Sunday, April 28, 2013

ግንባር፣ ትስስረ-ትውልድ እና የኢትዮጵያ ስነ-አስተዳደር


ንጥር ዘገባ

የሚሠራ ምንም አያወራ

በሀገራችን ውስጥ ከግማሽ ምዕት ዓመት በላይ የስነ-አስተዳደር ትግል በተለያየ መልክና ቦታ ሲካሄድ ቆይቷል። በዚህ ወቅት በተደረጉትና አሁንም እየተደረጉ ባሉት ትግሎች፤ የተለያዩ ድርጅቶች ከመሰሎቻቸው ጋር ጊዜያዊም ሆነ ረጅም ዕድሜ ያለው ትብብር መሥርተዋል። በሌላ በኩል ደግሞ፤ ዘለቄታ ያለው ግንባር መሥረቶ አብሮ የመሥራት፤ አልፎም መዋኀድ ጎልተው አይታዩም። ይልቁንም አንድ የነበረ* ድርጅት ሲከፋፈል ማየቱ የተለመደ ሆኗል። ባሁኑ ሰዓት የሀገራችን ፫ የስነ-አስተዳደር ምስቅልቅል መጨበጫ አጥቶ፤ የትስስረ-ትውልዱ* አምባገነን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ፬ ያለ ገደብ ዕብሪቱን የለቀቀበት ሀቅ ተከስቷል። ግፉ እንዲህ በበዛበት ሀገርና አብዛኛው ሕዝብ የማይወደው መንግሥት በሥልጣን ላይ በተቆናጠጠበት ሁኔታ፤ እንዴት ነው ሕዝባዊ ትግሉ የተጓተተው? ወገናችን እንዲህ መጎሳቀሉ መቼ ነው የሚያቆመው? ሀገራችን መቼ ነው ነፃ የምትወጣው? ኢትዮጵያዊያን በያለንበት ቦታ ከማዘን ወጥተን፤ መቼ ነው በአንድነት ወደ ትግሉ የምንቀላቀለው? እስከዛሬ በትግሉ ዙሪያ ምን ተደርጎ ምን ተገኘ? ከዚህ ተነስተን ወደፊት መሄድ የሚቻለው ምን በማድረግ ነው? እና ምን ይደረግ? እናስ እንዴት ያለ የትግል አንድነት መመሥረት እንችላለን? እኒህንና እኒህን የመሳሰሉ ጥያቄዎች በያለንበት ማንሰላሰላችን አልቀረም። በሀገራችን ካለው የስነ-አስተዳደር ሀቅ ትምህርት ወስደን ወደፊት መሄድ መቻል አለብን። የእስከዛሬውን የትግል ትብብር ዘገባ መመርመሪያውና ለወደፊቱ በትክክለኛ መንገድ መሰባሰቢያው ሰዓቱ አሁን ነው። የመንግሥት ለውጥ ብቻ ሳይሆን የሥርዓት ለውጥ መደረግ እንዳለበት መረዳት አለብን። በዚህ መንፈስ፤ እስከዛሬ የተደረጉትን የትግል ትብብሮች ለማየት ይረዳን ዘንድ፤ ግንባር፣ ትስስረ-ትውልድ እና የኢትዮጵያ ስነ-አስተዳደር  በሚል ርዕስ፤ የግለሰብ ኢትዮጵያዊ የስነ-አስተዳደር ተሳትፎን ድርሻ፣ የትስስረ-ትውልድ ሚናን፣ እስከዛሬ የተመሠረቱትንና ያልተመሠረቱትን ግንባሮች በመመርመር፤ የተፈፀሙ ስህተቶችን ዓይተን ትምህርት በመውሰድ፤ ወደፊት ምን ማድረግ እንዳለብን ተጠቁሟል። በተጨማሪም መመሥረት ያለበትን ሀገር አቀፍ የትግል ድርጅት ያመላክታል።

መግቢያ

በሀገራችን ያለውን የስነ-አስተዳደር ሀቅ፤ እያንዳንዳችን በዝርዝር እናውቀዋለን። በድፍረት ደግሞ፤ እያንዳንዳችንም መደረግ ስላለበት ተግባር የተወሰን የመፍትሔ ሃሳብ አለን ማለት ይቻላል። ታዲያ ከዚህ ተነስተን፤ በአንድነት የጠላትንና የወዳጅን ሠፈር ለይተን ማስቀመጥ አለብን። በወዳጅ ሠፈር ዙሪያ፤ ሌሎች ማድረግ ያለባቸውን ብቻ ሳይሆን፤ እያንዳንዳችን ማድረግ ያለብንን በግልፅ መገንዘብ አለብን። በኢትዮጵያ ባለው እውነታ፤ በትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባርና በኢትዮጵያ ሕዝብ መካከል ያለው ትግል፤ ከመሠረታዊ ትክክለኛ ግቡ አንፃር፤ የተመሰቃቀለ፣ ረጅምና ውጣ ውረድ የበዛበት ነው። እዚህ ላይ መተኮር ያለበት፤ መሠረታዊ ትክክለኛ ግብ የሚለው ነጥብ ነው። ደርግ በትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር እንደተተካ ሁሉ፤ ሌላ የበለጠ አረመኔ ቡድን ሊከተል የሚችልበት መንገድ አለ። ይኼን ደግሞ ካሁኑ ተገንዝበን መንገዱን መዝጋት አለብን። በሌላ በኩል ደግሞ፤ ከምንፈልገው መሠረታዊ ትክክለኛ ግብ ለመድረስ፤ ሁላችን አለን ማለት፤ መቆጠር አለብን። ለዚህ ትክክለኛ ግብ፤ ትክክለኛ ራዕይ ሊኖረን ይገባል። ለዚህ ትክክለኛ ግብ፤ ተልዕኳችን በግልፅ መሥፈር አለበት። የእኛም ወገን ወዳድነት፣ ሀገር አፍቃሪነትና ለትግል ቆርጠን ተሠላፊነታችን በዚህ ይለካል።

አሁን በሀገራችን በኢትዮጵያ እየተፈፀመ ያለው የትስስረ-ትውልድ ማፅዳትና ማጥፋት ተግባር፤ የስነ-አስተዳደር ትግሉን ግለት አጋግሞታል። የትስስረ-ትውልዱ አምባገነን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት የደረሰበትን የምንነቱ ትክክለኛ መግለጫ ምዕራፍ፤ በግልፅ አስቀምጦልናል። ከዚህ አሁን ከደረሰበት ምዕራፍ፤ አምባገነኑ ቡድን ወደ ኋላ አይመለስም። ተጨማሪ የትስስረ-ትውልድ ማፅዳቶችና ማጥፋቶች መከተላቸው የጊዜ ጉዳይ ነው። የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ከተመሠረተ ጀምሮ በአማራው ወገናችን ላይ እያደረገ ያለውን ዘመቻ፤ አሁን በአንድነት ሁላችንም የተረዳነውና የኛ ብለን የተነሳንበት አንገብጋቢ ጉዳይ ሆኗል። በዕርግጥ ሌሎች ክብደት ያላቸው ሀገር አቀፍ ጉዳዮች አሉ። ተከታታይነቱንና አረመኔነቱን በተመለከተ፤ ይህ የትስስረ-ትውልድ ማፅዳትና ማጥፋት ክብደት ያለው በመሆኑ፤ የሁላችንን አቅል በአንድነት መሳቡ አንድ ብሩህ ገፅታው ነው።

ከአንድ ዓመት በላይ የሆነው የእስልምና ተከታይ ወገኖቻችን የሚያደርጉት የመብት ጥያቄ በራችንን ካንኳኳ ጊዜ ፈጅቷል። ገዳማት የታሪክና የምዕመናን መዘውተሪያ መሆናቸው ቀርቶ፤ በአምባገነኑ ቡድን መሪነት የመዋዕለ ነዋያቸው* መጨፈሪያ ሆነዋል። ሀገሪቱ እየተቆራረሰች፤ ድንበሯ ለጎረቤት ሀገር፣ ለሙ መሬት ከባለቤቱ እየተነጠቀ፤ ለውጪና ለትስስረ- ትውልዱ አምባገነን መንግሥት ከፍተኛ አባላት በርካሽ እየተቸረቸረ ነው። ያልተመጣጠነ የልማት ዕድገቶች በሀገራችን  የተለያዩ ክፍሎች ተከስቷል። ይህ ደግሞ፤ በሀብት ክምችት፣ በትምህርት ዕድገት፣ በሥራ ዕድል፣ በመንግሥት መዋቅር የሥልጣን ምደባ፣ በአካባቢ ልማትና በነዋሪዎች የሞራል አቋም ላይ ተከናውኗል። ይህ የሀገራችን የስነ-አስተዳደር ሀቅ ነው። ከዚህ በመነሣት፤ መሠረታዊ የሆኑ ጥያቄዎች በሁላችንም አእምሮ ሽከርከር አለባቸው።

በአንፃሩም ይኼ የትስስረ-ትውልድ አምባገነን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የማያደርሰው በደል እንደሌለ ተገንዝበን፤ አንዱን በማንሳት ሌላውን በመጣል ማውገዝና መጮሁን ክብደት አንሥጠው። ማክበድ ያለብን በኛ በታጋዮች በኩል፤ ምን ማድረግ አለብን? የሚለውን ነው። ለዚህ ደግሞ መጀመሪያ የሚጠቅመው፤ ታሪካችንን መመርመር፣ ለትግል ያለንን ቆራጥነት መመዘን ነው። የትስስረ-ትውልዱን አምባገነን የትግሬዎች ነፃ አውጪ መንግሥት መሠረታዊ የስነ-አስተዳደር ፍልስፍና፣ የአስተዳደሩን መመሪያ፣ ይኼን ቡድን ለማስወገድ መነደፍ ያለበት ራዕይና መሠረታዊ የስነ-አስተዳደር መፍትሔ ምንድን ነው? ለሚለው ይረዳን ዘንድ፤ ከእስከዛሬው የትግል ተመክሮቻችን በመነሳት፤ የተደረጉ ትብብሮችን መርምረናል። ምንም እንኳ የትስስረ-ትውልዱ አምባገኑ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ኃይለኛና አይበገሬ መስሎ ለጊዜው ታይም፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ አቸናፊ ሆኖ መውጣቱን መጠራጠር የለብንም። ይኼን ገሀድ ለማድረግ ደግሞ፤ ይኼን ቡድን በደንብ ማጥናትና የሚጠብቀን ምን እንደሆነ መረዳትና የራሳችንን የእስከዛሬ ታሪክ፣ ጥንካሬና ድክመት መመርመር ነው።

ግለሰብ ኢትዮጵያዊ፣ ዴሞክራሲያዊ መብቶችና የትስስረ-ትውልድ ስነ-አስተዳደር፤

ግለሰብ፣ ዴሞክራሲያዊ መብት፣ ትስስረ-ትውልድና ስነ-አስተዳደር የሚባሉትን ፅንሰ ሃሳቦች በተናጠል ማንኛችንም በድንብ ተንትነን ስለምናውቀው፤ ዝርዝር ሃተታውን እዚህ ማካተቱ አስፈላጊ አይደለም ብለን መሠረታዊ የማያጠያይቁ ትርጉሞቻቸውን ብቻ ጠቅሰናል። ነገር ግን፤ እነዚህ ፅንሰ ሃሳቦች ባንድነት ሲተሣሰሩ፤ የግንዛቤያቸው ጥልቀት ይመጥቃል። እናም የተቆላለፉበትን ግንኙነት በመተንተን፤ ትስስራቸው ለትርጉማቸው የለገሰውን ጭማሪ አንደምታ እናያለን።

ግለሰብ ኢትዮጵያዊ ስንል፤
ማንም ግለሰብ፤ በትውልድ ማለትም በእናትና በአባቱ ኢትዮጵያዊ የሆነ፤
ወይንም በሕገ-መንግሥቱ በተደነገገ አንቀፅ መሠረት ኢትዮጵያዊነትን ያገኘ ማለት ነው። ይህ ግለሰብ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት አንዱ ትስስረ-ትውልድ ወይንም ከአንድ በላይ የትስስረ-ትውልድ ሊኖረው ይችላል። በተጨማሪም በኢትዮጵያ ከሚነገሩት ቋንቋዎች አንደኛውንም ወይንም ካንድ በላይ የሚናገር ወይንም አንዳቸውንም የማይናገር ሊሆን ይችላል። በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙት ሃይማኖቶች አንደኛውን የተቀበለ ወይንም ሃይማኖት አያስፈልገኝም ያለ ሊሆን ይችላል። ወንድ ወይንም ሴት፣ ረጅም ወይንም አጭር፣ ጥቁር ወይንም የቀይ ዳማ ሊሆን ይችላል። ሌሎች ሰብዓዊ መግለጫዎችም አንዱን ወይንም ሌላውን በመያዝ ሊገለፅ ይችላል። እናም ኢትዮጵያዊ የተባለ ግለሰብ፤ የግድ ከአንድ የተወሰነ ትስስረ-ትውልድ መሆን፣ ወይንም አንድ የተወሰነ ቋንቋ መናገር፣ ወይንም አንድ የተለየ ሃይማኖት መከተል፣ ወይንም አንድ መልክ መያዝ፣ ወይንም አንድ የተወሰነ ቁመት ያለው መሆን የለበትም።


ዴሞክራሲያዊ መብቶች ስንል፤
አንድ ግለሰብ፤ በኢትዮጵያ ሲኖር፤ በኅብረተሰቡ ውስጥ በሚኖረው ተሳትፎ፤ የግለሰቡን ነፃነት ከኅብረተሰቡ ሕልውና አንፃር ለይቶ የሚያስቀምጥ ደንብ ነው። ግለሰቡ ከሌሎች የኅብረተሰቡ አባላት ጋር ለሚያደርገው ግንኙነት፤ በሕግ የተደነገገለት መብትና መከተል ያለበት ግዴታ የግለሰቡ ዴሞክራሲያዊ መብቶች ይባላሉ። እኒህም፤ ሃሳቡን ለመግለፅ የሚኖረው መብት፤በመናገር፣ በመጻፍ፣ ከሌሎች ጋር በመሰብሰብ፣ በመደራጀትና ሰላማዊ ሰልፎችን በማድረግ በኩል የተከበሩ መሆናቸው፤ የስነ-አስተዳደር ተሳትፎውን በሚመለከት በየትኛውም የሀገሪቱ ክልል ውስጥ ለሚደረገው ማንኛውም የአስተዳደር ውድድር፤ የፈለገውን የሰነ-አስተዳደር ድርጅት የመደገፍና የመከተል፤ የፈለገው ተወዳዳሪ የመምረጥና ራሱም የመመረጥ መብቱ የተጠበቀለት መሆኑ፤ ሥራንና ሀብት ማፍራትን በተመለከተ በማንኛውም የሀገሪቱ ክፍል ሀብት አፍርቶ፤ ግሮ ጥሮ፤ ራሱ ተቀጥሮ ወይንም ሌሎችን ቀጥሮ በማሠራት ሀብት ማፍራትና መተዳደር መብቱ መከበሩ፤ በሃይማኖት ረገድ የፈለገውን ሃይማኖት መከተል ወይንም አጠቃሎ ሃይማኖት ያለመከተል መብቱ መጠበቁ፤ እነኚህ ሁሉን ባያጠቃልሉም፤ መሠረታዊ የዴሞክራሲያዊ መብቶች ናቸው።

ትስስረ-ትውልድ ማለት፤

በትውልድ ደረጃ፤ በቅርብ በተሳሰረ ዝምድና የተቆላለፈ፤ አንድ ቋንቋ በመናገር፤ ባንድ አካባቢ በመሥፈር ወይንም ኩታ ገጠም በሆነ ወይንም ሌሎች ጣልቃ በገቡበት የሀገሪቱ ክፍል በመዘርጋት፤ የጋራ የሆነ የቆዬ ታሪክ የሚጋሩ ሰዎች ማለት ነው። አንድ ግለሰብ፤ ከአንድ ትስስረ-ትውልድ ወይንም ከአንድ ትስስረ-ትውልድ በላይ ከተገኙ ወላጆቹ ይወለዳል። ትስስረ-ትውልድ፤ በኅብረተሰብ ዕድገት ሂደት የሚለወጥና ቋሚ ያልሆነ ክስተት ነው። በተለይም በአንድ ሀገር ባሉ የኅብረተሰቡ ክፍሎች ያለው ግንኙነትና በመካከላቸው ያለው የንግድ ልውውጥ እንቅስቃሴ እያደገ ሲሄድ፤ አጥር የሆነው የትስስረ-ትውልድ ማነቆው ይፈርሳል። የኅብረተሰቡ አባላት እንቅስቃሴ ይጎለብታል። በተለያዩ የትስስረ-ትውልድ አባላት መካከል ያለው በጋብቻ መተሣሰር ያድጋል። የሀገሪቱ ተወላጆች ሀገርዊ ዕሴቶቻቸውን የትውልድ መገለጫቸው ያደርጋሉ። በዚህ ወቅት፤ በያንዳንዳቸው የትስስረ-ትውልድ ተከልለው የተቀመጡት ታሪክና ዕሴቶች ከጠቅላላ ሀገራዊ ዕሴቶች ጋር ባንድ ሆነው የጋራ ይሆናሉ። እዚህ ላይ መሰመር ያለበት፤ ትስስረ-ትውልድ፤ በመንግሥት ትዕዛዝ የሚደነገግና የሚሽከረከር ባህርይ አለመሆኑ ነው። ማንንም ግለሰብ በትስስረ-ትውልዱ ራሱን እንዲገልፅ ማስገደድ አይቻልም። ይህ ከተደረገ፤ አድራጊው የተለየ ጉዳይ ያለውና የኅብረተሰብ ዕድገትን የተፀናወተ ክፍል ነው። የኅብረተሰብ ዕድገትን መሐንዲስ ሆኖ መቀየስ፤ ፀረ-ኅብረተሰብነት ነው።

ሰነ-አስተዳደር ትርጉሙ ግልፅ ነው።
ማንኛውም አስተዳደርን የተመለከተ ጉዳይ፤ ፍልስፍና፣ መመሪያና የአፈፃፀም ሂደት አለው። ይህ ባጠቃላይ አንድ ዘርፍ ነው። የጥናትና የተግባር ጎን አለው። ይህን ዘርፍ ነው ስነ-አስተዳደር የምንለው። እንግዲህ ይህ የግንዛቤ ማስተዋያ፣ የፍልስፍና መመርኮዣና የተግባር መለኪያ ያለው መስክ ነው። የተለያዩ፤ ተፃራሪ፤ ትክክለኛና ትክክል ያልሆኑ መልኮች አሉት።

ስለ ፅንሰ ሃሳቦቹ ይኼን ያህል ከዘረዘርን፤ ሲተሣሰሩ ያላቸውን የትርጉም ምጥቀት እንመዝን። ግለሰብ ኢትዮጵያዊ የሚኖረው የዴሞክራሲያዊ መብቶች ከላይ ለያንዳንዱ ፅንሰ ሃሳብ ከተዘረዘረው የተለዬ አይሆንም። የትስስረ-ትውልድ ስነ-አስተዳደር ሲጨመር ግን ለወጥ ይመጣል። በመሠረቱ አንድ ኢትዮጵያዊ ግለሰብ፤ በኢትዮጵያዊነቱ በሀገሪቱ የሰነ-አስተዳደር ሂደት ሲሳተፍ፤ ያለው መለያ፤ ኢትዮጵያዊነት ብቻ ነው። ከማንኛውም ትስስረ-ትውልድ መምጣቱ፤ ተሳትፎውን ሊያግደው ወይንም ሊረዳው አይገባም። ለመሳተፍ፤ ከኢትዮጵያዊነቱ ሌላ ተጨማሪ ምንም ነገር እንዲያቀርብ መፈተሽ የለበትም። ከአንድ በላይ ከሆኑ የተለያዩ ትስስረ-ትውልዶች በመምጣቱም፤ በሀገሪቱ በሚኖረው የስነ-አስተዳደር ተሳትፎው እንቅፋት ሊገጥመው አይገባም። መለኪያው ኢትዮጵያዊ ነው ወይንስ አይደለም? የሚለው ብቻ መሆን አለበት።

እዚህ ላይ የሀገራችንን የተለዬ ሁኔታ ማካተቱ ግድ ይሆናል። በኢትዮጵያ የስነ-አስተዳደር ታሪክ ውስጥ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ሕጋዊነት አግኝቶ የትስስረ-ትውልድ አስተዳደር ተግባራዊ የሆነው በትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ነው። በርግጥ በዘመነ መሣፍንት ወቅት፤ ማዕከላዊ መንግሥቱ በተዳከመበት ዘመን፤ የመንደሩን ሰዎች፣ የቀየውን፣ የጎጡን፣ የደብሩን፣ የምክትል ወረዳዉን፣ ያውራጃውን ሰዎች አሠልፎ ለሥልጣን መቆናጠጫ መሠሪያ ማድረግ፤ የተስፋፋ ነበር። ያኔም ቢሆን ግን፤ ያንድ አካባቢና ያንድ ትስስረ-ትውልድ መሣፍንትም እርስ በርሳቸው የሚዋጉበትና ከሩቅ ዝምድና ከሌላቸው መሣፍንት ጋር መመሳጠር የተለመደ ነበር። ባሁኑ ሰዓት ያለው የትስስረ-ትውልድ አስተዳደር፤ ከታሪክ አኳያ ወደ ኋላ የተጎተተ የወቅታችን መርዝ ነው። የትስስረ-ትውልድ መሠረታዊ ስነ-አስተዳደሩ፤እኛእናሌሎቹየሚል መጋረጃ ማካለል ነው። ሌሎችን እንደራስ አድርጎ ማየት ይቀርና፤ የውጪ እና አልፎ ተርፎም እንደተቀናቃኝና ተፎካካሪ አድርጎ ማየት የመጋረጃው ተልዕኮ ይሆናል። ይህ መጋረጃ ውሎ አድሮ፤እኛትክክለኞች፤ሌሎቹትክክለኛ ያልሆኑ፤እኛየተበደልንሌሎቹየተጠቀሙ የሚል የማካለያ ልዩነት አበጅቶ፤ በጦርነት ብቻ የሚፈታ ቅራኔን ያራምዳል። መዘንጋት የሌለበት፤ በዚህ ሂደት፤ አናሳ የተባሉ የትስስረ-ትውልዶች፤ ከማዕከላዊ ሀገራዊ አስተዳደር ተሳትፎ መገለላቸውን ነው። ዴሞክራሲና የትስስረ-ትውልድ ስነ-አስተዳደር እሳትና ጭድ ናቸው። የትስስረ-ትውልድ ቆጠራ በስነ-አስተዳደር ተሳትፎ ከገባ፤ የግለሰብ ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲያዊ መብቶች ገደል ገቡ ማለት ነው። አንድም፤ ግለሰቡን ኢትዮጵያዊ ያለመብት ባዶ ያስቀረዋል፤ ሌላም በትስስረ-ትውልዶች መካከል አቻነት ያጣ ስነ-አስተዳደር በሀገሪቱ ያነግሣል። ባንድ መንገድ ወይንም በሌላ፤ አንዱ ትስስረ-ትውልድ በላጭ ሆኖ ይገኛል። እናም፤

የትስስረ-ትውልድ ስነ-አስተዳደር የግዴታ ከአንድ የትስስረ-ትውልድ የበላይነት ጋር የተቆራኘ ነው። ሥልጣን በመያዙ ብቻ ወይንም ቀጥተኛ የሆነ የበላይነት በተዘዋዋሪ መንገድ በመጨበጡ፤ የራሱን ትስስረ-ትውልድ የበላይነት ማስፈሩ የማይቀር ሀቅ ስለሚሆን ነው። ምክንያቱም፤ በሥልጣን ላይ የሚወጣው ክፍል የሚወክለው፤ የትስስረ-ትውልዱን እንጂ ሌሎቹን አይደለምና ነው። ይህ ማለት አናሳና ጎልባታ ትስስረ-ትውልዶች ይኖራሉ። እኒህ ጎልባታ የተባሉት ትስስረ-ትውልዶች ደግሞ በቁጥራቸው ብዛት ብቻ የሀገሪቱን የስነ-አስተዳደር ምኅዳር ተቆጣጣሪዎች ይሆናሉ። አናሳ የተባሉት የትስስረ-ትውልዶች ከማዕከላዊ ሥልጣኑ ምን ጊዜም የራቁ ይሆናሉ። እናም የግለሰቡ ኢትዮጵያዊ መሆን ትርጉም የለሽ ባዶ ቀፎ ይሆናል። ግለሰቡ የትስስረ-ትውልዱ ጥገኛ ይሆናል። በዚህ በኩል የቡድን መብት በሚል የሚቀርበው ክርክር ሆድ አያሞላም። ምክንያቱም፤ አንድ ግለሰብ፤ ከፈለገው ሌላ ግለሰብ ጋር የመቧደን መብት አለው፤ ነገር ግን የአንድ ትስስረ-ትውልድ አባል ስለሆነ፤ ከዚያ ትስስረ-ትውልድ አባላት ጋር የግድ ሆነ የውድ መተሳሰር አለብህ የሚለው ፅንሰ ሃሳብ፤ ኢትዮጵያዊነቱን ይጋፋል። በሌላ በኩል ደግሞ፤ የዚያ ትስስረ-ትውልድ አባል ያልሆኑ በዚያ ቡድን መግባት ስለማይችሉ፤ የተለየ መብት መፍጠርና መለያየት ይመጣል። ይህ ደግሞ ዴሞክራሲያዊ ያልሆነ አሠራር ነው። እናም አፍራሽ ነው።

የግንባር መሠረታዊ ግንዛቤ፤

ጠላትን ለይቶ ማወቅና ወዳጅን ለይቶ ማጥበቅ፤ በታጋይ ኃይሎች መካከል፤በኢትዮጵያዊያንም ሆነ በሌሎች ሀገሮች የትግል ታሪክ ዘንድ ዋና የመነሻ ነጥብ ነው። ይህ፤ ሊያደርጉት ለሚፈልጉት ማንኛውም ወገን-የለዬ ትግል፤ ግዴታ አስፈላጊ ጨብጥ ነው። ፍቅርም ሆነ ጠብ መነሻና መድረሻ አለው። እኒህ ሁለት ክንውኖች፤ ጠቡም ሆነ ፍቅሩ፤ በሁለት አካላት መካከል ለሚደረጉ ግንኙነቶች መግለጫዎች ናቸው። እኒህ አካላት ደግሞ የራሳቸው የሆነ ምንነት፣ ባህርይ፣ ዓላማና ግብ አላቸው። ስለዚህም፤ አንዱ አካል ከሌላው አካል የሚለይበት ጉዳይ አለ። አንዱ አካል ከሌላው በፍቅርም ሆነ በጥላቻ የሚተያይበትም ጉዳይ አለው። ይህ መሠረታዊ ጉዳይ ደግሞ፤ አንዱ ከሌላው ጋር እንዲፋቀር ወይንም እንዲጣላ የሚያደርገው ንክክ* ነው።

ትክክለኛ ግንባር የሚመሠረተው፤ ግንባር መሥራቾቹ ዓላማቸውን የሚያራምዱበትና ጥቅም የሚያገኙበት ሆኖ ሲያገኙት ነው። የመጨረሻ ግባቸው ተፃራሪ በሆኑ አካሎች መካከል ትክክለኛ ግንባር አይመሠረትም። እኒህ ጊዜያዊ ትብብር  እንጂ፤ ግንባር ሊመሠርቱ ተፈጥሯቸው አይፈቅድላቸውም። ግንባር አውቀው የሚገቡበት ቤት ነው። ግንባር በፈቃደኝነት ላይ የተመረኮዘና መከበር ያለባቸው መመሪያና ሕጎች ያሉበት አካል ነው። ግንባር ውድድር አለበት። ግንባር ትብብር አለበት። ግንባር አንድም በስነ-አስተዳደር መሠረቴ የምተማመነው እኔ ስለሆንኩ፤ በትክክለኛ መንገድ ከሄድኩ ከሌሎቹ ተባባሪዎቼ የበለጠ እኔ ግቤን የምመታ ነኝ። ብሎ በማስላት፤ በፍላጎት በጅ የያዙትን በሙሉ ባንድ ጉድጓድ የመክተት ስሌት ነው። ጥንካሬን በመተማመን፤ እዚያ ግንባር በመግባት፤ በሚያደርጉት ጉዞ፤ለኔ ቀና መንገድይፈጠርልኛል በማለት የሚጫወቱት ቁማር ነው።

የግንባር መሠረታዊ ዓላማ፤ ጠላትን በማሳነስ፤ የወዳጅን ጉልበት ለማጠንከር ነው። ቀጥሎ ደግሞ ጊዜያዊ አጣዳፊነት የሌለውን ግጭት፤ ጊዜ ሰጥቶ፤ በሂደት ለማስወገድ አለበለዚያም ለወደፊት ለማስተላለፍ ነው። በዚህ መንገድ፤ ግንባር ጥንካሬን የሚሰጥ፣ የወዳጅን ሠፈር አተልቆ የጠላትን ወገን የሚያሳንስ፤ የስነ አስተዳደር ብስለትን የሚጠይቅ የትግል ስልት ወይንም ዘዴ ነው። ግንባር በግልፅ ተመሥርቶ ባደባባይ ሊታወጅ ይችላል። ግንባር በህቡዕ ሊመሠረትና በድብቅ ሊጠበቅ ይችላል። በዚህ መንገድ የሚመሠረተው ግንባር፤ በተወሰኑ የድርጅቶች አባላት መካከል እውቅና አግኝቶ፤ ባደባባይ ለመውጣት ጊዜውን ሊጠብቅ ይችላል። ግንባር አንድ ቀመር ብቻ ተከትሎ፣ ይኼን የተከተለ ብቻ፣ ይኼ ካልሆነ የሚባልበት፤ ያለቀ የደቀቀ ቀኖና አይደለም። መሠረታዊ የሆኑት ምንነቶቹ ግን እስካሁን የጠቀስናቸው ናቸው።

በአንድ የሀገር ትግል ውስጥ፤ ግንባር እንዲፈጠር የሚያመቹ ሁኔታዎች አንድ ጊዜ ይከሰታሉ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ተስለምልመው ይጠፋሉ። ትክክለኛ ግንባር እንዲፈጠር የሚረዱት ሶስት ጉዳዮች ናቸው።

አንደኛውና መሠረታዊ
የሆነው ጉዳይ፤ ግንባር ሊፈጥሩ በሚሰባሰቡ ድርጅቶች መካከል፤ የዓላማና የግብ አንድነት፣ ተመሣሣይነት ወይንም ተቀራራቢነት መኖሩ ነው።  በሂደት ልዩነታቸውን ሊያጠቡና አንድ ሊሆኑ በሚችሉ ድርጅቶች መካከል፤ ትክክለኛ ግንባር ሊፈጠር ይችላል። ይህ የግድ መፈጠር ያለበት ግንባር ነው። ተቀራራቢነት ኖሯቸው አንድ ሊሆኑ የማይችሉ ድርጅቶች ቢኖሩም፤ በመካከላቸው ያለው ልዩነት ጠብን ግድ የሚል ካልሆነ፤ በድርድር ተቻችለው በመኖር ግጭቱን ያስወግዱታል።

ሁለተኛው     አንፃራዊ የበላይና የበታች በመካከላቸው የሌለባቸው ድርጅቶች መሆናቸው ነው። ግንባሩን ለመፍጠር በሚፈልጉት ድርጅቶች መካከል አንፃራዊ የበላይነት የያዘ አንድ ድርጅት የሌለበት የትግል ፍጥጫ ውስጥ ሆነው መገኘታቸው ነው።
ሶስተኛው     ዴሞክራሲያዊ አሠራር የሠፈነባቸው ድርጅቶች መሆናቸው ነው።ዴሞክራሲያዊ አሠራር በሁሉም ድርጅቶች ውስጥ በመኖሩ፤ መተማመንና ለሕግ መገዛት ጎልቶ ቦታውን ስለያዘ፤ ያላንዳች ቅሬታ ግንባሩ ሊተገበር ይችላል።

የትስስረ-ትውልድ ስነ-አስተዳደርና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት

በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያ የስነ-አስተዳደር ምኅዳር በትስስረ-ትውልድ ስነ-አስስተዳደር ተወሯል። ይሄን በመመልከት እጅን ሠጥቶ አብሮ መንጎድ ቀላል ነው። በትስስረ-ትውልዱ አምባገነን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ስነ-አስተዳደር በመጠመቅ፤ እኔም እንደነሱ በማለት፤ አብሮ ማጫፈር ቀላሉ መንገድ ነው። በሌላ በኩል ግን፤ የሀገራችንን እውነታ በማጤን፤ ያለፈውንና የመጪውን በማገናዘብ፣ ይህ ጉዞ አደገኛ መሆኑን ተረድቶ፤ እምቢዮ በማለት፤ ትክክለኛ የሚሉትን መንገድ መከተል ሀገራዊ፤ ትውልዳዊና ታሪካዊ ኃላፊነታችን ነው። ይሄን ስናደርግ ብዙ ክፍሎች ዓይኖቻቸውን ያጉረጠርጣሉ። እንግዲህ ጉዳዩ ፍራቻ ነው? ወይንስ ሽንጥ ያለው አለመኖር? ነው።

የትስስረ-ትውልዱ አምባገነን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት እስከዛሬ ሲገዛ እንደነበረው፤ ለወደፊቱም ለመቀጠል ሕልሙና እቅዱ ነው። ባለፉት ሃያ ሁለት ዓመታት፤ ይህ ቡድን፤ ከተቃዋሚዎች በኩል ጠንካራ ፈተና የተፈጠረበት፤ የግንቦት ፲፭ ቀን ፲፱፻፺፯ ዓመተ ምህረት ምርጫ በተደረገ ጊዜ ብቻ ነበር። እንደማይደገም በግልፅ ይህ ቡድን ቃል ገብቶልናል። በትስስረ-ትውልድ ስነ-አስተዳደርም ሆነ በመሠረታዊ ሀገር አቀፍ ስነ-አስተዳደር፤ ይህ አምበገነን መንግሥት በሕግ ለመገዛት ቅንጣት ዓላማ እንደሌለው በግልፅ አሳይቶናል። ቁም ነገሩ፤ ይህን ቡድን በሕግና በስነ-ሥርዓት አቸንፋለሁ ብሎ፤ እሱ በቀደዳቸው መንገዶች መንጎዱ ሳይሆን፤ መሠረታዊ ልዩነቶችን አውቆና አስምሮ፤ ወደፊት ለመሄድ አስፈላጊ ትግባሮችን መንደፉ ላይ ነው።

የትስስረ-ትውልዱ አምባገነን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት የትስስረ-ትውልድን ስነ-አስተዳደር የሚያራምድበት ዋናው ምክንያት፤ በሀገሪቱ ውስጥ ተቀናቃኝ እንዳይኖረው ብቻ ነው። በርግጥ በትክክል ስነ-አስተዳደሩን ቢከተለው፤ የቡድኑ መነሻ አናሳ ትስስረ-ትውልድ ስለሆነ፤ ተጠቂ ይሆናል። ስለዚህም ሀገር አቀፍና ትስስረ-ትውልድ ወለድ የሆነ ዲቃላ ስነ-አስተዳደር እየተከተለ ነው። ሲመቸው በትስስረ-ትውልድ ስነ-አስተዳደር ይመረኮዛል። የሥልጣን ጥያቄ ሲመጣበት፤ አንድም ታግዬ ያገኘሁት ነው ይላል። ያለዚያም እኔ የፈጠርኳችሁ ናችሁና ምን አገባችሁና፤ ምንስ ቆርጧችሁ ትጠይቁኛላችሁ ይላል። በሶስተኛ ደረጃ ደግሞ፤ ሕጉን እኔ እንጂ እናንተ አትተረጉሙትም ይላል። መስሎ ከታየው ደግሞ፤ አረንጓዴ ብጫ ቀይ ሰንደቅ ዓላማችንን እያውለበለበ፤ የሀገር ጉዳይ ነው ይላል። እንግዲህ የትስስረ-ትውልዱ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት የትስስረ-ትውልዱ ስነ-አስተዳደር ለራሱ ሕልውና እንደሚያሰጋው ያውቃል። አማራጩ ሀገር አቀፍ ስነ-አስተዳደሩም ቦታ እንደማይሠጠው ያውቃል። እናም በጉልበት መግዛቱና በሥልጣን መሰንበቱ፤ ባሁኑ ሰዓት የሕልውናው ጥያቄ ነው። ከዚህ ውጪ ሊኖር አይችልም። ምንም ዓይነት ድርድርና የሥልጣን መጋራት በሕልናው መዝገበ ቃላት ቢፈለግ አይገኝም። እኛ ከዚህ ልንረዳ የሚያስፈልገን፤ አንደኛ ለዚህ ቡድን ማንኛውም የስነ-አስተዳደር መንገድ፤ ለሥልጣኑ መሰንበቻ እንጂ፤ በሀቅ የሚተገበር ፍልስፍናውና መመሪያው እንዳልሆነ ነው። ከዚህ አኳያ፤ በማንኛውም መንገድ ቢኬድ፤ ጦሩን መዞ ሥልጣኑን ለመጠበቅ እንደሚገድል መገንዘብ አለብን። እናም ይኼን ቡድን ከሥልጣን የማስወገዱ ጉዳይ፤ መታየት ያለበት፤ አምባገነኑን በሌላ ከመተካት አንፃር ብቻ ሳይሆን፤ ተከታዩ አስተዳደር፤ የሚከተለው የስነ-አስተዳደር ፍልስፍናና የአስተዳደር መመሪያው፤ የኢትዮጵያዊያንን መብት የሚያከብርና የሀገሪቱን ነፃነት የሚያስጠብቅ እንዲሆን ነው። የትስስረ-ትውልድ ስነ-አስተዳደር፤ አንድም ለኢትዮጵያዊያን እኩልነት እንቅፋት ነው፤ ሌላም ውሎ አድሮ ሀገሪቱን ለመበጣጠስ የተዳፈነ ረመጥ ነው።

ይኼን ግንዛቤ በአእምሯችን ይዘን፤ እስኪ ባጠቃላይ በትግሉ ሂደት በተለይ ደግሞ በዚያ የግንቦት ፲፭ ቀን ፲፱፻፺፯ ዓመተ ምህረት ምርጫና ከዚያ ወዲህና ከዚያ በፊት የተፈጠሩትን ግንባሮች እንመልከት።

የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር የፈጠረው ግንባርየላይ አልጋ የውስጥ ቀጋየዘረኛው አምባገነን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ራሱ ከነማንና ከነማን ድርጅቶች የተዋቀረ ግንባር መሆኑ ባይታወቅም፤ ሌሎቹን ባምሳሉ ጠፍጥፎ፤ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባርን ፈጥሯል። በዚህ ግንባር ውስጥ የተካተቱትና በዋናነት የሚጠሩት፤ ከራሱ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ሌላ፤ ብሔራዊ የአማራ ዴሞክራሲያው ንቅናቄ (ብአዴን) የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) እና የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) ናቸው። ይህ አካል አራት መንገድ ግንባር አልነበረም።

አንደኛ፤      ከትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር በስተቀር፤ ነፃ ድርጅቶች የሉበትም፤ ነፃ ድርጅቶች የመሠረቱትም ግንባር አልነበረም። ከትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር በስተቀር፤ ሌሎችን ይኼው የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ጠፍጥፎ የፈጠራቸው አምሳሎቹ እንጂ ነፃ ድርጅቶች አልነበሩም፤ አይደሉምም።

ሁለተኛ፤      ከትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር በስተቀር፤ በሌሎች ድርጅቶች ጥቅም ላይ የተመሠረተ አልነበረም። ከኢትዮጵያ ነፃ ለመውጣት የተመሠረተ ነፃ አውጪ ድርጅት፤ ከሌላው ከኢትዮጵያ ነፃ ለመውጣት የተመሠረተ ድርጅት ጋር፤ ከትብብር ያለፈ፤ ግንባር የመፍጠር ዓላማ ሊኖረው አይችልም።

ሶስተኛ፤      ከትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር በስተቀር፤ በሌሎች ድርጅቶች ፍላጎት አልተመሠረተም። የሌሎቹ  ድርጅቶች ፍላጎት፤ ለየራሳቸው ወገን ነፃነት መሆኑ ቀርቶ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባርን ጥቅም ማስጠበቅ አልነበረም። ሆኖም ግን ይኼንን ተግባር በመፈፀም ላይ ያሉ የድርጅት ቀፎዎች ናቸው።

አራተኛ፤      ራሳቸውን ነፃ ለማውጣት የተመሠረቱ ድርጅቶች፤ ከነፃነታቸው በታች ለሆነ ጉዳይ ግንባር አይመሠርቱም። እናም ከጥቅም፣ ከፍላጎት፣ ከነፃነትና ከዓላማ አንፃር ትርጉም የሌለው ግንባር፤ የውሸት ግንባር ነበር፤ ነውም።

በተለይ ደግሞ ደርግ ከወደቀ በኋላ፤ የግንባርነታቸው ትርጉም በጓዳ በር አፈትልኮ አምልጧል። ነፃ እንውጣ ብለው ከተነሱበት ሀገር ነፃ ወጥተዋል ወይንም አሁንም በባርነት ውስጥ ናቸው። ገዥ ሆኖ ባርነት የለም። ገዥ ሆኖ ነፃ አውጪ ድርጅት መሆን የለም። ስለዚህ ትርጉም የሌለው ነፃ አውጪነት ሆነ። አሁንም የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ሆኖ የተቀመጠው ገዢ ቡድን፤ ከማን ነፃ ሊወጣ ነው? ደርግ ሲወድቅ፤ መጀመሪያ የህዝባዊ ግንባር ሓርነት ኤርትራ፣ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባርና የኦሮሞ ነፃነት ግንባር የተዋዋሉበት ትብብር ፈረሰ። በመከተል ደግሞ ይኼ የኢሕአዴግ የውሸት ግንባር መፍረሱ አይቀሬ ሆኗል። እኒህ ድርጅቶች ለሚወክሉት ወገን ሳይሆን፤ ለትስስረ-ትውልዱ አምባገነን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት የቆሙ ናቸው። አያስገርምም፤ ለዚሁ ነውና የተፈጠሩት። ለዚህ ማጣፊያ የሆነው ደግሞፌዴራልየሚል ጌጥ በአስተዳደሩ ላይ መለጠፉ ነው። ይህ ነበር እና ነውም በገዢው ቡድን በኩል የነበረውና ያለው የስነ-አስተርዳደር ሀቅ። በአንፃሩ ደግሞ በተቃዋሚው በኩል የተመሠረቱ ግንባሮች ነበር። የገዢውን ግንባር ምሥረታ እዚህ ላይ ጋብ አድርገን እስኪ የራሳችንን የተቃዋሚውን ወገን እንመልከት። 

በተቃዋሚው ወገን የተደረጉ ትብብሮችና የተመሠረቱ ግንባሮች፤

ሲሮጡ የታጠቁት ሲሮጡ ይፈታል።

የተቃዋሚውን ወገን እንመልከት። ከኢትዮጵያ ነፃ መውጣት አለብኝ ብሎ የተመሠረተ የስነ-አስተዳደር ድርጅት፤ ኢትዮጵያን ነፃ አውጣለሁ ከሚል ድርጅት ጋር ግንባር ሊመሠርት አይችልም፤ ዓላማቸው ተፃራሪ ነውና! ከዚያ መለስ እንኳ፤ በትስስረ-ትውልድ ዙሪያ የተሰባሰቡና በሀገረ አቀፍ ዓላማ የተዋቀሩ ድርጅቶች ግንባር ሊመሠርቱ አይችሉም። ከላይ እንደተዘረዘረው፤ የያንዳንዱ ድርጅት መሠረታዊ ዓላማና ግብ፤ ሊመሠርት ከሚፈልገው ግንባር ምንነት ጋር አብሮ መሄድ አለበት። የግንባሩ ዓላማ ከራሱ ዓላማ ከተፃረረ፤ ግንባሩ መመሥረት የለበትም፤ ከተመሠረተም የውሸት ነው ማለት ነው። ኢትዮጵያን ከትስስረ-ትውልዱ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ነፃ ለማውጣት፤ ኢትዮጵያዊ የሆነ ዓላማና ግብ መተለም ግዴታ ነው። አለበለዚያ የግንባሩ ዓላማ ኢትዮጵያን ነፃ ለማውጣት አይደለም ማለት ነው፤ ኢትዮጵያን ነፃ የሚያወጧት ኢትዮጵያዊያን ናቸውና።

ግንባር በተቃዋሚው ወገን የተጀመረው፤ የስነ-አስተዳደር ትግል በሀገራችን በተጀመረ ጊዜ የነበረው አፈና መፈናፈኛ ስላልሠጠ፤ የተለያዩ ቡድኖች በተለያየ ቦታ ትግላቸውን ለተለያየ ዓላማ በመጀመራቸው ነው። የዳበረ ቀርቶ ማንኛውም የስነ-አስተዳደር ውይይት በሀገራችን ባለመኖሩ፤ እኒህ የተጀመሩ የስነ-አስተዳደር ቡድኖች መቀራረባቸው ቀርቶ፤ እርስ በርሳቸው ማንነታቸውን በየራሳቸው መለኪያ እየመዘኑ፤ ወዳጅ ነው ጠላት ነው የሚል የፍርድ በትር እየመዘዙ፤ መራራቅ ያዙ። የኤርትራ ነፃ አውጪ ግንባር/ተጋድሎ ሀርነት ኤርትራ/ጀብሃ፣ የኤርትራ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር/ህዝባዊ ግንባር ሓርነት ኤርትራ/ሸዓቢያ፤ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር/ኦነግ፣ ቀደም ብለው የተመሠረቱ የትስስረ-ትውልድ የስነ-አስተዳደር ድርጅቶች ናቸው። ይህ ግን የሕልውናቸው መቀጠል፤ የግድ አያደርገውም። እኒህ የትስስረ-ትውልድ የስነ-አስተዳደር ድርጅቶች ዋና ሚናቸው፤ የትስስረ-ትውልድ ስነ-አስተዳደርን ቋሚና ግዴታ እንዲሆን ለማድረግ ብቻ ነው።

ኅብረት ተብሎ፤ በዶክተር በየነ ጴጥሮስ፣ በዶክተር መራራ ጉዴናና በሌሎች በውጭ ሀገር በቀሩት ድርጅቶች መካከል የተፈጠረው ግንባር፤ የውሸት ግንባር ነበር። በመካከላቸው ሀገር አቀፍና የትስስረ-ትውልድ የስነ-አስተዳደር ድርጅቶች ነበሩባቸው። ከነዚህ በኅብረቱ ከተካተቱት የስነ-አስተዳደር ድርጅቶች መካከል፤ አንደኛውን የትስስረ-ትውልድ ስነ-አስተዳደር ድርጅት ይመሩት የነበሩ፤ እኔ በምወክለው ሕዝብ መሬት ሌሎች የግንባሩ አባል ድርጅቶች መወዳደር የለባቸውም።ነበር ያሉት። ምርጫው ተጠቃሎ በአካባቢያቸው የአቸነፉት ቁጥር ሲገለጥና ግንባሩ ደስ ብሎት ሲወያዩ፤ እኒህ መሪ፤ድሉ የኔ አካባቢ ሕዝብ እንጂ የኢትዮጵያ ሕዝብ አይደለምነበር ያሉት። በተመሳሳይ መንገድ ሌላውም መሪ በአካባቢያቸው ከራሳቸው ድርጅት በስተቀር ሌሎቹ የግንባሩ አባል ድርጅቶች ተወዳዳሪ እንዳያቀርቡ አድርገዋል። ይኼ የሚገርም አልነበረም። እኛ የምንወክለው ወገናችን ነው ባሉት ቦታ፤ ሌሎች ተወዳዳሪ ማቅረባቸውን በምንም መንገድ ሊቀበሉት አይችሉም ነበርና። ይሄ የተፈጥሯቸው ክን* ነው። ቀጥሎም በሀገር ውስጥ የተቀመጡት በውጪ ከሚገኘው የኅብረቱ አካል ተለዩ። ይኼም የሚያስገርም አልነበረም።

በኤርትራ የሸዓቢያው ኢሳያስ፤ ጀብሃን፣ በወያኔ ተባባሪነት ከኤርትራ ምድር ጠራርጎ በማስወጣት፤ ብቻውን ሜዳውን ጋልቦበታል። በኤርትራ ሕዝብ ዓይን፤ ለሸዓቢያ ከጀብሃ የበለጠ የሚቀርበው የስነ-አስተዳደር ድርጅት አልነበረም። የነአረጋዊ በርሄና መለስ ዜናዊ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር፤ ተጋድሎ ሓርነት ትግራይን፣ ጠርናፊትን፣ ኢዲዩንና ኢሕአሠን፤ ከትግራይ መሬት ውጡ በማለት ወግቶ አባሯል። ልብ አድርጉ፤ ቢያንስ ተጋድሎ ሓርነት ትግራይ፣ የትግራይን ነፃነት ሊያመጣ የተመሠረተ ግንባር ነበር። በትግሬዎች ዓይን፤ ለትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር፤ ተጋድሎ ሓርነት ትግራይ አጋሩና ደጋፊው ነበር። ሌላ ድርጅት ባጠገቡ እንዲኖር የማይፈልገው የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር፤ እኔና እኔ የምወክለው እንጂ ሌሎች ኢትዮጵያዊያን በትግራይ ምድር መኖር የለባቸውም ብሎ፤ በትግራይ ምድር፣ በወልቃይት፣ በጠገዴ፣ በጠለምት፣ በዋግ ያሉትን ኢትዮጵያዊያን አባሯል። ብዙዎችን ገድሏል። በነዚህ አካባቢዎች የነበሩት አማሮች ናቸው። እኒህ አካባቢዎች ከዚያ በፊት የጎንደርና የወሎ ክፍሎች ነበሩ። መሠረታዊ ፀረ-አማራ አቋሙ በየቦታው በዝርዝር የተገለፀ ስለሆነ እዚህ ጥልቅ አንገባበትም።

ያልተፈጠሩ ግንባሮች፤
 “ ሳይሉ ጥፈት ውል ሳይዙ ሙግት”  የስነ-አስተዳደር ሂደት ግድ የሚለውን የግንባር ምሥረታ ወደ ተግባር ማስኬድ የማይቻለው፤ ከላይ በተጠቀሰው ምክንያት ሆኖ፤ በግልፅ ሲቀመጥ፤ በያንዳንዱ ድርጅት የውስጥ አስተዳደር ጉድለት ሲኖርበት ነው። ይህም የዴሞክራሲያዊ አሠራር ተቀባይነት በሌለው ቦታ፤ ትክክለኛ ግንባሮች ሊፈጠሩ አይችሉም ማለት ነው። በአብላጫው ምክንያት ሆኖ የሚቀርበው፤ የሚዋቀረውን የግንባር አስተዳደር በሚመለከት፤ የድርሻ ቦታን መሻማቱ ላይ ነው። እኔ ግንባር ከተፈጠረ የግል ሥልጣኔን አጣለሁ ከሚል ፍርሀትም ነው።

ይህ የሚከሰትበት መንገድ፤እኔ ታሪክ አለኝ፣ . . . እኔ ጥንካሬ አለኝ፣ . . . እኔ የትግል መስመሬ የላቀ ነው፣ . . .  እኔ . . . እኔ . . . እኔ . . . እና እኔ ጠሪ ካልሆንኩበት ግብዣ አልሄድም፣ . . . እኔ አጀንዳውን ካላቀርብኩ አልመጣም፣ . . . እኔ የበላይነቱን ባንድ መንገድ ሆነ በሌላው ካልያዝኩ አልቀላቀልም፣ . . . አባላቴ እስኪያፀድቁት መቆየት አለብኝ፣ . . . መላ የአባላት ስብሰባ እስክጠራ መቆየት አለብኝ፣ . . . ይኼኛው አንቀፅ ለአባላቴ አስቸግሯል፣ . . . ጊዜው አሁን አይደለም፣ . . .” የሚሉት ማደናቀፊያ ምክንያቶችን በመምዘዝ ነው።

በግልፅ በኛ ሀገር በትግል ተመክሯችን ጎልቶ የሚታይ አንድ ሀቅ አለ። ከድርጅቶች ይልቅ የድርጅቶቹ መሪዎች ቦታዉን አጣበው መያዛቸው ነው። ከድርጅቶች ይልቅ መሪዎቹ የሚታወቁት፤ ወሳኝና ፈላጭ ቆራጮቹ እነኚሁ መሪዎች ስለሆኑ ነው። በርግጥ ይኼ፤ አንድ ድርጅት የዴሞክራሲያዊ አሠራርን የማይከትል ለመሆኑ ገላጭ ነው። ከሞላ ገደል በኢትዮጵያ ያሉ የስነ አስተዳደር ድርጅቶቾ በሙሉ በዚህ አባዜ ተሰልበዋል። እናም የእከሌ ድርጅት መባሉ ይቀላቸዋል። ማንም የድርጅት አባል ይኼን አሜን ብሎ የሚቀበል የለም። ይኼ ክደቱ ራሱ ምስክር ነው። መሪዎቹ የዴሞክራሲያዊ አሠራርን የሚከተሉ ቢሆኑ ኖሮ፤ አንድም የኃላፊነት ዘመናቸውን በመተዳደሪያ ደንባቸው እንዲሠፍር በማድረግ፤ በየወቅቱ የመሪዎች ልውውጥ ባደረጉ ነበር። ሌላ እንደነሱ ሆኖ የሚመራ ተተኪ አጥተናል የሚለው ምክንያት ተልካሻ ነው። ከወጣት አባላታቸው መካከል መልምለው ለዚህ ብቁ እንዲሆኑ ማድረግ ግዴታ ነበረባቸው።

እንቀጥልና በኛ የትግል ታሪክ ውስጥ፤ ከላይ በተዘረዘሩት ምክንያቶች፤ ብዙ ግንባር መፈጠር የነበረባቸውና የታለፉትን ዝርዝር እንመልከት። እዚህ ላይ ሊመሠረቱ የነበሩት ግንባሮች ትክክል ይሆኑ ነበር ወይንስ አይሆኑም ነበር የሚል እንደምታ እየተሰጠ እንዳልሆነ ግልፅ ማድረግ እንፈልጋለን። ከፅንሰ ሃሳብ አኳያ ግንባር ከተመሠረተ፤ መሆን ለነበረበት ማመልከት ብቻ ነው። አንባቢ ይሄን እንዲያው ግምት ውስጥ እንዲያስገባው የተሰጠ ገለፃ መሆኑን ይገንዘብልን።

ምሳሌ ፩፤     አንድን ትስስረ-ትውልድ እንወክለዋለን በሚሉ ድርጅቶች መካከል። ለምን ቢባል፤እኒህ ድርጅቶች የሚወክሉት ወገንና ከትግሉ በኋላ ሊከተል የሚፈልጉት ዓላማና ግብአንድ ነውና። ይህ ውሎ አድሮ መዋሃድን ያስከትል ነበር።
ምሳሌ ፪፤     ተመሣሣይ ርዕዩተ ዓለም ባላቸው ድርጅቶች መካከል። ለምን ቢሉ፤ርዕዩተ ዓላማቸው ሆነ ግባቸው ተመሣሣይ ነውና። በሰላም በሚተዳደሩ ሀገሮች ውስጥ፤ መንግሥትን ለመመሥረት፤ ተመሣሣይ ርዕዩተ ዓለም ያላቸው ድርጅቶች ቀርቶ፤ ተቀራራቢ የሆነ አመለካካት ያላቸው እንኳ፤ የሀገር አስተዳደሩን ኃላፊነት በመጋራት
የጥምረት መንግሥት ይመሠርታሉ።

በአንደኛው ምሳሌ ሥር የሚዘረዘሩ፤

፩ኛ፤ በተጋድሎ ሓርነት ኤርትራ (ተሓኤ / ጀብሃ) እና በህዝባዊ ግንባር ሓርነት ኤርትራ (ህግሓኤ / ሻዕቢያ)
፪ኛ፤ በተጋድሎ ሓርነት ትግራይ (ተሓኤ / ጠርናፊት) እና በህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት / ወያኔ)
፫ኛ፤ ኦሮሚያን ነፃ እናወጣለን በሚሉ የተለያዩ ድርጅቶች
፬ኛ፤ አፋርን እንወክላለን በሚሉ የተለያዩ ድርጅቶች

በሁለተኛው ምሳሌ ሥር የሚዘረዘሩ፤

፩ኛ፤ በኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) እና በመላ ኢትዮጵያ ሶሺያሊስት ንቅናቄ (መኢሶን)
፪ኛ፤ በኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) እና በቀይ ኮከብ
፫ኛ፤ በቀይ ኮከብ እና በመላ ኢትዮጵያ ሶሺያሊስት ንቅናቄ (መኢሶን
፬ኛ፤ በኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) እና በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ህብረት (ኢዲህ)
፭ኛ፤ በኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) እና በኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ -ዴሞክራሲያዊ (ኢሕአፓ-)

፮ኛ፤ በሁለቱ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲዎችና (ኢሕአፓ/ኢሕአፓ-) በግንቦት ሰባት

፯ኛ፤ በአንድነት ፓርቲና በመኢአድ

፰ኛ፤ በግንቦት ሰባትና በመኢአድ

፱ኛ፤ በግንቦት ሰባትና በግንቦት ሰባት ዴሞክራሲያ

፲ኛ፤ በግንቦት ሰባትና በአንድነት ፓርቲ . . . ..

ከትግሬዎችን ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ጋር ስምምነት ማድረግ አይቻልም፤

ጠርጥር በገንፎ ውስጥ እንዳለ ስንጥር

ከሕዝቡ ወገን የሆነ ድርጅት፤ በምንም መንገድ የትግሬዎችን ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት አምኖ ለመግባባት መንገድ መጀመር የለበትም። የትግሬዎችን ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት የአንድ ፓርቲ መንግሥት መሥርቶ መግዛት ከመጀመሩ በፊት የነበረው ታሪክ የሚያስረዳን የማይታመን ድርጅት መሆኑን ነው። ለዚህ ምስክሩ፤ የትግራይ ነፃ አውጪ ግንባር፣ የጠርናፊት፣ የኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ሕብረትና የኢትዮጵያ አብዮታዊ ሠራዊት ታሪኮች ናቸው። በውስጣቸው እንኳ የአመራር አቀያየራቸው ከዘመነ መሣፍንት አይለይም። በመካከላቸው የሚገኙትን ግለሰቦች እንዴት እንደሚያጠፉ ለመረዳት ያንዳንድ ታጋዮችን የአሟሟት ታሪክ መጥቀሱ ይበቃል።የማሚቴን እጅ ያላዬ በእሣት ይጫወታልእንዲሉ።

የሀገሪቱን ሥልጣን ነጥቆ አንድ ፓርቲ ብቻ ሰይሞ የሚገዛ ድርጅት ነው። የአንድ ፓርቲ ብቻ በአንድ ሀገር መኖር ደግሞ፤ አንደምታው ብዙ ነው። ይህ ፓርቲ፤እኔእናሌሎችብሎ በሀገሪቱ ውስጥ ልዩነት ፈጥሮ ክልል ስላሰመረ፤ ሌሎችየሚላቸውን በጥላቻና በፍርኀት ይመለከታል። ይህ ፓርቲ መላ ሕዝቡን እንደማይወክል ስለሚያውቀው እናም በሕዝቡም ሆነ በትክክለኛ የሕዝቡ ወኪሎች መተማመን ስለማይችል፤ሌሎች በጥርጣሬና በጠላትነት ማየቱ ያለ ነው። ማንኛውንም ነገር በቁጥጥሩ ሥር ካላደረገ፤ ሕልውናው አደጋ ላይ የወደቀ ይመስለዋል። ስለዚህ፤ በምንም መንገድ ቀዳዳ መፍጠር ስለማይፈልግ፤ መደራደርና በምንም ነገር መስማማት አይችልም። የመደራደር መንገድ ከተፈጠረ፤ ጊዜ ለመግዢያ፣ ሌሎችን ለማዘናጊያ እና ትክክለኛ መስሎ ለመታየትና የፖለቲካ በጎ አምለካከት ለመገብየት ብቻ ነው።የሚክድ ሰው አደራ ሲያስቀምጡበት እጅ ይነሳልነውና ሚስጥሩ።

የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነውበሚል ዘዬ፤ ሌሎች የማይወዷቸው ድርጅቶችን ለማጥቃት ብለው ከትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ጋር ለመወዳጀት መሞከር፤ ባንገት ላይ መንጠልጠያ ገመድ ማስገባት ነው።የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነውየሚለው አባባል፤ በዚህ ጸሐፊ የተወሰነ ጥናት ሂሳብ፤ ከውጭ ኢትዮጵያዊያን የለቀሙት እንጂ፤ ኢትዮጵያዊነት ልጓም የለውም። የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥትን ለማጥቃት ከአረመኔው ኢሳያስ ጉያ ሄዶ መጠለል፤ አንድም የኢሳያስ አፈወርቂን ማንነት አለመረዳት ነው፤ አለያም በራስ ላይ የሌለ ጥንካሬን መሥጠትና ለአደጋ መጋለጥ ነው። እናም ከትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ጋር ሆነ ከኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ምንም ዓይነት ስምምነት ላይ ለመድረስ መሞከር፤ የሕልም ውስጥ ዋናየተለዬ አይደለም። በቂ ኢትዮጵያዊ ኃይል አለን።

ምን ይከተል?

የመቀናጆ በሬ ሲመሽ ወደ ቤቱ ይስባል

ካለፈው መማርና ወደፊት ሊያገለግለን የሚችለውን መውረስ ይጠቅመናል። በመሠረቱ ከግንባር ምሥረታው በፊት መጤን ያለበት፤ ለምን ይመሠረታል ለሚለው መልስ መሥጠት ነው። ባሁኑ ሰዓት ምን ዓይነት መንግሥት በሀገራችን አለ? የሚለውን መመለስ አለብን። የዚህን መንግሥት ምንነት በምንገልፅበት ጊዜ፤ በትክክል ጠቅላላ ማድረግ ያለብንን ማየት እንችላለን። በደፈናው ትግል መደረግ እንዳለበት መቀበሉ ብቻ በቂ አይደለም። የምን ትግል? ለምን እስከዛሬ ድረስ ትክክለኛ ግንባር አልፈጠርንም? ያገደን ምንድን ነው? ከባህላችን ነው ወይንስ ከግለሰብ ማንነታችን? ይህ የሚመለሰው በሀገራችን ያለውን የስነ-አስተዳደር ሀቅ ስንረዳ ነው። አሁን የሚደረገው ትግል የዴሞክራሲያዊ መብቶችን ለማስከበር አይደለም። አሁን የሚደረገው ትግል፤ ከሌሎቹ እኔ የበለጠ ትክክለኛ ነኝ እያልን እርስ በርሳችን የምንወዳደርበት አይደለም። የኢትዮጵያ ሕዝብና ሀገራችን ኢትዮጵያ ያለችበት ሀቅ፤ የነፃነት ማጣት ጉዳይ ነው። መጀመሪያ ሀገራችን ነፃ ወጥታ ነው ሌላው የሚከተለው። የትስስረ-ትውልዱ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት ሀገራችንን እየገዛ ያለው፤ እንደባዕድ ሆኖ፤ በኢትዮጵያዊነትና በኢትዮጵያዊያን ላይ በመዝመት ነው። እናም ከዚህ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነፃነት መፈለጉ ሀቅ ነው። ለዚህ የኛ ሚና፤ አንድ ሀገራዊ አስተባባሪ አካል መመሥረትና፤ ጥረታችንን በሙሉ በአንድነት ማቀናጀት ነው። 

ይኼን ከተቀበልን፤ ትግሉና ትግሉ የሚጠይቀው ድርጅት ግልፅ ነው። ሀገርን ነፃ ለማውጣት አንድ ድርጅት ብቻ ነው መኖር ያለበት። ሀገርን ከአንድ በላይ በሆኑ ድርጅቶች ነፃ ለማውጣት መነሳት፤ ሀገሪቱን ለመከፋፈል ወይንም ቆይቶ ሌላ ጦርነት ለማንሳት ማቀድ ይሆናል። እናም ሀገርን ነፃ ለማውጣት አንድ ድርጅት ብቻ ነው መኖር ያለበት። አንድ ድርጅት ደግሞ አንድ ሠልፍ፣ አንድ ራዕይ፣ አንድ ተልዕኮ፤ አንድ ግብ ነው ያለው። ወገናችን ከአምባገነኑ ጥፍር ራሱን ለማላቀቅ በሚያደርገው ትግልና አንዷን ሀገራችን ነፃ ለማውጣት፣ እንያንዳንዳችን ኢትዮጵያዊያን፤ በሀገር ቤት የምንኖርም ሆነ ከሀገር ውጪ ያለን፤ በአንድነት የምንሠለፍለትና የምንሠለፍበት አንድ ድርጅትና አንድ ዓላማ መጨበጥ አለብን። ይኼ እስካልሆነ ድረስና ሌላውን አማራጭ ከወሰድን፤ ያለው ገዢ ቡድን እንኳ ቢወገድ፤የእሬያ ታጥቦ ጭቃነትነው ጉዟችን። ከላይ እንደተጠቀሰው ጨልሞ ማየት የማይቻልበት ጊዜ ገና ቢሆንም፤ መሽቷልና ወደ ቤታችን እናምራ። ....  ይቀጥላል      



No comments:

Post a Comment