1ኛ / ‘’ለተወለዱበት ጎሳ ወይም መንደር የሚታገሉ’’፤
እነዚህ ሁሉም ማለት ይቻላል የወያኔ ቅኝቶች ናቸው። ወያኔ ካሰመረው መስመር አይወጡም። ምክንያቱም ለመጡብት ጎሳ ወይም መንደር ነጻነትና እኩልነት የሚታገሉ ቢሆን ኑሮ፤ የህዝቡ ኑሮው በተሻሻለና መብቱ በተከበረለት ነበር። ተቃዋሚዎች እንዲባሉ ''ደጋፊወቻችን ታሰሩብን።'' ሲሉም ይሰማሉ። አንዳንዴም ''ከሌሎች ተቃዋሚዎች ጋር ሕብረት ፈጠርን፣ የሕብረቱ መሪ 'እኔ ነኝ...እኛ ነን።" ሲሉ ይሰማና፤ ገና የተፈራረሙንበት ቀለም ሳይደርቅ ''ፈረሰ'' ይሉናል ወይም ድምጻቸው ይጠፋል። ወያኔ የተለመደውን የማጭበርበሪያ ምርጫ ሲጠራ አብረው ያጫፍራሉ። የተወሰኑ "ወንበሮች'' ከተፈቀደላቸውም ''ሸንጎ" ገብተው "ውጡ በቃችሁ" እስኪባሉ ድረስ ተውኔቱን ያዳምቃሉ። ታዲያ እነዚህ ተቃዋሚዎች በሚገርም ሁኔታ የሚመሩበትም ሆነ የሚተዳደሩበት ግልጽ የሆነ መርሀ-ግብር እንኳን የላቸውም። አመራር አከላት ያላቸው አይመስልም። ከሀያ ዓመት በፊት የምናያቸው ‘’ሊቀመናብርት’’ አሁንም እነ’ሱ ናቸው። ብዙ ማለት ይቻላል። አላማቸው ግን ግልጽ ነው፤ በወገን ስም እየነገዱ ከወያኔ የምትተርፈውን ፍርፋሪና የሰምቶ አዳሪነት ስልጣን ይዞ እንድ ካሮት ወደታች እያደጉ ማገልገል ነው። እያገለገሉም እስካሁን ድረስ ዘልቀዋል።
2ኛ/ "ለዲሞክራሲ፣ ለሀገሪቱና ለህዝቧ ልዕልና የሚታገሉ"፤
"ለዲሞክራሲ፣ ለሀገሪቱና ለህዝቧ ልዕልና የሚታገሉ"፤ በ'ርግጥም በተቃዋሚነት ተደራጅተው መረሀ-ግብር ነድፈው በተውሰነ ደረጃም ቢሆን ታግለዋል። ይሁን እንጂ ከያዘቱ አላማና ካላቸው የህዝብ ድጋፍ አንጻር ሲታይ፤ ወያኔን አስወግደው ኢትዮጵያን የዲሞክራሲ ሀገርና ኢትዮጵያን የኢትዮጵያዊያን ማድረግ በቻሉ ነበር። ነገር ግን ከሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ባህሪና ምግባር ውጭ የሆነውን ወያኔን ለማወቅ ባለመቻላቸው፤ ከአምባገነኖች ምንጋጋ ልንላቀቅ ቀርቶ፤ በባሰ ደረጃ ገዥዎቻቸን ሀገሪቱ ራሷንና ውድ ልጆቿ ለዓለም ዲታዎችና ለታሪካዊ ጥላቶቻችን በጨረታ ቸበቸቡን። አሁንም ችብቸባው ተጠናክሮ ቀጥሏል።
ሁሌም የሚነሰው 1997ቱ ነው። ይሁን እንጅ በምጨረሻዋ ሰዓት የትግሉ መሪዎች ''ሳይቀናጁ የተቀናጁ'' ስለነበሩና ወያኔ እነሱ ከሚያውቁት በበለጠ እነሱን ያውቃቸው ነበርና፤ የብዙ ወገኖቻችን ህይወት ቀጥፎ፣ ብዙዎችንም ለስድትና ለእስር ዳርጎ፣ ለገዥዎቻችን የልብ ልብ ሰ'ቶ ተጠናቀቀ። ''የሰላም ትግል'' ብዙዎቹን ተስፋ አስቆረጣቸው።
በአሁኑ ወቅት ያሉት የሀገር ቤት ተቃዋሚዎች ''መሰብሰቢያ አዳራሽ ተከለከልን፣ ደጋፊዎቻችን ታሰሩብን፣ ወዘተ'' ከሚል የተለመደ ወሬ-መሰል ተቃውሞ በቀር፤ ሰላማዊ ትግል የሚጠይቀውን ሁሉ መሰዋአትነት ለመክፈል ተዘጋጅተው፤ ህዝብን አደራጅተውና መሪ ሆነው በተግባር ለውጥ ሊያመጣ የሚችል እንቅስቃሴ ሲያደርጉ አይታዩም።
3ኛ/ ‘’የባህር ማዶ የወያኔ ተቃውሚዎች’’፤
የባህር ማዶ የወያኔ ተቃዋሚዎች ከኢትዮጵያ ለመገንጠል ከሚታገሉት ጀምሮ፣ የኤርትራን መገንጠል እስክ የማይቀበሉትና በገዥው ላይ ጦርነት ያወጁ ሁሉ ያሉበት ሲሆን፤ ከተመሰረቱ የኔን ትወልድ ዕድሜ የሚያስከነዱ ስምና ዝና ለማትረፍ የተሰለፉትን ሁሉ ይጨምራል።
አንዲያውም የኢንተርኔት ድህረ-ገጽን ለሚከታተል በኢትዮጵያ ዲሞክራሲ የማምጣቱም ሆነ ሀገሪቱን ለመገነጣጠል የሚደረገው ትግል በተለይም በዋሽንግተን፣ በለንደንና በአምስተርዳም ከተሞች ላይ ያለ ይመስላል።
ሁሉም ባህር ማዶ ያሉ የወያኔ ተቃዋሚዎች የሚናገሩተና የሚጽፉት፤ ግን በተግባር የማያሳዩት ነገር ቢኖር ''ትግሉ መካሄድ ያለበት በሀገር ውስጥ ነው። የትግሉ ባለቤት ህዝብ ነው።'' የሚል ነው። ነገረ ግን ህዘብ ካላደራጁትና ለሚጠይቀው መሰዋአትነት መሪና አር’ያ የሚሆነው ድርጅት ወይም አመራር ሳይኖር እንዴት አድርጎ ነው እንደ ወያኔ ያለ ጭራቃዊ ገዥ ማስወገድ የሚችለው? (እንዲያውም የኢትዮጵያ ህዝብ በተለያዩ ግዚያት ሆ! በሎ በመውጣት የወያኔ ጥይት በልቶታል። ግን መሪና አደራጅ ስላልነበረውና ስላ’ጣ ሳይሳካለት ቀርቷል። የ1997ቱ ማስታወሱ በቂ ነው።) ተብለወ ሲጠየቁ ደግሞ ማጣፊያው ያጥራቸዋል ወይም ‘’ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ’’ አይነት መልስ ይሰጣሉ። ይህ ብቻ አይደለም፤ ወታደር ሳይኖራቸው ጦርነት ያውጃሉ። እነሱ የፈሩትን መሰዋአትነት የሀገር ቤቱ ህዝብ እንዲያደርግላቸው ጥሪ ያስትላልፋሉ። ለ'ነሱ አስፈላጊ መስሎ ከታያቸው ደግሞ ባህር ማዶ ላይ ሆነው የሽግግር መንግስት ይመሰርታሉ ወይም ወያኔን አብረን እንመስርት ይሉታል። በዚህም አያቆሙም፤… በዓመት አስከ 4 ቢሊወን ዶላር ድራስ እየረጠቡት የሚያገለግላቸውን ወያኔን '’ለመጣል እየታገልን ነውና እርዱነ፣ የፓለቲካም እውቅና ስጡን፣ ወዘተ….።'' እያሉ በየቤተ-መንግስታቸው በር ሻማ እያበሩ ይማጽናሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ ''የኢትዮጵያ ድንበር ቀይ ባህር ነው” እያሉ፤ እጅግ በሚያሳፍርና የኢትዮጵያዊያንን ክብርና ስብዕና በማዋረድ አቶ ኢሳያስ አፈወርቂን ''ወያኔን ይውጉልን፣ ይረዱን፣ ወታደሮች አሰልጥኑልን፣ ወዘተ….።'' በማለት ደጅ ይጠናሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ ''ሀገር ቤት መግባት አንችልም።" እያሉ ''የሰላማዊ ትግል'' አዋጅ ያውጃሉ።
"ለምን ትግላችሁ ውጤት አያመጣም? ወያኔዎች እኮ በኢትዮጵያ ህዝብ(ለሆዱ ካደረው ውጭ)የተጠሉና ድጋፍ የሌላቸው ናቸወ።" ተብለው ሲጠየቁ ''እየሰራን ነው፣ ገብታችሁ ሞክሩት...ትግላችን የምትተቹ ወያኔ ናችሁ…. ወዘተ" ከማለት ውጭ በተቆርቋሪነት አስተያየት ለሚሰጥ እንኳን በዙዎቹ በጎ አመለካከት የላቸውም። በ’ጠቃላይ ”ግራ ገብቷቸው ግራ የሚያጋቡ'' ናቸው ብል ማጋነን አይሆንም። ይህን የምለው እድሜ ልክ የወያኔ መቀለጃ ከመሆን፤ ራስን መርምሮ እውነትኛውን የትግል መስመር መያዙ አማራጭ የሌለው አማራጭ በመሆኑ ነው።
እውነታው የባህር ማዶው ትግል የሀገር ቤቱን ትግል ያግዛል። እንድ ኢሳት ያሉ መገናኛ አውትሮችና የኢንተረኔት መገናኛዎች ህዝቡ የበልጠ ግንዛቤ እንዲኖረውና የተለያዩ ሀሳቦች እንድንለዋወጥ ማድረግ ይቻላሉ፤ እያደረጉም ነው። ውለታቸውን ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝብ አይረሳም። ሀገር ቤት ያሉትን እውነተኛ የዲሞክራሲ ታጋዮችንና የእስረኛ ቤተሰቦችን በገንዘብም ሆነ በሞራል መርዳትና ማበረታታት ይቻላል። ከዚህ ውጭ ግን ሀገር ቤት ገብቶ የሚጠይቀውን መሰዋአትነት ከምክፍልና ከወያኔ ጋር ፊት ለፊት ከመጋፈጥ ውጭ የሚደረግ የይሰሙላ ትግል የገዥዋቻችንን እድሜ ሲያራዘም እንጅ ሲያሳጥር አላየንም።
4ኛ/ ‘’የወያኔ የክፉ ቀን ታጋይ ድርጅቶች (ፓርቲዎች)’’፤
የወያኔ የክፉ ቀን ታጋይ ድርጅቶች (ፓርቲዎች)፣ በሀገርም ውስጥ ሆነ በባህር ማዶ ተጠናክረው በጽናት የሚሰሩ ናቸው። ብዙዎቹ የድሮ የወያኔ አባል ሲሆኑ፤ በድርጅቱ ውስጥ ከፍተኛ ስልጣን የነበራቸው፣ አድራጊና ፈጣሪም ነበሩ። ከወያኔ ''የተለያዮት'' አንዳዶቹ ከስልጣን ፍትጊያና በሀብት ዘረፋው የሚገባንን ያህል አላግኘንም ብለው ሲሆን አንዳንዶቹ ግን ሆን ተብሎ የተባረሩ ናቸው። ለማስመስል እስር ቤትም ይወረወሩና ከተፈቱ በኋላ አዲስ ግዳጅ ይሰጣቸዋል። ይሁን እንጅ ሁሉም አንድ "ቃል ኪዳን" አላቸው፤ ምንም ምን ቢሆኑ ወያኔን የማገልገል አላማ። እነዚህ ሰዎች በተለያዩ መንግዶች የተደራጁና የሚያደራጁ ሲሆኑ፤ አስፈላጊ ከሆነ ጭምብላቸውን አውልቀው (97 ላይ የተከሰትውን እናስታውስ።) በቀጥታ አለያ ግን በተዘዋዋሪ ለወያኔ የሚታገሉ ናቸው። አላማቸውም፤ …..
ሀ/ የወያኔ ተቃዋሚ በመምሰል ህዝብን፣ ለዲሞክራሲና ለአንድነት የሚታገሉትን ማሳሳትና ማዘናጋት።
ለ/ የራሳቸውን የተቃዋሚ ድርጅት ወይም ፓርቲ በማቋቋምና ከሌሎች ተቃዋሚዎች ጋር ህብረት/ አንድነት /መድረክ/ግ’ባር በመፍጠር፣ በሀገሪቱ ውስጥ ጠንካራና ወያኔን የሚያሰጋ ተቃዋሚ አንዳይኖር ማድረግ፤ ካለም እንዲመታ ማድረግ።
ሐ/ በተላያዩ የተቃዋሚ ድርጅቶችና ፓርቲዎች ውስጥ ተሰግስገው ለወያኔ መረጃዎችን ማቀበል።
መ/ ዋናው ግብ ደግሞ ምናልባት ወያኔ በህዝብ አመፅም ሆነ በተለየ ምክንያት ከስልጣን የሚባረርበት ሁኔታ ቢፈጠር፤ ''እኛም ተቃዋሚ ነበርን!" በማለት ስልጣን ኮርቻ ላይ ለመፈናጠጥና የወያኔ ሰዎችንና ጥቅማቸውን በማስከበር በሌላ ዙር ስርዓቱ እንዲቀጥል ማድርግ ነው።
በተለይ በአሁኑ ወቅት ትላንት "ትግራይና ኤርትራ የኢትዮጵያ ቅኝ ግዛቶች ናቸው፤ ኢትዮጵያዊ አይደለንም።" በማለት የመቶ ሺዎቸን ወገኖቻችን ህይወት መስዋት አድርገው፤ የባህር-በር አልባ እንዳላደረጉን ሁሉ፣ ''ብንፈልግ ጦርነት መፍጠር እንችላለን''፣ወዘተ... በማለት፤ ታሪክና ትውልድ ይቅር የማይለው በደል አንዳልፈጽሙ ሁሉ፤ ዛሬ ደገሞ ''የ'ኛ ነጻ አውጭ'' ሆነው የመሪነቱን ቦታ ከተቃዋሚ ነን ባዮች ተረክበው ተቆጣጥረውታል። በስውርም ሆነ በአደባባይ ወያኔዎች የሌሉበት የወያኔ ተቃዋሚ ማግኘት ይከብዳል። ግን እነሱማ ምን ያድርጉ? ዘፋኙ እንዴት ነበር ያቀነቀነው?......
''.....ወሰዱት አሉ የሁመራን መሬት፣
የመተማን መሬት.. ያውም የ'ኛን እጣ፣
እነሱ ምን ያ'ርጉ ከ'ኛ ሰው ሲታጣ።''
No comments:
Post a Comment