ዳግማዊ ጉዱ ካሣ
ክፍል ፩
ማሳሰቢያ፡- ማንም ይሁን ማን የደም ግፊት ካለበት፣ በቀላሉ የሚናደድ ወይ የሚበሳጭ ከሆነ፣ የኢትዮጵያዊነት ስሜቱ የሚያይልበትና ዘወትር የሚያስጨንቀው ከሆነ… ይህን ጽሑፍ በጭራሽ ባያነብ ይመረጣል፡፡ ይህ መጣጥፍ በተቻለ መጠን ከተሞክሮና ከሕዝባዊ ብሶቶች በመነሣት በስፋት የሚስተዋሉ እውነታዎችን እንዳለ የሚያቀርብ እንጂ በተለመደው የይሉኝታና የመለሳለስ ባህል ተዋዝቶ አንድን ወገን ለማስደሰት ወይ ሌላን ወገን ለማስከፋት ያልታለመበት በመሆኑ አንባቢ ከየትኛውም የስሜት ጫፍ በራቀ ሁኔታ እንዲያነብብ ይመከራል፡፡ መልካም ንባብ!
… “በእግራችሁ ጫማ አድርጉ እንጂ ሁለት እጀ ጠባብ እንኳ አትልበሱ፡፡ በማናቸውም ሥፍራ ወደ ሰው ቤት ስትገቡ ያንን ሥፍራ እስክትለቁ ድረስ በዚያው ቆዩ፤ ሰዎች በማይቀበሏችሁና በማይሰሟችሁ ቦታ ሁሉ የእግራችሁን አቧራ አራግፉና ከዚያ ወጥታችሁ ሂዱ፤ ይህም ለእነርሱ የማስጠንቀቂያ ምሥክር ይሆንባቸዋል፡፡”
ማር. 6፣ 9 - 12
‹ንገረኝ ካልሽማ ተቀይሜሻለሁ፣ ግን አንቺን ትቼ መኖር እፈራለሁ…› የሚለው የቴዲ አፍሮ ዘፈን ትዝ አለኝ - የኢሣትን የዛሬ ልዩ ዝግጅት ስመለከት፡፡ እርግጥ ነው - ይህ መሰሉ ዝግጅት አዲስ አይደለም፡፡ እኔም በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ብዙ ጊዜ ተመላልሻለሁ፡፡ ግን የበደል ነገር በተወሳ ቁጥር ስሜትን እንደአዲስ ስለሚቀሰቅስ ሁልጊዜ ያው አዲስ ነው፡፡ ታማኝ በየነ በዛሬው ዕለት ስለወያኔዎች ኮኬነት ከሲሳይ አጌና ጋር ባደረገው መሳጭ ቃለ ምልልስ ያቀረበው ዝግጅት አንጎልን ያቀውሳል፡፡ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ ሲያስቡት በርግጥም ከማሳበድ ያልፋል - ከዚያ በላይ ካለ፡፡ ለነገሩ ከወያኔ በቀር በዚህ ጊዜ ያላበደ ኢትዮጵያዊ የት ሊገኝ?
ሀተታችንን በአንዲት ቀልድ አዘል ቁም ነገር እንጀምር፡፡ አንድ የአንድ መሥሪያ ቤት ሽማግሌ ዘበኛ ወረፋቸውን ጠብቀው ደሞዛቸውን ቆጥረው ሲረከቡ አሥር ብር እላፊ ይወስዱና እንደወትሮው 300 ብር ሣይሆን 310 ብር ይዘው ይሄዳሉ፡፡ ገንዘብ ከፋይዋ ከፍላ ስትጨርስ ወጪን ከቀሪ በምታወራርድ ጊዜ አሥር ብር መጉደሉን ትረዳለች፡፡ በስህተት ለማን እንደከፈለችም ትውስ ይላትና የማስመለሻ ዘዴዋን ወዲያውኑ ታቀነባብራለች፡፡
በቀጣዩ ወር ደመወዝ ስትከፍል ያቺን አሥር ብር በስህተት የከፈለቻቸውን ዘበኛ ወርኃዊ መሃያቸውን ሊወስዱ ተሰልፈው ታያቸዋለች፡፡ ከዚያም ተራቸው ደርሶ ስትከፍላቸው አሥሩን ብር ቀንሳ 290 ብር ትሰጣቸዋለች፡፡ እሳቸውም ከፊቷ ላይ ሲቆጥሩት አሥር ብር መጉደሉን ይረዱና ‹ ምነው ልጄ! ለምን አሥር ብር ታጎድይብኛለሽ? በቅጡ ቆጥረሽ አትሰጪም እንዴ?› ብለው ይጠይቋታል፡፡ እሷም ‹እንዴ አባባ፣ ባለፈው ወር … ምነው እንኳን … ደመወዝዎን ስከፍልዎት … አሥር ብር እላፊ በከፈልኩዎት ጊዜ ለምን አልመለሱልኝም?› ብላ በሰው ፊት ታሳፍራቸዋለች፡፡ እንደወያኔ የሌባ ዐይነ ደረቅ የሆኑት ሽማግሌ የዋዛ አልነበሩምና ‹እንዴ፣ ምን ማለትሽ ነው! ያኔ የመጀመሪያ ስህተት ነው ብዬ በምሕረት አለፍኩሽ፡፡ አሁን ግን ለሁለተኛ ጊዜ ስህተት ስትሠሪ ልታገስሽ አልቻልኩም፡፡› ብለው ሕዝበ ተሰላፊ ደሞዝተኛን ጭምር በሣቅ ገደሉት፡፡ አዎ፣ ስህተትን በስህተት ማረም የወያኔዎች የባሕርይ ገንዘብ ነውና ይቺን ጨዋታ ከወያኔዎች ተፈጥሮ ጋር በማስተሳሰር ትንሽ ቆዝሙባት - ፈገግ ካሰኘቻችሁም እሰዬው፡፡
ወያኔ ጫካ የገባው የአፄውንና የደርጉን ስህተት በመቃወም ነበር ይባላል - በይባላል ደረጃ፡፡ እንጂ ዋናው ዓላማቸውማ ትግራይን ገንጥለው የራሳቸውን ነጻ ግዛት ለመመሥረት ነበርአሉ፡፡ ስሙ እኮ ‹ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ› ነው፡፡ በለስ ሲቀናውና የውጪዎቹ ደጋፊዎቹ ሃይ ብለው የሀገር ጥፋት አጀንዳ ሲያሲዙት ግን ሃሳቡን ቀይሮ ለታሪካዊ ጠላቶቻችን ምቹ ሆኖ ተገኘና እስካሁን የሆነውና አሁን እየሆነ ያለው ሁሉ ሆነ፡፡
አሁንና ከአሁን በኋላ መወሻሸት የለም፡፡ እቅጭ እቅጩን ነው የምንነጋገረው፡፡ እናም ወያኔ ጫካ የገባው - በገርነት አስተሳሰብ ወስደንለት - ስህተትን ለማረም ከሆነ ወያኔ በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ውስጥ ዓለምን የሚያስቀና ማኅበረሰብኣዊ ሥርዓት ዘርግቶ በትንቢቱ መሠረት ስደት ከኢትዮጵያ ሳይሆን ወደኢትዮጵያ ሊሆን በተገባ ነበር፡፡ በተገላቢጦሹ ታዲያ ስህተትን በስህተት መለሰና ወያኔ ሆዬ ቀጥሎና
እስካሁንም የም(ን)ለውን እንድ(ን)ል ምክንያት ሊሆን በቃ፡፡ በበቀል ተረግዞ በበቀል የተወለደው ወያኔ የነሚካኤል ስሑልን መሰል የአያት ቅድመ አያቶቹን ጭንጋፍ የክህደት ታሪክ እውን ካደረገ ይሄውና 22 ዓመት ሊሞላው ጥቂት ወራት ብቻ ቀርቶታል፡፡ በየት እንደሚመጣ አይታወቅም እንጂ ፈጣሪ ቁናውን ሠፍቶ የጨረሰ ይመስለኛል፡፡ ከፈጣሪ ቢሮ ተፈርሞ የሚወጣን ደብዳቤ የሚያስፈጽም አካል ጊዜው ሲደርስ ራሱ አምላክ ይገልጠዋል፡፡ የሚወጣ እንጀራ ደግሞ ከምጣዱ ያስታውቃልና ዕድሜ ለሰጠን ጊዜው ደርሶ ስናየው የመጪውን ምንነት የምንለየው ይሆናል፡፡
በነገራችን ላይ በዚያን ሰሞን በፈረንጅ ቋንቋ አወለካክፌ የጻፍኩትን ደብዳቤ ለብዙ ድረገፆች ብመይል ከሁለቱ በስተቀር በሌሎቹ የውኃ ይሁን የአልኮል ሽታ ሆኖ ቀረ፡፡ በሀገራችን የጤፋችንን ያህል በተወደደ እንግሊዝኛ እንደምንም ብዬ ዕርሜን ብሞነጫጭር በተለያዬ ምክንያት ተቃዋሚ ተብዬዎቹ ድረገፆች ሸለል አሉኝ፡፡ ‹ቂጥኛም ከውርዴ› መጫወቱ ዱሮም የነበረ በመሆኑ ከተለከፉበት በውል ያልገባኝ ደዌ እስኪፈወሱ በትግስትና በጸሎት መጠባበቅ አለብኝ እንጂ ልከፋባቸው አልፈልግም፡፡ ይሁንና ‹ንገረን ካሉማ … › በሚለው የቴዲ ግልብጥ ዜማ በድርበቡ ልንገራቸው፡፡ እንኳንስ እነሱ ጎብላላዎቹ ሐምሌና ነሐሴም ነጉደዋል፡፡
በቅድሚያ ግን ‹ethiolion.com›ንና ‹zehabesha.com›ን ‘Hit the iron when it is hot’ በሚል ርዕስ የሰደድኩትን ጽሑፍ ማንንም ሳይፈሩ ወይ ሳያፍሩ በራሳቸው ነጻ ምርጫ በማስተናገዳቸው በእጅጉ እንዳመሰግን ይፈቀድልኝ፡፡ የኢትዮጵያ አምላክ ወሮታቸውን ይክፈላቸው፤ ከክፉ ይጠብቃቸው፤ ሥራቸውንም ይባርክልኝ፡፡ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ ሐዋርያ መሆን ማለት እንዲህ ነው - ከልቤ ነው፡፡ ‹ያልፈሱበት ቂጥ አያፍሩበትም› እንዲሉ እነዚህ መድረኮች ቢያንስ ከኔዋ መልእክት አንጻር የሚያሳማቸው ነጥብ አላገኘሁባቸውም - ያዝልቅላቸው፡፡ የሌላውን ግን ሆድ ይፍጀው - ተከድኖም ይብሰል፡፡ እንዴ - በሌባ ጣት የአሳደህ በለው ትየባ ሙሉ ቀን ወይም ሙሉ ሌሊት የተከተበን ጽሑፍ ቅርጫት ውስጥ መክተት ምን ማለት ነው - ነውርም አይደል ወገኖቼ? “ይሄኔ የነእገሌ ቢሆን ኖሮ ብስናትም ቢሆን ከነምናምንቴው ያስተናግዱ ነበር” ልል አማረኝና ዳግመኛ መገናኘት የማይቀር ከሆነ ሆድ እንዳንባባስ ብዬ ተውኩት፡፡ በያም ላይ “ይሄ ደግሞ የማነው ‹ኮምፕሌክሳም›” እንዳልባልም ፈራሁ፡፡ ይህ ድርጊታቸው ግና አያቀባብርም ብቻም ሳይሆን ሌላም ባስባለ፡፡
በመሠረቱ እሥረኛ እሥረኛን ነጻ ሊያወጣ አይችልም፡፡ እሥረኝነት ደግሞ መገለጫው ብዙ ነው፡፡ ጥቅም፣ ዘረኝነት፣ አድርባይነት፣ እወደድ ባይነት፣ ወዳጅነትና ጓደኝነት፣ ይሉኝታ፣ ወዘተ. ኅሊናን ያሳውራሉ፤ ወኔንም ያኮላሻሉ፡፡ የተባለው ነገር እውነት መሆኑ እየታወቀ እንኳን በነዚህ ልቦናን አሳዋሪ ምክንያቶች የተነሣ ሰዎች ከእውነት ይርቃሉ፡፡ የእውነትን ጥሩር የታጠቀ ግን በሚያደርገው ነገር ሁሉ ስለማያፍር እውነትን እንዳመጣጧ ያስተናግዳል፤ መጋፈጥ ካለበትም ይጋፈጣል፡፡ በመጨረሻም እውነት ራሷ ነጻ ታወጣዋለች፡፡
[off
the record] ወገኖቼ! አንዲት ሴት ልጅ ወንድ ልጋብዝሽ ቢላት መታለል የለባትም - በራስ የምትተማመን ከሆነና ሌላ ጉዳይ(ዐመል) ከሌለባት የማንንም ግብዣ በቀላሉና ሳታምንበት መቀበል አይኖርባትም፡፡ ልጋብዝሽ ሲላት ለምን ብላ መጠየቅ አለባት፡፡ ለተራ ወዳጅነት ከሆነም እርሷም እንደወንዱ ሁሉ ልትጋብዝ ይገባታል፡፡ ያኔ አፍ ይኖራታል - የምትጠየቀውን እምቢም እሸም ለማለት እኩል ነጻነት ታገኛለች፤ የጥቅምና የይሉኝታ እሥረኛ ከሆነች ግን ለብዙ አደጋ ትጋለጣለች፡፡ ማን ጋብዞ ማን ማንን እምቢ ብሎ ይሄዳል? “ኧረ! ይህን ሁሉ ገንዘብ ያወጣሁት እህቴ ነሽ ወይንስ አክስቴ?” ብትባል ማጣፊያው ያጥራትና ወደሚቀርባት አሊቤርጎ መጓዝ ነው የሚኖራት ብቸኛ ምርጫ፡፡ በጥቅም የታሠረ/የታወረ ሰው መፈቻ የለውም፤ ግዝትም እንኳን አይፈታውም፡፡ ያጎበድዳል፤ ያዘጠዝጣል፤ ያሸረግዳል፡፡ ተሳደብ ቢሉት ይሳደባል፤ አሽሟጥ ቢሉት ያሽሟጥጣል፡፡ በቃ፣ ብሃፂሩ - ማለትም ባጭሩ - ብኩርናውን በምሥር እንደሸጠው እንደኤሣው ይሆንና የኅሊና ነጻነቱን - የራሱን ማንነትና እምነት ለሌሎች አሣልፎ የሸጠ ባሪያ ይሆናል፡፡ [on
the record] ብዙዎቹን ነጻ ነን ባይ ድረ ገፆችን በምናቤ ስቃኛቸው ለዚህ ዓይነቱ አስቀያሚ ሂደት ሰለባ የሆኑ ይመስሉኛል፡፡ (የከፋው ሰው ሲናገር ለካንስ ለከት የለውም እናንተዬ! ከእያንዳንዱ ዐረፍተ ነገር በኋላ ራሴን ስታዘበው እንዴት እንዴት ነው እምናገረው እባካችሁን?) ይገርማችኋል፡፡ አንዳንድ ድረ ገፆች ትግሬን ሲነኩባቸው ነብር ይሆናሉ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ አማራን ሲነኩባቸው አንበሣ ይሆናሉ፡፡ አንዳንዶች ኦሮሞን ከነኩባቸው ግሥላ ይሆናሉ፡፡ አንዳንዶች ኢሕአዲግን ከነኩባቸው ዓሣማ ይሆናሉ (ዓሣማ ሲናደድ እንዴት ይሆን ግን?)፡፡ አንዳንዶች ታዋቂ ግለሰቦቻቸውን ሲነኩባቸው የቆሰለ አውሬ ይሆናሉ፡፡ አንዳንዶች ግንቦት ሰባትን ወይም ጥምረትን ከነኩባቸው ንብ ይሆናሉ፡፡ አንዳንዶች መድረክን ከነኩባቸው አቦሸማኔን ይሆናሉ፡፡ አንዳንዶች ኢሕአፓን ከነኩባቸው ተርብ ይሆናሉ፡፡ አንዳንዶች ኦነግን ከነኩባቸው አነር ይሆናሉ፡፡ አንዳንዶች አርበኞች ግንባርን በጨረፍታም ቢሆን ነኻ ካደረጉባቸው ኩርፊያቸው አይጣል ነው፡፡ አንዳንዶች ሻዕቢያን ሲነኩባቸው ይገሰላሉ፡፡… አንዳንዶች ያን ወይ ይህን ሃይማኖት ሲነኩባቸው ጭክ እንዳለች ዶሮ ይሆናሉ፡፡ እጅህን አጣጥፈህ ካልተቀመጥህ ጣጣው ብዙ ነው፡፡ ይታያችሁ እንግዲህ - የትኛው ጸሐፊ የትኛውን አካል ሳይነካ ሊጽፍ ይችላል? በቀጥታም ይሁን በተዛዋሪ ይህን ወይ ያን ሳይነኩ እንዴት መጻፍስ ይቻላል? ስንቱ ተፈርቶ፣ ለስንቱስ አሸርግዶና ተሽቆጥቁጦ ይዘለቃል? ምሥጋና ከጻፍክ ግን በተለይ የተመስጋኙ ወገን አቀንቃኝ ባላደራ የሆነ ሚዲያ መሪ ዜናው አድርጎ ቦግ ያደርግልሃል፡፡ ይህም ከንቱነት ይመስለኛል፡፡ አጥብቆ በኩራዝና በሻማ ብርሃን መፈለግስ ደካማ ጎንህን የሚነግርህን ሰው ነው፡፡ አመስጋኝ አማሳኝ ነው እሚባል ከነተረቱ ወዳጄ ልቤ፡፡ ምሥጋና ያነሆልላል፤ ከዓላማም የማናጠብ ጠባይ አለው፡፡ ሰይጣንም የተዋረደው ራሱን ከመጠን በላይ በመውደዱና በራስ ፍቅር በመጠመዱ ነው፡፡ የምሥጋና ምርኮኛ የሚሆን ሰው ወይም ድርጅትም ቢሆን በራስ ፍቅር የተተበተበ ከንቱና ግዑዝ ነገር ነው፡፡ እንደውነቱ ከሆነ ጠንካራ ጎን ተናገሩት አልተናገሩት ምንም አይፈይድም፡፡ እንደ አካሄድ ታዲያ መታበይና በጥቂት ነገር መኩራራት የባሕርይ ዐመላችን እንደሆነ መዝለቁ ያሳስባል፤ ያሳዝናልም፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖ በኢትዮጵያ በሰማንያዎች የሚቆጠሩ ዘውጎችና በመቶዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካም ይሁኑ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች እንደዚሁም በመቶዎች የሚቆጠሩ የሃይማኖት ባለ አክሲዮን ኩባንያዎች አሉ፡፡ ሁሉም ጤነኞች ወይም ሁሉም በሽተኞች ናቸው ማለትም አይቻልም፡፡ ሰው የታየውን ሲጽፍ ከማፈን ይልቅ ታዲያን የሚመለከተው አካል ተመልክቶ ምላሽ እንዲሰጥ ቢደረግ ይበልጥ ጠቃሚ በሆነ ነበር እንጂ በየት ዞረሽ ቀደምሽኝ ዓይነት ገና ከአሁኑ በእከክልኝ ልከክልህ አንዱ የአንዱን ገመና ለመሸፋፈን መሞከሩ ከጅልነት ያለፈ ቡልሃነት ነው - የሥራ ቦታን ያለማወቅ ድንቁርናም ይመስለኛል፡፡ ‹ነጻ አስተያየትን እናስተናግዳለን› እያሉ ሕዝብን ‹የሚፎግሩ› የእነዚህን መሰል ድረ ገፆች አዘጋጆች ቆሽታቸው እንዲህ ጠባብ ከሆነች ፍየል ጠባቂ ቢሆኑ ይሻላቸዋል የሚል አስተያየት አለኝ፡፡ እኔማ ‹ድንቄም ሃሳብን በነጻነት ማስተናገድ!› እያልኩ ማሽሟጠጥ ከያዝኩ ቆይቻለሁ - እንደሠንጋተራና ካዛንቺሶቹ የቡና ቤት እህቶቼ ከንፈሬን ለሽርደዳ በሚያመች መልኩ ሞጥሞጥ በማድረግ፡፡ ሲጥማቸው ይለጥፋሉ - ሳይጥማቸው በሃያ ቁጥር ምስማር ይከረችሙሃል - ያኔ በአንዲት ቃል ወይም በአንዲት ዐረፍተ ነገር እንዳስከፋሃቸው ይገባሃል፤ ያቺን ጦሰኛ ስንጣሪ ሃሳብ ወይም ሐረግ አውጥቶ ቀሪውን ለባለአድራሻው ማድረስም አንድ ነገር ነበር - ግን ኢትዮጵያዊው የትምክህትና የትዕቢት አባዜ የትም ብንሆን መች ይለቀንና፡፡ እንደእውነቱ ግን የሚላክ ነገር መጣም ያለበት ለነሱ ነው ወይንስ ለአንባቢ? እኚህን መሰል ወገኖች አይጋፎረምንና የአቡነ አረጋዊ - ማነው - የአማረ አረጋዊን ሪፖርተር ከኢቲቪ ቀጥሎ በሁለተኛነት በማስቀመጥ ‹ወያኔ ቁጥር ሦስት› ቢባሉ ያንሳቸው ይሆን? ሆ! ‹በጊዜ የጮኸ ጅብ አያሳድረኝም› አሉ! ከአሁኑ የምን ሰውን ለማፈን መሞከር ነው፡፡ ‹ውሻና ባለጌ በቤቱ ይኮራል› እሚባለው ለካንስ ትክክል ነው፡፡ ኤዲያልኝ! ይሄ ኢትዮጵያዊነት ስንቱን ያሳያል ‘ባካችሁን…
ይህ ዓይነቱ ነገር ‹ቂጥ ከፍቶ ክንንብ› ዓይነት ነው እሚመስለኝ፡፡ ሀገር የሚያውቀውን የወያኔን ገመና ከማራገብ ይልቅ የራስን ማንነት በመፈተሸ ከወዲሁ ራስን ማረቅ ይገባል እንጂ በቃላት አጠቃቀም ዙሪያ ዘርፍ እያወጡ በፀጉር ስንጠቃ በመፈላሰፍ የገዛ ወገንን በደጅ ማባረር ሞራላዊም ሆነ ሀገራዊ ርባና የለውም፡፡ ሌባን ሌባ ቢተካው ለውጡ የት ላይ ነው? የወያኔን ቱሪናፋ ቲቪና ሬዲዮ በተቃዋሚ ቱሪናፋ የሚዲያ ውጤት ለመተካት የተያዘ ሩጫ ካለ ያ ትልቅ ስህተት ነውና ከአሁኑ ቆም ተብሎ ቢታሰብበት የተገባ ነው፡፡ ለነገሩ የኢትዮጵያ መሬት በ144 ጠበል ካልተረጨ የሚያበቅለው ሁላ አጋሰስና ደንቆሮ፣ መጭና እንክርዳድ እየሆነ ተቸግረናልና ከአሁኑ ይልቅ የወደፊቱ ቢያስፈራን ሥጋቱ እንደሥጋት ትክክል ነው - ‹የአበራሽን ጠባሳ ያዬ በእሳት አይጫወትም› ወንድሜ፡፡ ቢሆንም ተስፋችን ይበልጡን በፈጣሪ ላይ ነውና አንድዬ እንደሚያስተካክለው ትልቅ ተስፋ አለኝ - ከተደጋጋሚ ቅጣትም እንዲሠውረን ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን፡፡
ወደዋናው ጉዳይ ልመለስ፡፡ ይሉኝታ ከትግራይ ተጠራርጋ ከወጣች ብዙ ዘመን አለፈ ብዬ ለማመን መገደዴን ስገልጥላችሁ ልደብቀው በማይቻለኝ ሀፍረት እየተሸማቀቅሁ ነው፡፡ አዝናለሁ - ግን መናገር ደግሞ አለብኝ፡፡ ይህን እንድልም ነባራዊ ሁኔታዎች ያስገድዱኛል፡፡ ከአንድ ትልቅ የሚባል ማኅበረሰብ ውስጥ ጥቂት የማይባል ወገን በእልህና በቁጪት ተነሳስቶ ቀሪውን ሀገር ሲወርና በምርኮ ይዞ ነጻነትን በመደፍጠጥ ሀብትንና ንብረትን ሙሉ በሙሉ ሲቆጣጠር ይሉኝታቢስነት እንጂ ሌላ ሊባል አይችልም፡፡ እናም በአሁኑ አያያዝ ወያኔና የበቀለባት የትግራይ መሬት በጥቅሉ ይሉኝታና ሀፍረት የሚባሉ ቃላት በመዝገበ ቃላቸው (dictionary) ውስጥ ስለመኖራቸው መጠራጠር ጀምሬያለሁ ብዬ በድፍረት ስናገር በጠንካራ ኢትዮጵያዊነት የምትታወቁ የዚያ ክልል ጥቂት የማትባሉ ባለሦስት ዐይን ዜጎች ከእውነታውና ከብሶቴ አንጻር ብዙም እንደማትቀየሙኝ በመገመት ነው፡፡ አባባሌን የምትጠራጠሩ ካላችሁ አዲስ አበባንና መላዋን ኢትዮጵያን በአሁኑ ወቅት ጎብኙና የምለውን በተግባር አረጋግጡ፡፡ሀብትና ንብረት እንዴት እንደሚያፈሩና በአንድ ቀን አዳር እንዴት ሚሊዮነር እንደሚሆኑ ተውትና ለአነጋገራቸው እንኳን ለከት እያጡ የመጡ ዜጎች ቁጥር ቀላል እንዳልሆነ ትረዳላችሁ፤ ፍርድ ደግሞ ለራስ ነው፡፡ አንዳንዶቹ የዋሃን ትግሬዎች በዘራቸው ማንነት እንዴት እንደሚኮፈሱ እኮ ብታዩ እናንተም ታፍሩላቸዋላችሁ፤ ታዝኑላቸዋላችሁም፡፡ ‹ጥንት በደጉ ዘመን የማውቀው ጓደኛየ እንዲህ ነበር እንዴ?› ብለህ እስክትጨነቅም ድረስ ታሪክን ወደኋላ ዞረህ እንድትፈትሽ ትገደዳለህ፡፡ (አንዳንዶቹ) ማተብ የሚባል ነገር ያላቸውም አይመስሉም፡፡ አማራነትም ሆነ ትግሬነት በምርጫ ሳይሆን በተፈጥሮ ግዴታ እንደሚገኝ ተዘንግቶ አማራን ከምድረ ገፅ ለማጥፋት የተያዘው ወያኔያዊ ዘመቻ ሊበርድ ያለመቻሉ ምሥጢርም ክፉኛ ያስጨንቃል፡፡
No comments:
Post a Comment