰች ዕለት ደርሳለች፤ በርግጥም በሁሉም የሀገረ ጥቅም እና በሁሉም ዜጋ መብት በደል የፈፀመው የጉልበት አገዛዝን ከመሰረቱ ፈነቃቅለው ፍትህ የሚሰበክባቸው፣ ዲሞክራሲ የሚሰፍንባቸው፣ ሰብዓዊ መብት የሚከበርባቸው የሙክራቦቻችንን ቅፅር የሚገነባው የለውጥ ንፋስ፣ ከፍታቸው ሰማይ ጥግ ከሚደርሱት ተራሮቻችን፣ ቁልቁል ሊንደርደር ሲያኮቦኩብ ይታየኛል፡፡

(ከለውጡ በኋላስ? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ፣ ሊከሰት የሚችለውን ‹ፖለቲካል ፓራዳየም› እና ራሳቸውን ‹አማራጭ ኃይል› ያደረጉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተስፋ ሊጣልባቸው ይችላሉ? ወይስ ከዚህም ወደ ከፋ መከራ የሚያደርሱን ‹የዳቢሎስ ፈረስ› ናቸው? የሚሉትን ጥያቄዎች ከፓርቲዎቹ ስንስክሳር ጭምር መፈተሹን ሳምንት እመለስበታለሁ፤ አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንደሚያስቡት ዓላማችን ኢህአዴግን ሽረን፣ እንርሱን ማንገስ እንዳለሆነ ይረዱ ዘንድ መምከሩ አስፈላጊ ነው፤ ይህ መፈንቅለ መንግስት እንጂ አብዮት ሊሆን አይችልምና)



(ተመስገን ደሳለኝ)

Sunday, September 1, 2013

አረመኔው የሕወሐትና የደሕንነት ሹም

የሕወሐት አባልና የአገር ውስጥ ደህንነት ዋና ሃላፊ የነበረው /ስላሴ /ሚካኤል ከያዘው ስልጣን መነሳቱን ምንጮች በመጥቀስ ከሁለት ወር በፊት ዘገባ አቅርበን ነበር። በጭካኔው የሚታወቀውና በሙስና የተነከረው /ስላሴ በሙስና ዘብጥያ ወርዷል። በእስር ቤት በሺህ የሚቆጠሩ ወገኖችን
ያሰቃይ የነበረው /ስላሌ ከበረሃ ጀምሮ በርካታ የድርጅቱን ታጋዮች በመረሸን እንደሚታወቅ ባለፈው ዘገባ መገለፁ ይታወሳል። በትግሉ ዘመን የፓርቲው አባለት « ፆታዊ ግንኙነት ስታደርጉ ተገኝታችኋል…» በሚሉና ሌሎች ተልካሻ ምክንያቶች እንዲረሸኑ በበላይ አመራር ውሳኔ የተላለፈባቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ የፓርቲው አባላት (ታጋዮች) ለመግደል ይጣደፉ ከነበሩት መካከል ኢሳያስና /ስላሴ ዋናዎቹ ነበሩ አቶ መለስ ሁለቱን አባላት ወሳኝ በሆነው የደህንነት ቢሮ ቁልፍ ስልጣን የሰጧቸው « አድርጉ » የተባሉትን ያለማመንታት ተግባራዊ እንደሚያደርጉ ጠንቅቀው ስለሚያውቁ ነበር። /ስላሴ ስልጣን በጨበጠ ማግስት በአንድ ቀን አርባ የቢሮው አባላትን ( መኮንኖች ተብለው ነው የሚጠሩት) እንዳባረረ የገለፁት ምንጮቹ፣ በየጊዜው በመቶዎች የሚቆጠሩ አባላትን « ተሃድሶውን አልተቀበላችሁም፣ የቅንጅት ደጋፊዎች ናችሁ..» በሚሉና ሌሎች ምክንያቶች ከማባረርእስር ቤት እስከመወርወር የደረሰ እርምጃ ሲወስድ ቆይቷል። ከመለስ ጋር በሃሳብ ያለተስማሙ ሁለት ከፍተኛ ባለስልጣናትን በገዛ መኖሪያ ቤታቸው በገመድ በማነቅና በስለት በማረድ የጭካኔ ተግባር ያስፈፀሙት /ስላሴና ኢሳያስ መሆናቸውን ተገልጧል። በግፍ የተገደሉት የመገናኛ / አቶ አየነውና የቤተመንግስት የደህንነት ሹም አቶ ዘርኡ ናቸው።
መስከረም 2 ቀን 1996. የኢትኦጵ ጋዜጠኛን ቢሮው በማስጠራት ለሁለት ሰአት ያክል ካስፈራራው በኋላ እንደሚገድሉት ዝቶ አሰናበተው። ጋዜጠኛው 15 ቀን ውስጥ አቋሙን አስተካክሎ፣ የመረጃ ምንጮቹን አሳልፎ ካልሰጠ እንደሚገደል ነግሮ ያሰናበተው አረመኔው /ስላሴ፣ መስከረም 20 ቀን 1996ዓ፣ም ሰባት የፌደራል ፖሊሶችን በማሰማራት ጋዜጠኛው የግድያ ሙከራ እንዲፈፀምበት አድርጓል። ፖሊሶቹ አካሉን ካጎደሉትና ክፉኛ ከደበደቡት በኋላ ድልድይ ውስጥ ወርውረት እንደሄዱ ይታወቃል። 1997 እና 98 . በሰላማዊ ዜጎች ላይ የተወሰደውን ጭፍጨፋ፣ እስርና ድብደባ ከጠ// ትእዛዝ በመቀበል ተፈፃሚ ያደረገና ዋና ተዋናይ የነበረው /ስላሴ፥ ዜጎች ያሰቃይበት ወደነበረው ማእከላዊ እስር ቤት ተወርውሯል።

(ከኢየሩሳሌም አርአያ)