ለርዕሰ አድባራት ለንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አባላት፤ እንዲሁም በUK እና በመላው ዓለም ለምትገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተወሕዶ ሃይማኖት ተከታዮች በሙሉ። በመጀመሪያ በቸሩ ፈጣሪአችን ሥም የከበረ ሰላምታችን ይድረሳችሁ።
በስደት ሀገር ከተመሠረተች 40 ዓመታትን ያስቆጠረቸው ርዕሰ አድባራት ለንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ
ክርስቲያን ለአያሌ ዓመታት የምእመኗ ሰላምና አንድነት ተጠብቆ በመቆየት ለከፍተኛ የዕድገት ደረጃ ከደረሰች በኋላ እነሆ ባለፉት
ሁለት ዓመታት ግን ሰላሟ ተናግቶ የቤተ ክርስቲያኗ በጎ ገጽታና መልካም ምሳሌነቷ ይልቅ በስሟ የሚፈጸመው ክፉውና አሳዛኙ
ተግባር ጎልቶ እየተስተጋባ ብዙ ክርስቲያኖችን ሲያሳዝንና ግራ ሲያጋባ ቆይቷል።
ለክርስቲያኑ ሕዝብ ግራ መጋባት ዋነኛው ምክንያትም እግዚአብሔር ሳይፈራና ሳይከበር በመመለኪያ ቤቱና ለአዳም ዘር
ድህነት ሲል በተሰቀለበት መስቀሉ ስም ሃሰት እውነት መስሎ እየተነገረ፤ የአስተዳደር ጉዳይን ከሃይማኖት ሕግጋት ጋር አደባልቆ
አግዝፎና አጣሞ በማቅረብ ሕዝበ ክርስቲያኑ ተወናብዶ ወዳጅና ጠላቱንም ሆነ ክፉና ደጉን መለየት ተስኖት የሰዎች ድብቅ ዓላማ
መሣሪያ አድርጎ ለማስቀረት የሚደረገው ያላሰለሰ ጥረት ነው።
በርዕሰ አድባራት ለንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተፈጠረው ችግር መንስኤ ሃስትና
ተንኮል ካልተቀላቀሉበት እውነታው አጭርና ግልጽ ነው።
በእንግሊዝ ሀገር ስደት ላይ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተወሕዶ ሃይማኖት ተከታይ ኢትዮጵያኖች ሰላም፣ ፍቅርና
አንድነትን ፈጥረው፤ የሚተዳደሩበትና የሚመሩበት ወጥ የመተዳደሪያ ሕግ ቀርፀው ቤተ ክርስቲያኗን ላለፉት 40 ዓመታት ሃብትና
ጉልበታቸውን በመለገስ በእግዚአብሔር ተራዳዒነት በተከታዮች ብዛትም ሆነ በሃብትና ንብረት ተደራጅታ በባዕድ ሃገር ለብዙ ትውልድ
የሚተላለፍ ቅርስ ባለቤት ሆና እንድትቆይ አደረጉ። የቤተ ክርስቲያኗ በሃብት መደርጀትም ሆነ በአገልግሎት መስፋት እያደገ
መምጣት አንጻር ሲሰራበት የነበረው የውስጥ መተዳደሪያ ደንብና ትረስት ዲድ መሟላት የሚገባቸውን አንቀጾች ስለማያካትት መሻሻሉ
ስለታመነበት የደንብ ማሻሻያ ኮሚቴ በአባላት ተመርጦ በመሰየም ማሻሻያውን አርቅቆ እንዲያቀርብ መደረጉ የሚታወስ ነው።
የቀረበው ማሻሻያ ረቂቅም ለሕዝብ ውይይት ቀርቦ እንደ አስፈላጊነቱ መሻሻልና መስተካከል ተደርጎበት እንዲፀድቅ
ተወስኖ ውይይቱ ተጀምሮ ሳለ ሕዝብ መርጦ የሾማቸው አስተዳዳሪ አባ ግርማ ከበደና በሰበካ አስተዳደር ጉባኤ አባልነት ሕዝብ
መርጦ ከሰየማቸው ውስጥ በተለይ ሦስት ካህናት ከአባ ግርማ ከበደ ጋር በመሆን በቀጥታና በተዘዋዋሪ ሕዝቡ በማሻሻያ ደንቡ ላይ
ውይይት እንዳያካሂድ መብቱን ከመገደብ አልፈው ሙሉ በሙሉ ነፈጉት።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተወሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ መተዳደሪያ ደንብ በሆነው በቃለ ዓዋዲውና ቤተ
ክርስቲያኗ በእንግሊዝ ሀገር በተመዘገበችበት የቻሪቲ ሕግም (ትረስት ዲድ) ሆነ በውስጥ መተዳደሪያ ደንቡ ላይ የተደነገገውን
የአባላት መብት የጣሱት እነዚህ ካህናት ይህ የአባላትን መብት መጣስ ሕገ ወጥ ተግባር ይሸፈንላቸው ዘንድ እውነታውን ወደጎን
በመጣል ጉዳዩን የሃይማኖት ሕግ መጣስ አድርገው የሃሰት መረጃ በማቅረብ በሕዝቡ መካከል መከፋፈልና ጥላቻ እንዲስፋፋ አደረጉ።
ምእመናኑን ወክለው የተመረጡ 4 ምእመናን የሰበካ አስተዳደር ጉባኤ አባላት በገዛ ፍቃዳቸው ከሥልጣናቸው በመልቀቅ
ስራ ሲያቆሙ አስተዳዳሪውን ጨምሮ የቀሩት፤ ሦስቱ ካህናት 1 የሰንበት ት/ ቤት ወጣቶች ተወካይ ጋር 4 በመሆን የአገልግሎት
ዘመናቸው እንዳለቀና ከዛም በላይ ደግሞ ኮረም የማይሞሉ መሆናቸው በግልጽ እየታወቀ ፍጹም አንባ ገነናዊ ባህሪን በመላበስ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ የተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታይቶም ተሰምቶም በማያውቅ ሁኔታ የቤተ ክርስቲያኑ አባላት የሚያነሱትን የመብት
ጥያቄ ያስተባብራሉ ብለው ያመኑባቸውን ከ16 በላይ ምእመናንንና ዲያቆን የቤተ ክርስቲያን አባልነታቸውን በመሰረዝ ቤተ
ክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ እንዳይደርሱ በደብዳቤ አገዱ።
ይህ ክርስቲያናዊ ያልሆነ አንባገነናዊ ተግባራቸው ህዝበ ክርስቲያኑን በከፍተኛ ደረጃ በማስቆጣቱ በቤተ ክርስቲያን
ውስጥ ከፍተኛ ረብሻ ተነስቶ ቤተ ርክስቲያኗ አገልግሎቷን አቋርጣ ልትዘጋ ቻለች።
ቤተ ክርስቲያኗ ተዘግታ የቤተ ክርስቲያኗ አባላት ውጭ በተበተኑበትም ወቅት እነዚህ ሕዝብ መርጦ የሾማቸውና
የወከላቸው መሆኑን በመርሳት አንባ ገነንነት የተጠናወታቸው የቤተ ክርስቲያኗ አስተዳዳሪና 3 የሰበካው አስተዳደር ጉባኤ አባላት
የቤተ ክርስቲያኗ አባላት ሳይፈቅዱና ሳያውቁ ቤተ ክርስቲያኗ አባል ሆና ለማታውቅበት ካሁን ጀምሮ በሀገረ ስብከት ስር ሆናለች
በማለት ይህንኑ ውል በመፈራረም በአዋጅ አስነገሩ።
በዚህ ሕገ ወጥና ክርስቲያናዊ ያልሆነ እርምጃቸው የቤተ ክርስቲያኗን አባላት ለዓመታት ከቆረቡበት፤ ወግ ማዕረግ
ካዩበትና ለዓመታት ከአገለገሉበትና ከተገለገሉበት ቤተ ክርስቲያናቸው ለማባረር በመሞከር ቤተ ክርስቲያኗን ከነሃብትና ንብረቷ
በቁጥጥራቸው ሥር ያዋሉ ስለመሰላቸው የቻሪቲ ኮሚሽን ከተቀሩት የቤተክርስቲያን አባላት ጋር በመነጋገር፤ በመደራደርና በመፈራረም
ፈጽሙ በማለት Action plan ነድፎ የሰጣቸውን ወደ ጎን በመጣል በራሳቸው ፍቃድ፤ ለራሳቸው ዓላማና ተግባር በሚያመቻቸው
ሁኔታ የቤተ ክርስቲያኗን አባላት ወደ ጎን በመተው የሌሎች አብያተ ክርስቲያን አባላት በመሰብሰብ ቤተ ክርስቲያንን መልሰው
በመክፈት የቤተ ክርስቲያኗ አባላት ውጪ በመቅረት፤ ብርድ፣ ዝናብና በረዶ እየተፈራረቀባቸው በገዛ ቤተ ክርስቲያናቸው የበይ
ተመልካች በመሆን እንዲጸልዩ አደረጓቸው።
በዚህም አላበቁም በግቢው ውስጥ ድንኳን እየጣሉ ጸሎት የሚያካሂዱ የቤተ ክርስቲያኗ ዋልታና ማገር የሆኑ ምእመናን
ከግቢው ውስጥ ለማባረር የተለያዩ ሙከራዎችን በማድረግ ያላሰለሰ ጥረት አደረጉ ነገር ግን አንዱም ላይሳካላቸው ችሏል። ቤተ
ክርስቲያናቸው ተነጥቆ እውጪ ለመጸለይ የተገደዱት የቤተ ክርስቲያኗ አባላት ለሕገ ወጥ ተግባርን ሕገ ወጥ ምላሽ መሥጠትን
ሳይሆን ሕገ ወጥ ድርጊትን በሕጋዊ አካሄድ ሕግ ፊት አቅርቦ ፍትሕን ማግኘት የሚለውን መርህ በመከተል፤ በታላቅ ትዕግሥት
ጽናትና ጥንካሬ በፈጣሪ ተራዳኢነት ፍትሕን ለማግኘት በጠቅላላው ለ2 ዓመታት የተቃረበ ጊዜ መራራ ትግል በማድረግ አስፈላጊውን
የሕግ አካሄድ መመሪያና ደንብ አሟልተው በማቅረብ የቤተ ክርስቲያኗ ሕጋዊ ባለቤትነት ጥያቄና የውስጥ መተዳደሪያ ደንብ ሕጋዊ
ሰነድነት ጉዳይ ፍርድ ቤት ቀርቦ ይወሰንበት ዘንድ የቻሪቲ ኮሚሽን ሙሉ ፍቃድና ይሁንታ እንዲያገኝ አስደረጉ።
በዚህ መሠረት ሰኞ 09/02/2915 የተጀመረው የፍርድ ቤት ችሎት ማክሰኞና ረቡዕ ሙሉ ቀናት ቀጥሎ ከቆየ በኋላ
ሐሙስ ታርፎ ዓርብ የመጨረሻው የዳኛው የፍርድ ውሳኔም ተበየነ።
የዳኛው የፍርድ ውሳኔ
የመጨረሻው የዳኛው የፍርድ ውሳኔም በጥቅሉ እንደሚከተለው ነው።
1.
የቤተ ክርስቲያኗ አባላት ለዓመታት ቤተ ክርስቲያኗን (ቻሪቲውን) በገንዘባቸውና በጉልበታቸው የረዱና ሲያገለግሉም ሆነ ሲገለገሉ የኖሩ ስለሆነ በቤተ ክርስቲያኗ ጉዳይ ያገባቸዋል፤
2.
የቤተ ክርስቲያኗ አባላት የቤተ ክርስቲያኗን ጉዳይ ፍርድ ቤት ለማቅረብ የሚያስችል አግባብ አላቸው፤ ይህንንም ለማድረግ ከቻሪቲ ኮሚሽንም ሙሉ ፍቃድ አግኝተዋል አስፈላጊውን ፎርማሊቲ ሁሉ አሟልተው አቅርበዋል፤
3.
የቤተ ክርስቲያኗ አባላት በመረጡት ካህን አማካኝነት የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት የማግኘት መብት አላቸው፤
4.
የቤተ ክርስቲያኗ አባላት ያለምንም ገደብና መሰናክል ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በተራ በመግባት የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እንዲያከናውኑ ፍርድ ቤቱ የፍርድ ማዘዣ (Interim relief Order) አውጥቷል፤
5.
ይህ የፍርድ ቤቱ ውሳኔም በፍርድ ቤቱ ማዘዣ ላይ በወጣው ዝርዝር ቀንና አፈጻጸም መሠረት ተፈጻሚነት ይኖረዋል፤
6.
ይህ የፍርድ ቤት ማዝዣ ተግባራዊ እንዳይሆን በሚሞክርና በሚያሰናክል ላይ ፍርድ ቤቱ ጥብቅ እርምጃ ይወስዳል የሚል ነው።
ከላይ በጥቅሉ የተሰጠው የፍርድ ቤት ብይን ከተላለፈ በኋላ ሥልጣን አንለቅም ብለው የሚንገታገቱት ካህናት ጠበቃ በፍርዱ ላይ ይግባኝ ጠይቆ ዳኛው የይግባኙን መሠረት ለዳኛው እንዲያቀርብ መመሪያ ሰጠው።
በመመሪያውም መሠረት ጠበቃው ከ1 ሰዓት በላይ ጊዜ የወሰደ የተንዛዛ የይግባኝ ጥያቄዎቼ መሠረቶች ናቸው ያላቸውን ነጥቦች አቅርበ። ዳኛውም በሚገባ ካዳመጠ በኋላ በመጨረሻ ዳኛው ይግባኙን ውድቅ (reject) እንዳደረገው በመግለጽ ፍርዱ ተጠናቋል። ከፍርዱ (Judgement) መጠናቀቅ በኋላ የፍርድ ቤቱን ማዘዣ አፈጻጸም በተመለከተ ዳኛው ለሁለቱ ጠበቆች ዝርዝር መመሪያ ሰጥቶ ችሎቱን ዘግቷል።
በዚህ የፍርድ ውሳኔ መሠረት የቤተ ክርስቲያኗ አባላት በጉዳዩ በመርታት መብታቸውን የሚያስከብር የፍርድ ቤት ትዕዛዝ (Interim relief Order) ማግኘት የቻሉ ሲሆን፤ ሌላው ወገን ግን በይግባኙ ከቀጠለበት ይግባኝ ለማለት ይፈቀድለት ዘንድ ለይግባኝ መሥሪያ ቤት (Appeal Court) ማመልከት ይኖርበታል።
ወድ የርዕሰ አድባራት ለንደን ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አባላትና መላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት እምነት ተከታዮች።
እኛ ለቤተ ክርስቲያናችን፣ ለመብታችን እና ለእውነት የቆምን የቤተ ክርስቲያኗ አባላት ችግራችንና ክሳችን የቤተ ክርስቲያኗ እንዲያስተዳድሩንና እንዲመሩን ራሳችን መርጠን የሰየምናቸው ጥቂት ካህናት በወያኔ አገዛዝ ሹመኞችና ካድሬዎች እየታገዙ አሥር፣ ሃያ፣ ሰላሣ ዓመትና ከዛም በላይ የኖርንባት፤ ከልጅነት እስከ ጎልማሳነትና እስከ አዛውንትነት ያገለገልንባትም ሆነ የተገለገልንባትና ሃብትና ጉልበታችንን አፍስሰን በእግዚአብሔር ተራዳኢነት ካደራጀናት ቤተ ክርስቲያናችን መብታችንን ገፈው ሊያባርሩን የሚሞክሩትን እንጂ የትኛውንም ወገን ደግፈው ከቆሙ እንደኛው ካሉት ወንድሞቻችን፣ እህቶቻችን፣ አባትና እናቶቻችን ጋር አንዳችም ችግር የለብንም ሊኖርብንም አይገባም። ከፍርዱም በሁዋላ በሚወጡ መግለጯዎች ላይ፤ ክሱ የተመሰረተው በዘር ላይ ተመርኩዞ ነው፤ አመልካቾቹም ሆነ ተከታዮቻቸው ዘረኞች ናቸው፤ የሚል የሀሰት ፕሮፖጋንዳ እየተነዛ ነው። ይህ ግን ሆን ተበሎ በክርስቲያኖች መካከል ከፍተኛ ክፍፍልን በመፍጠር ድጋፍ ለማግኘት የሚደረግ ጥረት ነው። መሰረት የሌለው ውሸት ነው። ስልጣን የጠማው ወይም መልቀቅ የማይፈልግ መሪ የሚጠቀምበት የከፋፍለህ ግዛው የአመራር/የማወናበድ ስልት ነው። ይህ ደግም ምን ያህል ጥፋት እንዳመጣና እንደሚያመጣ ታሪክ ምስክር ነውና ይህንን ትልቅ ውሸታቸውን ማጋለጥና መቃዎም የሁሉም ክርስቲያን ሃላፊነት ነው።
በዚህ መሠረትም ከአሁን በፊት በጉዳዩ አፍላነትም ሆነ ትዕግሥትን በማጣትና በግልፍተኝነት ተፈጥረው የነበሩ የግለሰቦች ጊዚያዊ መቃቃሮች ሁሉ ወደ ጎን ተትተው እመካከላችን ሆነው እኛን በመከፋፈል ሊጠቀሙብን ከሚሹት የቀበሮ ባህታውያን በስተቀር ሌሎቻችን አንድነታችንን መልሰን በመጠንከር በአንድ ጣራ ስር በመሆን እግዚአብሔርን ለማምለክና ስሙን ለማመስገን የሚከለክለን አንዳችም ነገር ሊኖር እንደማይችል ያለንን የጸና እምነት ለመግለጽ እንወዳለን። የእግዚአብሔር ተራዳዒነት ከሁላችንም ጋር ይሁን!!! አሜን!!! ርዕሰ አድባራት ለንደን ደብረ ጽዮን ቤተ ክርስቲያንን እናድን ማህበር።
የእግዚአብሔር ተራዳዒነት ከሁላችንም ጋር ይሁን!!!
አሜን!!!
ርዕሰ አድባራት ለንደን ደብረ ጽዮን ቤተ ክርስቲያንን እናድን ማህበር።
E-mail: ourchurchdebretsion@gmail.com
No comments:
Post a Comment