በስደት የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር አስተባባሪ ኮሚቴ
Coordinating Committee of Exiled Members of Ethiopian Teachers’ Association
የተሰጠ መግለጫ
ጥቅምት 14, 2005 ዓ/ም
በመምህራን ላይ ጥቃቱ ቀጥሏል፣ትግሉም እንዲሁ።ወያኔ/ኢሕአዲግ በመምህራን ላይ የሚያካሄደውን መጠነ ሰፊ ጥቃት በተለያየ ስልት በስውርና በግልጽ በመንቀሳቀስ ካለፉት ዓመታት በባሰና በከፋ መልኩ ቀጥሎበታል።በተለይ ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ላይ መምህራን ባደረጉት የሥራ ማቋም አድማና ከዚሁ ጋር ተያይዞ ባቀረቡት የመብት ጥያቄ ሳቢያ የአፋናውና የጥቃቱ ሁኔታ በአደገኛነቱ እጠርዝ ላይ ደርሷል። ወያኔ በኢትዮጵያና በሕዝቧ ላይ የሚፈጽመውን ደባና የማጭበርበር መሣሪ ተግባሩ ላይ ዛሬም እንደትላንቱ ተጠምዶ የቀጠለበት መሆኑን ከኢትዮጵያ ሕዝብ ቀርቶ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ባላቸው የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ድርጅቶና ከበርከታ የመንግሥታት አካላት የተሰወረ አይዶለም።
ባለፈው ዓመት የመምህራንን የመብት ጥያቄ ለማቃለል፣ለማኮሰስና የጭብጡን አቅጣጫ ለማሳት የጥቂቶችና በችሎታ ማነስ አማራጭ ያጡ መምህራን ጥያቄ ነው የሚል በያኔው ጠ/ሚኒስትር የቅጥፈት ማብራሪያ ለወያኔ ፓርላማ መቅረቡን እናስታውሣለን።ከዚህ በባሰም የሕዝቡን ሥነልቦና ይሰርቃል በሚል አስተሳሰብ “ ከሽብርተኞች ጋር ያበሩ” በማለትም ለዉሸቱ ክስ ማጠናከሪያ ቀርቦ ነበር።እንደዚህ በመሰሉ ተራና መሠረተቢስ ውንጀላዎች መምህራንን አንገት ለማስደፋት የሚሠራው ደባ አሁንም እየተካሄደ ይገኛል።
ከደባዎቹ መገለጫ አንደኛው የብዙሐን መምህራን በነፃ የመደራጀት መብት መግሰስ ቀደሚዉን ሥፍራ ይዟል። ይህ መብት የተነፈገው ከ1985 ዓ.ም ጀምሮ ቢሆንም ያሁኑን ለየት የሚያደርገው በትምህርት ሚኒስቴር አጋፋሪነት የክልል መስተዳድሮች፣ የክልል ትምህርት ቢሮዎች ፣ከዚያም በታች ባሉት እርከኖች እስከ ወረዳና ት/ቤቶች ድረስ ትዕዛዝ ወርዶ የመምህራን ማህበሩ አመራር ከት/ቤት መሰረታዊ መምህራን ማህበር እስከ ከፍተኛው እርከን ድረስ በወያኔ/ኢሕአዲግ አባላት እንዲያዝ ተብሎ የ2004 ዓ.ም የዘመቻ ዕቅድ ሆኖ ተግባራዊ ተደርጓል።
በዚህና በመሳሰሉት ሕገወጥ እርምጃዎች የተማረሩና ግፉን ለመጋፈጥ የቆረጡ መምህራን ተለጣፊው ማህበር ተብየው በመምህራን ውስጥ የወያኔ የስላላ ክንፍ እንደማይወክላቸውና ሕጋዊነትም እንደሌለው በመግለጽ ከደመወዛቸው ለማህበሩ የሚቀነስባቸው ገንዘብ እንዲቆም በመጠየቅ የአባልነት ክፍያውን አቋርጠዋል።ይህ እርምጃ በአማራ ክልልና በአዲስ አበባም በሰፋት ቀጥሏል።የተለጣፊዉን የገቢ ምንጭ ለማድረቅና ዕውቅናም ለመንፈግ የሚደረገው እንቅስቃሴ በሌሎችም ክልሎች መዳረስ ያለበት ወቅታዊና ተገቢ የትግል ስልት እንደሆነ በስደት የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር አባላት አስተባባሪ ኮሚቴ ያምናል።በተጫማሪም መምህራን የሚተማመኑባቸውን ሐቀኛ መሪዎች አጭተው በማስቀመጥ ትግሉን እንደአመቺነቱ በህቡዕና በግልጽም መቀጠል ይጠባቅባቸዋል።
ሌለው በአሁኑ ወቅት የተከሰተው የወያኔ/ኢሕአዲግ መምህራንን የሚያዋክብበትና ቁም ስቅል የሚያሳይበት ብሎም ለመቀጣጫነት የሚያገለግለውንና ሊያባርር የሚችልበት አዲስ መላ አፈላልጎ ያገኘ ይመስላል።ይህ እንደ አዲስ ግኝት በወያኔ ሥርዓት የሚራገበው ዕቅድ “ የመምህራንና የትምህርት ተቋማት አመራር የሙያ ፈቃድ አሰጣጥና እድሳት ” የሚል ስያሜ ይዞ ብቅ ብሏል። ዕቅዱ ላይ ላዩን ሲያዩት እንከን ( ክፋት) ያለው ላይመስል ይችላል።ችግሩ ግን ያለው በወያኔ በማር የተሸፈነ ሬት የማቅረቡ ተፈጥሮአዊ በሕርዩ ላይ ነው።ይህ አካሄዱ ደግሞ ኢትዮጵያውያንንም ሆነ የውጪውን ዓለም የሚያደናግርበት፣የሚያወናብድበት ፣የሚያታልልበትና የሚከፈፍልበት መሰሪ ተግባሩ ነዉ።ከዚህ አኳያ በመነሳት “ የሥራ ወይም የሙያ ፈቃድና እድሳትን” ተግባራዊነት በተመለከተ የተዘጋጀውን ሰነድና ይዘቱን በከፊል እንመልከት።
ትምህርት ሚኒስቴር የካቲት 24 /2004 ዓ.ም ያወጣው ባለ34 ገጽ የመምህራንና የትምህርት ተቋማት አመራር የሙያ ፈቃድ አሰጣጥና እድሳት አፈፃፀም መመሪያ ተሰራጭቷል።በመላ አገሪቱ ከአፀደ ሕፃናት እስከ መምህራን ትምህርት ኮሌጆች በማስተማር ሥራ ላይ ለተሰማሩ መምህራን የትምህርት ሳምንት ተብሎ በተያዘው ከመስከረም 4 ቀን እስከ መስከረም 14, 2005 ዓ.ም በዘለቀው ጊዜ በመወያያ አጀንዳነት መቅረቡ ታውቋል።
በዚህ መመሪያ የሙያ ፈቃድ አስጣጥና እድሳት ሰነድ ከአፀደ ሕፃነት እስከ መምህራን ትምህርት ኮሌጆች በሚገኙ የመንግሥት፣ የሕዝብና የግል ትምህርት ተቋማት መምህራን ፣ እንዲሁም ከአፀደሕፃነት እስከ መሰናዶ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ተቋማት አመራር ላይ ተፈጻሚነት ይኖረዋል ይላል። ይህም መመሪያ በመምህራን ትምህርት ኮሌጆች የሚያስተምሩ መምህራንን ብቻ የሚመለከት እንጂ በሌሎች ኮሌጆችና ዩኒቨርስቲዎች የሚያስተምሩ መምህራንን፣ የኮሌጅና ዩኒቨርስቲ አመራርን የማያጠቃልል መሆኑ አሠራሩ ወጥነት የጎደለውና ከመጀመሪያ ደረጃ እስከ ከፍተኛው እርከን የትምህርት ጥራት ለማስጠበቅ እንዳልታቀደ ያሳያል።
የሙያ ፈቃድ አሰጣጥና እድሳት ዓላማዎች የትምህርትን ጥራት ፣ የትምህርት ተቋማትን አመራር ብቃት
ለማስጠበቅ የሚል ሲሆን ለአመልካቾችም ቅድመ ሁኔታዎች ተቀምጠዋል።ከእነዚህም አንዱ አመልካቾች በመማር
ማስተማሩ ዙሪያ( Paction Research) ያካሄዱበትን ማስረጃ እንዲያቀርቡም የሚያስገድድ ቅድመ ሁኔታ ተቀምጧል።
በአንድ ክፍል ከ100 በላይ ተማሪዎች በሚታጎሩበትና የረባ የላቦራቶሪና ቤተመጸሕፍት በማይሟሉበት አገር ይህ አሠራር
ከቅዣት የሚያልፍ አይሆንም። የወያኔ ት/ሚኒስቴር በምሳሌነት በወሰዳቸው በአሜሪካና በከናዳ የመምህራን ክፍል
ለትምህርትና ለምርምር በሚያስፈልጉ ዕቃዎች የተሟሉ ናቸዉ ። በጀትም አላቸው።ባንድ ክፍል የሚገኙት የተማሪዎች
ብዛትም ከ15-20 ነው።መምህራን በሚያስተምሩበት ክፍል ሆነው በየክፍለጊዜው ተማሪዎች ናቸው ወደ መምህራን ክፍል
የሚሄዱት።በአንደንድ ት/ቤቶች ለዋናው መምህር ረዳት መምህርም ይመደብለታል።በኢትዮጵያ ይህ ሁኔታ የለም።
በዲፓርመንት ደረጃ እንኳን ለተወሰኑ መምህራን ለዲፓርትመንቱ በሚያስፈልጉ እቃዎች ያልተሟላ አንድ ክፍል ነው
ያሏቸው።በዚህ ሁኔታ ላይ የሚገኙ መምህራንን የምርምር ሥራ ካላቀረቡ የማስተማር ፈቃድ አይሰጥም ማለት እብደት
አይዶለምን ?
ከዚሁ ጋር ተያይዞም የተደራጀ የልማት ሠራዊት መገንባት፣የትምህርት ሽፋን ማሳደግ፣የትምህርቱን ሥርዓት
ከአደናቃፊ አመለካከት መጠበቅ፣ኢሕአዲግና መንግሥት በመተካካት ሂደት የደረሱበት እመርታ፣የሀይማኖት አክራሪነት
በኢትዮጵያ በሚሉ አጀንዳዎች አወያይቶ በትምህርት ጉዳይ ሽፋን የፖለቲካ ዓላማውን ለማጠናከር እየሠራ ይገኛል።
አጀንዳዎቹን ስንመለከት ትንሽ ቆሎ ይዞ ወደ አሻሮ መጠጋት እንዲሉ የትምህርት ጥራት ማረጋገጥ፣ የተደራጀ የልማት
ሠራዊት መገንባት፣ የትምህርቱን ሽፋን ማሳደግ በሚል መንደርደሪያ ሽፋን ትምህርቱን ከአደናቃፊ አመለካከት መጠበቅ
የሚለው አባባል በራሱ ስለትምህርት ጉዳይ ከወያኔ አፍራሽ ዕቅድ ውጪ አማራጭ የማይቀርብበት እንደሆነና ያለሕዝቡ
ተሳትፎ እያካሄደ ያለውን አሠራር ከነጉድለቱ እንዲቀጥል በማለም መሆኑን ነው የሚያመለክተው።ይህንንም ስውር ደባውን
ለማጠናከር የሀይማኖት አክራሪነት የሚል ራሱ ወያኔ የፈጠረውን ሕዝብን ማሸበሪያና መከፋፈያ አጀንዳ ሰንቅሮ ትምህርት
ቤቶች በነፃነት እንዳይንቀሳቀሱ ለማፈን ከማቀድ ውጪ ሌላ የሚታሰብ አይሆንም።መቼም ከዕባብ እንቁላል እርግብ
አይጠበቅም።በመጨረሻ የተቀመጠው “መተካካት” ብሎ ፈሊጥ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዘር መድሎ፣ከአምባገነናዊ አገዛዝ፣
ከድህነትና ጉስቅልና----ነፃ ለመውጣትና የሥርዓት ለውጥ ለማምጣት በየአቅጣጫው እየታገለ ባለበት በአሁኑ ወቅት ወያኔ
በመተካካት እመርታ ታይቷል ማለቱ በእርግጥ ለበጣ ነው።ለከት የሌለው የተለመደ ውሸት ነው።በትምህርት ቤቶች
እነዚህንና የመሳሰሉትን አጀንዳዎች ይዞ መቅረቡ መምህራንና ተማሪዎች በአንድነት ቆመው ወደ ሕዝቡ እንዳይዘልቁና
ለፍትሕ፣ ለእኩልነትና ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ታግለው እንዳያታግሉ ለመግታት መሆኑ ግልጽ ነው።
ከዚህ አንፃር መምህራን በየስብሰባዎቹ (ከመስከረም 4-14/2005 ዓ.ም በተደረጉት) ካቀረቧቸው ፈታኝ ጥያቄዎችና
አስተያየቶች በከፊል ለአንባቢያን ግንዛቤ እንዲረዱ ከዚህ ቀጥለን አቅርበናቸዋል፤
1. ከአፀደሕፃነት እስከ መምህራን ትምህርት ኮሎጆች ለሚገኙ መምህራን ብቻ የሙያ ፈቃድ ለመስጠት ለምን
አስፈለገ? የማስተማር ችሎታ ማነስና የትምህርት ጥራት ውድቀት የታየው በነዚህ ደረጃዎች ብቻ ሆኖ ነዎይ?
2. መምህራን በራሳቸው ውሣኔ የማስተማር ሥራውን እየተው ወደ ተለያዩ አገሮች በመሔድ ላይ እያሉ የመምህራንን
ፍልሰት መግታት የተሳነው ት/ሚኒስቴር ይህን የሙያ ፈቃድ ማውጣቱ ፍልሰቱን አያባብሰዉም ዎይ?
3. በአሁኑ ጊዜ በአገሪቱ የመምህርነት ሙያ ምን ያህል ተወዳጅ፣ ማራኪና ሳቢ የሙያ ዘርፍ ሆኖ ነው የሙያ ፈቃድ
መመሪያ ማውጣት ያስፈለገው?
4. የመምህራነትን ሙያ ተወዳጅ፣ ማራኪና ሳቢ ሊያደርጉ የሚችሉ የመምህሩን ጥቅማጥቅም የሚመለከቱ ጉዳዮች
ለምን በመመሪያው ውስጥ አልተካተቱም?
5. መመሪያው ለሙስና የተጋለጠ ነው፤ ምክንያቱም ከቅርብ ኃላፊ የሚሰጥ ነጥብ ስላለና በኃለፊነት ቦታ
የተመደቡትም የሥርዓቱ የድርጅት አባልና ተሿሚዎች ስለሆኑ ለወያኔ/ኢሕአዲግ አባል ለሆኑት በማዳላት የተሻለ
ነጥብ በመስጠት ያልሆኑትን መምህራን ለመጉጃና ለማጥቂያነት ሊጠቀሙበት ስለሚችሉ ነው።
6. በመመሪያው ለሙያ ፈቃድ እድሳት ተመዝነው ስኬታማ ባልሆኑ አመልካቾች ከፍተቱ እንዲሟላ ሁኔታዎች
ይመቻቻሉ ይላል፤ ዝርዝሩ ተብራርቶ አልቀረበም፤ከዚህም በተጫማሪ 70% ውይም 3.5 በታች ውጤት
የሚያመጡ መምህራን በርካታ ሆነው ቢገኙ ክፍተቱን ለማሟላት ወጪ አይጠይቅም? ከአገሪቱ ኤኮኖሚያዊ አቅም
አኳያ እንዴት ይሸፈናል?
7. የሙያ ፈቃድና እድሳት የሚያገለግለው ፈቃድ ለተሰጠበት የትምህርት ደረጃ ብቻ ነው ሲባል 9ኛ እና 10ኛ
በሁለተኛ ደረጃ የሚያስተምር በ11-12( መሰናዶ)፣ የመሰናዶው በኮሌጅ ገብቶ ማስተማር አይችልም ማለት ነው?
ይህ ከሆነስ የመምህሩን የማስተማር መብትና ችሎታ የማዳበር ዕድል አይገድብም ?
8. በመመሪያው የሙያ ፈቃድ ማግኘት ያልቻሉ በማስተማር ሥራ አይቀጥሉም ይላል፤በማስተማር ሥራ የማይቀጥሉ
ከሆነ በምን ዓይነት መንገድ ይሰናበታሉ? በዳረጎት? በጡረታ ወይስ በነፃ?
9. የሙያ ፈቃድ እድሳት ልምድ የተገኘው ከአውስትራሊያ፣ ካናዳና አሜሪካ እንደዚሁም ከኤሺያ አገሮችና ከደቡብ
አፍሪካ እንደሆነ ተጠቅሷል። በእነዚህ አገሮች የሚገኙ መምህራን የኑሮ ደረጃና ለሥራ ምቹነት ከእኛ የኑሮ ደረጃና
ለመማር ማስተማሩ ግብአት የሚሆኑ ነገሮች መሟላት አኳያና አገሪቱ ከምትገኝበት የኤኮኖሚ ሁኔታ ጋር
ይጣጣማል?
10. ከሌላው የመንግሥት ሠራተኛ /ሲቪል ሰርቫንት በተለየ ለመምህሩ የሙያ ፈቃድ ለምን አሰፈለገ?
11. በአገር አቀፍ የመምህራንና የት/ት አመራር የሙያ አሰጣጥ እድሳት ስትሪንግ ኮሚቴ ከፌዴራል ት/ት ሚኒስቴር እስከ ክልሎችና የወረዳ አስተዳደሮች ይቋቋማል ይላል የሚቋቋመው ስትሪንግ ኮሚቴ ገለልተኝነት እስከ ምን ድረስ ነው? ገለልተኝነቱስ የሚያረጋግጠው ማነው? የሚሉ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ቀርበው በቂ ምላሽ የሚሰጥ አካል ባለመገኘቱ ለበላይ አካል እናስተላልፋለን የሚል እንደ መልስ ተሰጥቷል።መምህራን ዕቅዱን እንደማይቀበሉት አሳባቸውን አጠናክረው ማሳወቃቸውን ከደረሰን መረጃ ለመረዳት ተችሏል።በስደት የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር አስተባባሪ ኮሚቴ ይህ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ያምናል።
በሌላ በኩል በተለይ በአዲስ አበባ ከዚህ ከሙያ እድሳት ጎን ለጎን በተለየ የቀረበው አጀንዳ “ የእስልምና አክራሪነትን እንቃወማለን ”የሚል ጭፍን የአቋም መግለጫ እንዲወጣ በወያኔ በኩል ታስቦ የነበረ ቢሆንም በመምህራን ከፍተኛ ክርክርና ተቃውሞ በአገራችን የሀይማኖት አክራሪነት የለም፤ ስለሆነም በሀይማኖቶች መካከል መቻቻልና መከባበር የታሪካዊ አብሮነታችን መገለጫ በመሆኑ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ እናስተላልፋለን በሚል እንዲተካ በመደረጉ የወያኔ ስውር ደባ ከሽፎበታል።
ካለፉት ዓመታት ቀጣይ ሆኖ የሚካሄደው የወያኔ በመምህራን ላይ ያነጣጠረ ጥቃት በሙያ ፈቃድና እድሳት የማስመሰያ ዕቅድ ያጋጠመውን ተቃውሞ በዝርዝር አይተናል።የሙያ ፈቃድ ልምዱ የተቀዳው በዚህ መግለጫ እላይ ከተገለጹት አገሮች ከመሆኑ ባሻገር ተግባራዊነቱ ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር፣ወያኔ ከሚያራምደው ስውር አጀንዳ አንፃር ለመዳሰስ እንገዳደለን።ለምሣሌ በአሜሪካ በማስተማር ሙያ ለተሰማሩ መምህራን በሚያስተምሩት የትምህርት ዘርፍ ከወሰዷቸው ኮርሶች ሌላ በማስተማር ሙያ( Pedagogy - Profession of Teaching ) ሥልጣና ወስደው ይዘጋጃሉ፤ ከዚያም ለ5 ዓመታት የማስተማር ፈቃድ ከየጠቅላይ ግዛቶቹ ትምህርት ቢሮዎች ይሰጣቸዋል።ይህ የሚመለከታቸው ጀማሪ መምህራንና በተለይ ከሌላ አገር በመምህርነት ሲያገለግሉ ወደ አሜሪካ የመጡትንና በሙያው ሊሠማሩ የሚፈልጉትን ነው።በዚሁ በአሜሪካ ባንደንድ ጠቅላይ ግዛቶች የዕድሜ ልክ (Life long ) ፈቃድ የሚሰጥበት ሁኔታም ነበረ።አሁን እየቀረ ቢሆንም።ለብዙ ዓመታት በማስተማር ሙያ የቆዩ መምህራን ግን ሲመረቁ ሙያዊ ትምህርት( Pedagogic) ከሚያስተምሩት ትምህርቶች ( ሒሳብ፣ ኬሚስትሪ፣ እንግሊዝኛ፣ ባዮሎጂ፣----) የወሰዱ ከሆነ በቀጥታ የማስተማሩን ሥራ ይቀጥላሉ፤ፈቃድም አያስፈልጋቸው። ብዙ ዓመት በሥራው ያልቆዩት ግን ከ5 ዓመታት በኋላ ከሙያው ጋር ተያያዥነት ያላቸው አጫጭር የሳምንታት ኮርሶች፣ የማሻሻያ ኮንፍረንሶችና ሴሚናሮች የመምህሩን የሙያ ዝንባሌና ክህሎት ለማሳደግ በማሰብ ይሰጣሉ።ወያኔ መምህራን ፈተና እንዲቀመጡና ፈቃድ እንዲያወጡ የሚፈልገው የመብት ጥያቄ እንዳያነሱና ሰጥ-ለጥ ብለው እንዲገዙ ስለሆነ ተቀባይነት አይኖረውም።የእድሳቱ ጊዜም ለ3 ዓመታት ለ3 ዙር የሚባለው አጠያያቂ ነው። ከ3 ዙር ( ከ9 ዓመታት) በኋላ ምንድነው የሚሆነው?። 3 ዓመት በጣም አጭር ጊዜ ነው መምህሩን ለመጉዳት የታሰበ ነው።
በሌላም አግባብ ስንመለከተው በአገራችን ብዙዎቹ መምህራን ከመምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጆችና ከፔዳጎጂ ዩንቨርስቲዎች ከሚያስተምሩት የትምህርት ዓይነቶች ( Academic Subjects) በተጫማሪ የሙያተኛ ሥልጣና (Pedagogy) ወስደውና ተመርቀው ለብዙ ዓመታት አገራቸውንና ሕዝባቸውን ያገለገሉ ናቸው።ላበረከቱት ግልጋሎት ምስጋናና ማበረታቻ ሲገባቸው እንደ አዲስ ተቀጣሪ ፈቃድ እንዲያወጡ መጠየቁ አስነዋሪ፣ አሳፋሪ፤ አሳዛኝና የማንአለብኝነት ተግባር ነው።ይህን እኩይ ድርጊት ተማሪዎች ፣ ወላጆች ፣ የትምህርት ባለሙያዎችና ባጠቃላይ ሕዝቡ ሊያወግዙት ይገባል።
ወያኔ/ኢሕአዲግ ስፍር ቁጥር በሌለው ዕቅድና አምባገነናዊ እርምጃ መምህራንን ማዋከብና ማጎሳቆል ቀጥሎበታል መምህራንንም ትግላቸውን ቀጥለዋል ። ሌሎች የሕብረተሰቡ አካሎችም እንደመምህራን ሁሉ ፍዳቸውን ማየታቸው አልቀረም።የገበሬዎችን መፈናቀል፣ የገዳማት መደፈርና የመነኮሳት/የመናንያን እንግልት፣ የሙስሊሞች የመደራጀትና የዕምነት ነፃነት መገፈፍ ግድያና ማሰቃየት የፋሺታዊ ሥርዓቱ መገለጫዎች ናቸው። ሁሉም ትግላቸውን ያስተባበሩ ዕለት ወያኔ ወዮለት!!!
መምህራን ታግለው የማታገል ልምዳቸውን ያድሳሉ!
የጋራ ትግል ለድል ያበቃል!!
ዜጎች ሁሉ ዕኩል የሆኑበት አገር ለመገንባት እንታጋል!!
ለበለጠ መረጃ በ eta1941@yahoo.com ሊያገኙን ይችላሉ