Thursday, March 20, 2014

የጎሣ ግጭቶችና የአለም አቀፉ ማኅበረሰቡ ሚና


(ክፍል ሁለት)
የተባበሩት መንግሥታት 1948 .. ባወጣው የሰብአዊ መብቶች ዓለም አቀፍ መግለጫ አንቀጽ 2 ላይ እያንዳንዱ ሰው በዘር፣ በቀለም፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ ወይም በሌላ አስተያየት፣ በኅብረተሰብ ምንጭ፣ በሃብት፣ በትውልድ፣ ወይም በሌላ አቋም ምክንያት ምንም ዓይንነት ልዩነት ሳይደረግበት በመግለጫው ላይ በተጠቀሱት መብቶችና ነፃነቶች በእኩል የመጠቀም መብት እንዳለው የደነግጋል። ይህንን ድንጋጌም መነሻ በማድረግ ዘረኝነትንና ሌሎች ከሰብአዊ መብቶችና ነፃነቶች ጋር የሚቃረኑ የአድልዎ ተግባራትን ለማስቀረት በሚል በአለም አቀፍ ደረጃ በርካታ ስምምነቶችና መግለዋዎች በተባበሩት መንግስታት አባል አገራት ጸድቀው ወጥተዋል።

ከእነዚህም መካከል በተባበሩት መንግስታት ጸድቆ የወጣውና ከጃንዋሪ 04 ቀን 1969 .. ጀምሮ ሥራ ላይ የዋለውማንኛውንም ዓይነት የዘር አድልዎ ለማስወገድ የተደረገ ዓለም አቀፍ ስምምነት”  በሚል የሚታወቀው ሰንድ በመግቢያው ላይ ስምምነቱ ያስፈለፈበትን አላማ ይገልጻል። ይኽውም፤ በዘር ልዩነት ላይ የተመሠረተ የበላይነት ፍልስፍና ሳይንሳዊ እውነትነት የሌለው፣ ከሥነ ምግባር አንጻር የሚወገዝ፣ ከማኅበራዊ ኑሮ አንፃር ፍትሕ የጎደለውና ትክክል ያልሆነና አደገኛ አስተሳሰብ መሆኑን፤ እንዲሁም በንድፈ ሃሳብ ደረጃም ሆን በተግባር የትም ቦታ ለአድሏዊ የዘር ልዩነት መኖር በቂ ምክንያት የሌለ መሆኑን ይገልጻል። አክሎም፤ በሰው ልጆች መካከል በዘራቸው፣ በቀለማቸው፣ ወይም በጎሣቸው ምክንያት የሚደረግ መድሎ በሕዝቦች መካከል ወዳጅነት የተሞላበትን ሰላማዊ ግንኙነት ለመፍጠር እንቅፋት የሚሆን የሕዝቦችን ሰላምና ደኅንነት፣ በአንድ መንግሥት ሥር አብረው በመልካም ሁኔታ ተስማምተው የሚኖሩትንም ሰዎች ሕይወት የሚያናውጥ መሆኑን ይገልጻል።

በአለም ታሪክ ጎልተው የሚጠቀሱት የዘር ማጥፋት እና የዘር ማጥራት ወንጀሎች አብዛኛዎቹ መንሰዔዎቻቸው የጎሣ እና ዘርን መነሻ ያደረጉ ግጭቶች ናቸው። 1915 አንድ ሚሊዮን አርመናዊያን በቱርኮች የጭካኔ እርምጃ ያለቁበትን ክስተት፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የፖሊሽ ዎች በሂትለር የተጨፈጨፉበትን፣ 2 ሚሊዮን ካምቦዳዊያን ኮሚኒስት በነበረውና Khmer Rouge ተብሎ በሚጠራው የአማፂ ቡድን የተገደሉበትን፣ በመቶ ሺህ የሚጠጉ የኢራቅ ኩርዶች 1987-1988 .. በቀድሞው መሪ ሳዳም ሁሴን የተጨፈጨፉበትን፣ 8 መቶ በላይ የሰው ህይወት የጥፋበት 1994 የሩዋንዳው የዘር ማጥፋት ወንጀል (Genocide) እና 1992 እስከ 1995 ባለው ጊዜ ውስጥ በዩጎዝላቪያ ሰርቦች በሰነዘሩት ጥቃት 2 መቶ በላይ ቦስኒዎች ያላቁበትን የዘር ማጥፋት ወንጀሎች ልንመለከት እንችላለን። እነዚህ እና ሌሎች ያልጠቀስኳቸውን ነገር ግን በሰው ዘር ላይ ቀላል የማይባል እልቂቶችን ያስከተሉ ክስተቶችን ብንመረምር የአለም አቀፍ ማኅበረሰቡን ባህሪ፣ ለጎሣ ግጭቶች የተሰጠውን የትኩረት መጠን፣ የአለም አቀፉን ፖለቲካ አቅጣጫና ባህሪይ፤ እንዲሁም በእንዲህ ያሉ ግጭቶች ዙሪያ አውንታዊ እና አሉታዊ ገጽታውን ለመረዳት ያስችሉናል።

በእዚህ ዘርፍ ዙሪያ ከፍተኛ ጥናትና ምርምር ያካሄዱት እና ከላይ በተጠቀሱት የዘር ማጥፋት ወንጀሎች ላይም ጥልቅ ምርምር በማድረግ “A  Problem  from  Hell”  America  and  the  Age  of  Genocide የሚል መጽሐፍ ያሳታሙት፤ በ Harvard’s  John  F.  Kennedy  School  of  Government  የሰብአዊ መብቶችና የአሜሪካን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ መምህርት የነበሩትና (እንዲህ ያለ መጽሐፍ ከጻፉ በኋላ ምን ነክቷቸው እንደሆነ ግራ ቢገባኝም) በቅርቡ በኦባማ አስተዳደር በተባበሩት መንግስታት የዩናይትድ ስቴተ አምባሳደር ተደርገው የተሾሙት Prof.  Samantha  Power ከእነዚህ እልቂቶች ጀርባ ያለውን የአለም አቀፉን፤ በተለይም የአሜሪካን መንግስትን አወንታዊ ሚና በርካታ መረጃዎችን በማጣቀስ አስቀምጠዋል። 602 ገጾች ባለው በዚህ መጽሐፋቸው ውስጥ ፕሮፌሰሯ ከእያንዳንዱ እልቂት ጀርባ ድርጊቱ ሆን ተብሎ እንዲፈጸም ሁኔታዎችን በማመቻቸት ወይም ሆን ብሎ በመፍቀድ፣ ወይም ድርጊቱ ሊፈጸም እንደሚችል እና የበርካቶችን ህይወት ሊቀጥፍ እንደሚችል አስቀድሞ እየታወቀ ችላ በማለት እና በአንዳንድ ሁኔታዎችም እልቂቱን ለሚፈጽሙት አካላት የፋይናንስና ሌሎች የቁስ ድጋፎችን በማድረግ የአለም አቀፍ ማኅበረሰቡ፤ በተለይም አገራቸው አሜሪካ የተጫወተችውን ሚና አጉልተው አስቀምጠዋል።

ከላይ በዘረዘርኳቸው እና የአለምን ሕዝብ እጅግ ባሳዘኑትና ባስደነበሩት የጭካኔ እርምጃዎች ዙሪያ ፕ/ር ሳማንታ ፓወር በመጽሐፋቸው ውስጥ በሰፊው የሰጡትን ማብራሪያ በጉዳዩ ላይ በቂ ግንዛቤ ለማግኘት ለምትፈልጉ አንባቢያን እየተውኩ በአፍሪካ ውስጥ ከተከሰተው የሩዋንዳው እልቂት ጋር በተያያዘ ያቀረቡትን ትንታኔ ብቻ ባጭሩ ልጥቀስ። የሩዋንዳውን የዘር ማጥፋት ወንጀል የመረጥኩት አፍሪካ ውስጥ የተከሰተ እልቂት ስለሆነና ከሁኔታው ለኢትዮጵያም ትምህርት ሊሆን የሚችል ነገር ይኖረዋል ከሚል ሃሳብ ብቻ ሳይሆን በዚህ እልቂት ዙሪያ የተባበሩት መንግስታት እና ከኃያላኖቹ አገሮች መካከል የአሜሪካን መንግስት አቋምና ባህሪም በቅጡ እንድንረዳ ያስችለናል በሚል ነው።

የ1994 ዓ.ም.ቱ የሩዋንዳው እልቂት ከመከሰቱ ሦስት ወራት በፊት በአገሪቱ ውስጥ ያለው በሁቱ እና በቱትሲ ጎሣዎች መካከል የተከሰተ የጎሣ ቅራኔ ወደ ተባባሰ ደረጃ ላይ መድረሱን የተረዱት በሩዋንዳ የተባበሩት መንግስታተ የሰላም አስከባሪ ኃይል መሪ የሆኑት ካናዳዊው ሜጀር ጀነራል ሮሜዎ ዳላይሬ የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ለመንግስታቱ ድርጅት ሰጥተው ነበር። በማስጠንቀቂያቸውም ላይ ሊደርስ የሚችለውን የቀረበ የእልቂት አደጋ በመጠቆም ሁኔታውን ከወዲሁ ለመቆጣጠር እንዲቻል የሰላም አስከባሪው ኃይል የሁቱ ታጣቂ ሚሊሻዎችን ትጥቅ እንዲያስፈታ እና በቱትሲዎች ላይ የተነጣጠረውን የጭፍጨፋ እቅድ እንዲያከሽፍ መመሪያ እንዲሰጠውና ተጨማሪም የሰላም አስከባሪ ኃይል እንዲመደብለት የሚጠይቅ ነበር። ይሁንና የሆነው ግን ከዚህ በተቃራኒው ነበር። ከተባበሩት መንግስታት የተገኘው ምላሽ ግን የጀነራሉን ጥያቄ ወደጎን በመተው ተጨማሪ ኃይል ከመላክ ይቅር እዲያውም በጀነራሉ ስር ከነበረው የሩዋንዳ ሰላም አስከባሪ ውስጥ አብዛኛው አገሪቱን ለቆ እንዲወጣ የሚያዝ ነበር። እንዲሁም እልቂቱን በማስተባበር ከፍተኛውን ሚና ሲጫወት የነበረውን የሩዋንዳ ሬዲዮ ጣቢያ አሜሪያ ያላትን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ስርጭቱን እንድታግድ ለቀረበውም ማሳሰቢያ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል። በዚህ እና ሌሎች ምክንያቶች ሳቢያ የ 8 መቶ ሺ ሰው ሕይወት በአሰቃቂ ሁኔታ ሊያልፍ ችሏል።

የሩዋንዳውን እልቂት በተመለከተ የአሜሪካ መንግስት የነበረውን አቋም እና የተወሰዱትን እርምጃዎች በተመለከተ ፕ/ር ሳማንታ ፓወር በመጽሐፋቸው ገጽ 338 ላይ ያስቀመጡትን ማብራሪያ እንዳለለአንባቢያን ለማስቀመጥ እወዳለሁ። ይህውም፦

The commission’s March 1993 report found that more than 10, 000 Tutsi had been  detained  and  2,000  murdered  since  the  RPF’s  1990  invasion.  Government- supported killers had carried out at least three major massacres of Tutsi. Extremist, racist rhetoric and militias were proliferating. The international commission  and  a  UN  rapporteru  who  soon  followed  warned  explicitly  of  a possible genocide. Low-ranking U.S. intelligence analysts were keenly aware of Rwanda’s history and the  possiblilty  that  atrocity  would  occur.  A January  1993  CIA  report  warened  of the likelihood of large –scale ethnic violence. A December 1993 CIA study found
that  some  4  million  tons  of  small  arms  had  been  transferred  from  Poland  to Rwanda, via Belgium, an extraordinary quantity for a government allegedly committed to a peace process. And in January 1994 a U.S. government intelligence analyst  predicated  that  if  conflict  restarted  in  Rwanda,  “the  worst  case  scenario would  involve  one-half  million  people  dying”.  …  When  Woods  of  the  Defense Department’s  African  affairs  bureau  suggested  that  the  Pentagon  add  Rwanda- Burundi  to  its  list  of  potential  trouble  spots,  his  bosses  told  him,  in  his  words, “Look, if  something happens in Rwanda-Burrundi, we  don’t care. Take  it off the list. US national interest is not involved and we can’t put all these silly humanitarian issues on lists. … Just make it go away.”

ከላይ በተጠቀሰው ጽሑፍ ውስጥ በግልጽ እንደሚታየው የአለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሩዋንዳው እልቂት ከመፈጸሙ በፊት እና እየተፈጸመ በነበረበተም ወቅት (100 ቀናት የፈጀ እልቂት ስለነበር) ድርጊቱ እንዳይከሰት ወይም ለማስቆምም ሆነ አደጋውን ለመቀነስ የሚችልበት አስተማማኝ ሁኔታ ላይ እንደ ነበር ነው። ይሁንና ይህን ማድረግ ስላልተፈለገ ምንም አይነት እርምጃ ሳይወሰድ ድርጊቱ እስኪጠናቀቅ ድረስ ከዳር ቆሞ መመልከትን መርጧል። እንደውም እልቂቱ በዚህ መልኩ እንዲጠናቀቅ ቀድሞውንም የታሰብ እስኪመስል ድረስ የተባበሩት መንግስታት የቅድሚያ ማስጠንቀቂያውን ወደጎ መተው እና አደጋ መኖሩ እየታወቀ በተቃራኒው ያለውንም ኃይል ከስፍራው ላይ ማውጣቱ፣ ፖላንድ ላይ የተመረተውን 4 ሚሊዮን ቶን የሚመዝን የተለያዩ የእጅ መሣሪያዎች (ቢላ፣ ገጀራ እና መጥረቢያዎች) ለእርስ በእርስ ግጭቱ እንደሚውል እየታወቀ ወደ ሩዋንዳ እንዲገባ መደረጉ፣ የሩዋንዳን ሕዝብ በዘር በመከፋፈል እርስ በርሱ በጠላትነት እንዲቧደን ቁልፉን ሚና የተጫወተችው ቤልጂየም የቀበረቸው የዘር ፈንጂ የሚፈነዳበት ጊዜው መቃረቡን ስታውቅ በሩዋንዳ የነበረውን የራሷን ሰላም አስከባሪ ኃይል አስቀድማ እንዲወጣ ከማድረጓም ባሻገር በፖላንድ የተመረተውን 4 ሚሊዮን የጦር መሣሪያ ተቀብላ ወገናቸውን ለመጨረስ ለተሰናዱት ሁቱዎች እንዲደርስ ማድረጓ፣ እንዲሁም ይህን ሁኔታ እያወቀ የአሜሪካ መንግስት የወሰደውን ኃላፊነት የጎደለው እና የምንቸገረኝ እርምጃ ስንመለከት እንዲህ አይነቶቹ እልቂቶች ምንም እንኳን አገራዊ ይዘት ቢኖራቸውም እና በጎሣዎች መካከል የሚፈጠሩ ቢሆኑም ሁኔታዎቹ እንዲባባሱም ሆነ ወደ ከፋ እልቂት እንዲያመሩ የሚደረገው ርብርቦሽ ግን አለም አቀፋዊ ይዘት ያለው መሆኑን በበቂ ሁኔታ ያሳያል።

ይህ ሁሉ ሕዝብ በተቀነባበር ሁኔታ በሩዋንዳ ብቻ አይደለም በሌሎቹም የዘር ማጥፋት ወንጅል በተፈጸመባቸ አገሮች ሁሉ እንዲያልቅ ከተደረገ በኋላ የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ለፍትሕ እና ለሰብአዊ መብቶች መከበር ዘብ የቆመ ለመምሰል የሚያደርገው ሽር ጉድ ከልብ መሆኑን እንድንጠራጠር ያደርጋል። እነዚህ እልቂቶች ከተፈጸሙ በኋላ በአለም አቀፍ ደረጃ ፍርድ ቤቶች ተቋቁመዋል፣ በሺዎች የሚቆጠሩ አለም አቀፍ የውይይት መድረኮች ተካሂደዋል፣ በርካታ መጽሐፎችና የጥናት ሥራዎች ተከናውነዋል። ለዚህም በብዙ ሚሊዮን የሚገመት ገንዘብ ፈሷል። ዛሬም ብዙዎች እነኝህን የሕዝብ እልቂቶች እያነሱ እና እየጣሉ ገቢ ማግኛና መተዳደሪያ አደርገውታል። አለም ካለፉት እልቂቶች አሁንም ያልተማረ መሆኑን ግን በየእለቱ በምንሰማቸው ዜናዎች ላይ እንደምናየው በመካከለኛው ምስራቅ የተለያዩ አገሮች በተለይም በአፍጋኒስታን፣ በኢራቅና በሶሪያ፤ እንዲሁም በአፍሪካ ውስጥ በላይቤሪያ፣ በሱማሊያ፣ በማሊ፣ በዲሞክራቲክ ኮንጎ፣ በሁለቱም ሱዳኖች፣ በሌሎች በርካታ አገሮች ወንድማማቾችና እህትማማቾች በዘር ጥላቻ እርስ በርስ ሲጨራረሱ እየታዘብን ነው። በዛሬዎቹም እልቂቶች የአለም አቀፉ ማኅበረሰብ በከፋ ሁኔታ ማድረግ የሚገባውን ባለማድረግ እና ማድረግ የማይገባውን በማድረግ አሉታዊ አስተዋጾውን እያበረከተ ነው። ለዚህም ለሁለት የተከፈለችው ሱዳን፣ የተበታተነችው ሱማሊያ፣ የተንኮታኮተችው ኢራቅ፣ ሥርአት አልበኝነት የነገሰባትን ሊቢያና በጦርነት እየታመሰች ያለችውን ሶሪያን ጨምሮ ሌሎች አገሮች የሚገኙበትን ሁኔታ ማየት ይቻላል።

እነዚህ አገሮች ዛሬ ለሚገኙበት ሁኔታ በውስጣቸው ካለው የመልካም አስተዳደር፣ የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መጥፋት እና የሰብአዊ መብቶች መጓደል ባሻገር አይን ያወጣው የምዕራቡ አለም ቅጥ ያጣ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ጥቅም ፍለጋ እንደ ዋና ምክንያት ሊጠቀስ ይችላል። አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞችም ይህን ሁኔታ የዳግም ቅኝ ግዛት ፓሊሲ ውጤት እንደሆነ ይገልጻሉ። እነኚህ የቅርብ ጊዜ ክስተቶች እንደሚያሳዩን ከሆነ ለአንድ ኃያል አገር የነዳጅ ዘይትና ሌሎች ኢኮኖሚያዊና ጂ-ኦ ፖለቲካዊ ጥቅሞች ሲባል አንድ ሌላ ድሃ ሃገር ከነ ሕዝቡ ሊወድም፣ ሊጠፋና እና ሊፈረካክስ እንደሚችል ነው። እጅግ የሚያስፈራው ደግሞ ከእንደነዚህ ኃይሎች የሚያስጥልና መከታ ሊሆን የሚችል ወይም ከተበደሉም በኋላ ፍትህ የሚገኝበት እና ኃያሎቹ አጥፊዎች የሚጠየቁበት አለም አቀፍና ገለልተኛ የሆነ የፍትህ መድረክ መታጣቱ ነው።

እጅግ ሰፊ እና ውስብስብ የሆነውን የአለም አቀፍ ፖለቲካ ባህሪይን ከጎሣ ግጭት ጋር በማያያዝ በትንሹም ቢሆን ከሩዋንዳው እልቂት በመነሳት ለማሳየት የፈለኩት አንድ አገር ወደ እንደዚህ አይነቱ የእልቂት ደረጃ አያምራ እንጂ መንገዱን ከተያያዘው በኋላ ግን ቀጣዩ ጉዞ ጭልጥ ያለ ድጥና ቁልቁለት መሆኑን ዛሬ በጎሣ ፖለቲካና በጎሣ ግጭት ላይ በሚቧልቱ የኢትዮጵያን ፖለቲከኞች ለማሳሰብ ነው።

በቸር እንሰንብት!

ከያሬድ ኃይለማርያም
ብራስልስ፣ ቤልጂየም

http://humanrightsinethiopia.wordpress.com/



                     




No comments:

Post a Comment