የዝንጀሮዎቹ ጌታ አጭር ታሪክ የተወሰደው ቻይናዊው ሊዩ ጂ/ Liu-Ji (1311-1375) ከጻፈው የሞራል ማስተማሪያ መጽሐፍ ነው። ይኽ አጭር ታሪክ የአምባገነን ገዢዎች የፖለቲካ ኃይል ከየት እንደሚፈስላቸው (ምንጩ ምን እንደሆነ) እና እንዴት ምንጩን በመቆጣጠር የአምባገነኖችን አቅም መቆጣጠር አልፎም ምንጩን በማድረቅ አምባገነኖችን ማስራብ እንደሚቻል በምሳሌ አድርጎ ግልጽ ያደርጋል። ሰለዚኽ የሰላማዊ ትግል ተመራማሪው እና ዘመናዊ የፖለቲካ ሳይንስ ጠበብቱ ሲድኒ ታይ (Sidney Tai) ከቻይንኛ ወደ እንግሊዘኛ ቋንቋ ተረጎመው። የእንግሊዘኛ ትርጉሙን “በማጭበርበር መግዛት” (“Rule by Tricks”) የሚል ርዕስ
ሰጠው እና ሰላማዊ ቅጣቶች (Nonviolent Sanctions) በሚል ርዕስ የአልበርት አነስታይን ሰላማዊ ትግል ምርምር ተቋም በሚያትማት ጋዜጣ ላይ አሳተመው ሲድኒ ታይ (Sidney Tai)። የዝንጀሮዎቹ ቅጣት ሰላማዊ ቅጣት እንደነበር እና የዝንጀሮዎቹ ጌታ ቅጣት ግን የኃይል ቅጣት (Violent Sanction) እንደነበር ወደፊት ከቦታው ስንደርስ እናስተውላለን። በቅርብ ደግሞ ጂን ሻርፕ (Gene Sharp) የተባለው ሌላው የዘመናችን የሰላማዊ ትግል ተመራማሪ እና በካምብሪጅ ዩንቨርስቲ መምህር ይኽን አጭር ታሪክ ከአምባገነን ወደ ዲሞክራሲ በሚለው መጽሐፉ ገጽ 17-18 ላይ ሰላማዊ ትብብር የመንፈግ ትግል (Nonviolent Non-cooperation Struggle) የሚለውን የሰላማዊ ትግል ጽንሰ አሳብ ለማብራራት ተጠቅሞበታል። የዚህ ጽሑፍ ግብ በዚህ አጭር ታሪክ አንባቢዎች እየተዝናኑ እንዲመራመሩ ማድረግ ነው። ይኽ ምርምር በቅርብ ለንባብ ለማቀርበው ጽሑፍ መሰረት ይጥላል የሚል እምነት አለኝ።
በ14ኛ ክፍለ ዘመን በፊውዳላዊቱ ቻይና ውስጥ ቹ (Chu) የምትባል ከተማ እንደነበረች፣ በዚያች ከተማ ውስጥ አንድ ሽማግሌ ሰው ዝንጀሮዎች በፍራቻ ተባብረው እንዲያገለግሉት በማድረግ ይኖር እንደነበር እና የቹ (Chu) ከተማ ኑዋሪዎች በሽማግሌው ብልጥነት እየተደነቁ “የዝንጀሮዎቹ ጌታ (“ju gong”/monkey
master)” ብለው ይጠሩት እንደነበር ይተርካል ሊዩ ጂ/ Liu-Ji በመጽሐፉ መግቢያ።
ይኽ ሽማግሌ ሰው ሁልጊዜ ማለዳ እየተነሳ በቁጥጥሩ ስር የነበሩትን ዝንጀሮዎች ያሰልፍ እና ትልቁ ዥንጀሮ የቀሩትን ዝንጀሮዎች እየመራ ወደ ተራሮች ወስዶ ፍራፍሬ እንዲያስለቅማቸው ትዕዛዝ ይሰጠው ነበር። ሽማግሌው በዝንጀሮዎቹ ላይ በደነገገው ህግ መሰረት እያንዳንዱ ዝንጀሮ በየቀኑ በተራራ ውሎው ከለቀመው ፍራፍሬ ውስጥ አንድ አስረኛውን (1/10) ለሽማግሌው መለገስ አለበት። የተጫነበትን ግዴታ ማሟላት ያልቻለ ዝንጀሮ እንደሚቀጣም ይደነግጋል ህጉ። ፈርተው እና ተሸብረው አሜን ብለው እንዲገዙ ለማድረግ። ዝንጀሮዎቹ ከተራራ ውሎዋቸው ሲመለሱ የተሰጣቸውን ህግ አክብረው ግብር ያስገባሉ። ስለዚህ ፈቅደው ባይሆንም ፈርተው ዝንጀሮዎቹ ለሽማግሌው ትብብር ለግሰውት ነበር ማለት ነው። ይኽን ማድረግ የተሳናቸው ዝንጀሮዎች ማታ ርህራሄ የሌለው ግርፍ (ቅጣት) ይፈጸምባቸዋል። መቃወም የሚታሰብ ጉዳይ አልነበረም ለረጅም ጊዜ። እያንዳንዱ ዝንጀሮ ብቃወም ሽማግሌው የሚፈጽምብኝ ቅጣት ርሃብ ከሚያደርስብኝ ቅጣት ይበልጣል በሚል ፍራቻ የሚጠበቅበትን ግብር ከፍሎ ተርቦ ማደርን ይመርጥ ነበር። ቅጣት ፍራቻን ፍራቻ ደግሞ የፖለቲካ ጸባይን ይቆጣጠራል። አንዳንዴም በተራሮቹ ላይ የሚለቀም ፍራፍሬ እጥረት ስለነበር ኑሮ ለዝንጀሮዎቹ እጅግ የመረረ ነበር። በዚህ አይነት ዝንጀሮዎቹ የሽማግሌውን አምባገነናዊ አገዛዝ ተቀብለው ለረጅም ዘመን ግልጋሎታቸውን እየለገሱት አብረው ይኖሩ ነበር በማለት ሊዩ ጂ (Liu-Ji) የሞራል ትምህርት ታሪኩን ይጀምራል።
ከእለታት አንድ ቀን በተራሮች ውለው የሚጠበቅባቸውን አንድ አስረኛ (1/10) ፍራፍሬ ለሽማግሌው ከገበሩ በኋላ ወደ ታጠረ ማደሪያቸው ገብተው ሳለ በመካከላቸው የነበረች ትንሽቱ ዝንጀሮ፡
“እኛ በምንውልበት ተራሮች ላይ ፈራፍሬ የሚያፈሩትን ትክሎች የተከላቸው ይኽ ሽማግሌ ሰው ነውን? ” በማለት የቀሩትን በዕድሜ የሚበልጧትን ዝንጀሮዎች ጠየቀች።
ከዚኽ በፊት ይኽን አይነት ጥያቄ ሰምተውም አስበውትም አያውቁም ነበር ዝንጀሮዎቹ። ስለዚህ ትንሽ ዝም ካሉ በኋላ ዝቅ ባለ ድምጽ “ አይደለም። ትክሎቹ የሚበቅሉት በራሳቸው ነው።” በማለት ለጥያቄዋ መልስ ሰጡዋት።
ትንሽቱ ዝንጀሮ ትንሽ ካሰበች በኋላ ጥያቄዋን በመቀጠል፡ “ታዲያ፣ ፍራፍሬዎቹን ካለሽማግሌው ፈቃድ መልቀም እና የራሳችን ማድረግ ለምን አንችልም?” በማለት አይን አይኗን የሚመለከቱን ዝንጀሮዎች ጠየቀቻቸው።ለጥያቄው መልስ ከመስጠታቸው በፊት ዝንጀሮዎቹ ነቃ ነቃ ማለት ጀመሩ። ከዚያ ጋል ባለ ስሜት እና ከፍ ባለ ድምጽ በአንድነት፡ “ አዎ፣ ሁላችንም ካለሽማግሌው ፈቃድ የለቀምነውን ፍራፍሬ መውሰድ እንችላለን” አሉ።
አሁንም ትንሽቱ ዝንጀሮ ጥያቄዋን በመቀጠል፡ “ታዲያ፣ ለምን ለሽማግሌው ታዛዥ ሆንን? ለምን ተባበርን? ለምን ለሽማግሊው አሜን ብሎ መገዛትን/መገበርን መረጥን? ለምን ትብብራችንን አንነፍገውም? ለምን እራሳችንን ነፃ አናወጣም?” ብላ ጥያቄዋን ሳትጨርስ ዝንጆሮዎቹ ድንገት ሁሉም ነገር ገባቸው። ነቁ። የሽማግሌው ጌታነት (ገዢነት) ምንጩ እነሱ ትብብር መለገሳቸው መሆኑን አወቁ። የተለገሰ ነገር ሊነፈግ ይችላል። ትብብር የለገሱት በፈቃደኛነት (መርጠው/በምርጫ) ሳይሆን በፍራቻ ቢሆንም የለገሱትን ትብብር መንፈግ እንደሚችሉ ድንገት ተከሰተላቸው። ካለዝንጀሮዎቹ ትብብር ሽማግሌው ገዢያቸውም ሊሆን እንደማይችል ሁሉ ወለል ብሎ ታያቸው።
ትብብር በመለገሳቸው ነፃነታቸውን አሳልፈው መስጠታቸው ሳይቀር ገባቸው። ተጸጸቱ። ሽማግሌው ነፃነት ከሰጣቸው የሚበላው ፍራፍሬ ስለሚያጣ ነፃነታቸውን እንደማይሰጣቸውም ቁልጭ ብሉ ታያቸው። የለገሱትን ትብብር በመንፈግ አሳልፈው የሰጡትን ነፃነታቸውን በእጃቸው ማድረግ እንደሚችሉ ሁሉ ተገነዘቡ። ነፃነታችን ለካ በራሳችን እጅ ነው ማለት ጀመሩ ትልልቆቹ ዝንጀሮዎች ለትንሽቱ ዝንጀሮ እራሳቸውን እየነቀነቁ።
በዚያኑ ሌሊት ሽማግሌው እንቅልፍ ላይ ሳለ ዝንጀሮዎቹ የማደሪያቸውን በር ከፈቱ። ሽማግሌው ከእነሱ እየተቀበለ በጎተራው ያጠራቀመውን ፍራፍሬ በሙሉ ወስደው በአካባቢያቸው ወደሚገኝ ጫካ ሄዱ። ከዚያ በኋላ ዳግም አልተመለሱም ዝንጀሮዎቹ። ሽማግሌው እንደተለመደው በማለዳ ተነስቶ ወደዝንጀሮዎቹ ማደሪያ ሲሄድ አንድም ዝንጀሮ ባለማየቱ ደነገጠ። ጎተራውም ባዶ መሆኑን ሲያይ ደግሞ ዙሪያው ገደል ሆነበት። ጠዋቱ ጨለመ ለዝንጀሮዎቹ ጌታ። የሚበላው አጥቶ በረሃብ ሞተ። ታዛዥነት(Obedience)፣ ትብብር (Cooperation) እና አሜን ብሎ መገዛት/መገበር (Submission) የተባሉትን የፖለቲካ ኃይል ምንጮች ዝንጀሮዎቹ ስለነፈጉት (ስላደረቁበት)።
በመጨረሻ ሊዩ ጂ/ Liu-Ji፥ “አምባገነኖች ህዝባቸውን የሚገዙት ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ሳይሆን በብልጥነት እና በማሞኘት ነው። እንደነዚያ አይነቶቹ ገዢዎች ልክ እንደ ዝንጀሮዎቹ ጌታ ናቸው። ህዝባቸው ካወቀ እና ከነቃ በኋላ ግን ብልጥነታቸው ያከትማል። ህዝባቸውን አዋርደው በግፍ የሚገዙበት መጠን ከፍ ባለ መጠን ደግሞ ህዝባቸው ነፃነቱ በእራሱ እጅ እንዳለ የሚያውቅበትን ጊዜ ያቀርቡታል” በማለት ታሪኩን ያበቃል።
መደምደሚያ (ስለ ሰላም ትግል ጽንሰ አሳብ መነሻ ጠቃሚ ንድፈ አሳብ)፥
የሰላም ትግል እምነት የሚነሳው ህዝብ አድርግ የተባለውን ሁልጊዜ እሺ ብሎ ላያደርግ እንዲሁም አታድርግ የተባለውን ሊያደርግ ይችላል ከሚል ቀላል ፅነሰ አሳብ ነው። ህዝብ የጠላውን መንግስት ሁልጊዜ በፍራቻ ያከብራል ማለት የዋህነት ነው። ስለዚኽ (1) ሰራተኞች ኢኮኖሚን የሚያሽመደምድ የስራ ማቆም እርምጃ ሊወስዱ ይችላሉ። (2) ነጋዴው ግብር አልከፍልም ሊል ይችላል። (3) ባለሙያዎች/ባለክህሎቶቹ ሰራተኞች ለመንግስት የሚለግሱትን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ የስልክ መገናኛ፣ የፕላን ማውጣት እውቀት/ክህሎት ሊነፍጉ እና መንግስትን ጨለማ ውስጥ ሊያስገቡት ይችላሉ። (4) ቢሮክራሲው እንዲፈጽም የተሰጠውን መመሪያ እሺ ላይል ወይንም ሊለግም እና ገዢው ቡድን በተለመደው ቅልጥፍና ህዝብ መግዛት ሊያዳግተው ይችላል። (5) ወታደሩ፣ ፖሊሱ እና ደህንነት በህዝብ ላይ እንዲፈጽሙ የታዘዙትን ወከባ፣ ስለላ፣ እስር፣ ግድያ ሁል ጊዜ እሺ ብለው ላይፈጽሙ ወይንም ሊለግሙ ይችላሉ። (6) የመንግስት ካዝና ሊራቆት እና ለፖሊስ፣ ለደህንነት፣ ወታደሮች እና ለካድሬዎች የሚከፍለው ደሞዝ ሊያጣ እና ላይታዘዙለት ይችላል። እንግዲህ ህዝብ ገዢውን ቡድን ካላከበር፣ ሰራተኞች ስራ ካቆሙ፣ ቢሮክራሲው መመሪያ የማይፈጽም ከሆነና ወታደሩ ህግ ማስከበሩን ቸል የሚል ከሆነ የገዢው የፖለቲካ ኃይል ምንጮች ተዳከሙ ወይንም በመድረቅ ላይ ናቸው ማለት ነው። ምንጩ ሰደርቅ የሚፈስለት ምግብ ይቆማል። ገዢው ቡድን ይራባል ብሎም ይሞታል እንደ ዝንጀሮዎቹ ጌታ። የማይደፈር ይመስል የነበረው አምባገነን መንግስት ከካርድ እንደተገነባ ህንጻ ይፈርሳል። ሞሊሶቪች ድምጽ ሲሰርቅ ሰርቢያዎች ይሕን ነበር ያደረጉት። ነፃነታቸውን ከእጃቸው አስገቡ። ስለዚህ ቦንብ፣ ታንክ፣ ጠበ መንጃ፣ መድፍ የተባሉት ህዝብ መግደያ፣ ተቋሞች መበተኛ፣ ትምህርት ቤቶች እና ፋብሪካዎች ማፍረሻ፣ የገጠር እና የከተማ መንደሮች ማቃጠያ እና ህዝብ በተለይ ሽማግሌዎች፣ አዛውንቶች፣ እና ህፃናት እንዲሰደዱ ማድረጊያዎች እና ሰብዓዊ መብት መርገጫ፣ ስልጣኔ አጋች እና አፍራሽ መሳሪያዎች መጠቀም አያስፈልግም ነፃ ለመውጣት። ሶሪያን ተመልከት።
በክፍል ሁለት/2 ደግሞ ከፍ ብሎ ቀለል እና ጠቅለል ባለ መንገድ ያነበብናቸውን የፖለቲካ ኃይል ምንጮች ዘርዘር እና ረቀቅ አድርገን መልሰን እንጎበኛቸዋለን። ከዝንጀሮዎች ወጥተን ወደ ሰው ልጅ ማህበረሰ በመግባት።
ግርማ ሞገስ
(girmamoges1@gmail.com)