Saturday, October 5, 2013

ኢትዮጵያ ወዴት? በየታሪካዊ ማጋጠሚያው አዲስ መልስ የሚሻ የተደጋገመ ጥያቄ

ኢትዮጵያ ወዴት? በየታሪካዊ ማጋጠሚያው አዲስ መልስ የሚሻ የተደጋገመ ጥያቄ

በየታሪክ ማጋጥሚያው የሚወጥር ጥያቄ

በተለያዩ የሀገራችን ወሳኝ የታሪክ ምዕራፎች ኢትዮጵያ ለመፃኢ እድሏ እጣ ፈንታ ወሳኝ በሆነ መሰቀለኛ የታሪክ መጋጣሚያ ላይ ተገኛለች ሲባል ደጋግመን ሰምተናል።በርካታ ጊዜያት መንታ መንገድ ላይ ናት ተብሎ ሲነገር እንሰማለን። በተወሰነ የታሪክ ማጋጠሚያ ላይ ሃገሪቷ በመስቀለኛ መንገድ ላይ ተገኛለች መባሉ በተራው የወደፊት የጉዞ አቅጣጫዋ ወዴት ነው ? የሚለው ጥያቄም ያስነሳል።በለውጥ ማዕበል ዋዜማ ላይ መገኘቷን ላይ ሁሉም ቢስማማም የጉዞዋ አቅጣጫ ወዴት እንደሆነ ግንአነጋጋር ይሆናል። በዲሞክራሲ ለውጥ አቅጣጫ ትከንፋለች ወይስ ፈርሳ፤ትበታተናለች፤ ምኞትና ሟርት፣ ተስፋና ስጋት ይደበላለቃልና የሃገራችን መፃኢ እጣ ፋንታ ብዙ ዜጎቿን ያስቆዝማል፤ያሳስባልም።

አልፎ ተርፎ ሃላፊነት የሚሰማቸው ግለሰቦች የሃገሪቷ መፃኢ እድል ያሳሳበቸው በርካታ ጎምቱ ጎመቱ ኢትዮጵያውያን ሓሳብ አፍላቂዎችም በእዚህ ርእስ ሥር የተሰማቸውንና ያሳሳባቸውን በፅሑፍ መልክ ለማስፈር ሞካክረዋል።አንዳንዶቹ እንዲያውም መፃህፍት ፅፈዋል።በ 1974 ዋዜማ ላይ አቶ አዲሰ ዓለማየሁ "ኢትዮጵያ
ምን ዓይነት አስተዳደር " ያስፈልጋታል የሚል ግልገል መፅሓፍ ፅፈው ለሕትመት አብቅተዋል።በ 1989 ፕሮፈሰር መስፍን ወለደማርያምም እንዲሁ "ኢትዮጵያ ወዴት" የተሰኘ አነስተኛ መፅሓፍ አበርክተዋል።ሁሉም ሃገሪቷ ከምትገኝበት ወደ አልታወቀ ወደ አላስፈላጊ አቅጣጫ እንዳትጓዝ ዬት መሄድ እንዳለባት በውል ባይጦቁሙም ወዴት አቅጣጫ መጓዝ እንደሌለበት ለመጠቋቆም ሞካክረዋል።

መልካም እድሎች የማስመለጥ አባዜ

በሃገሪቷ እጣ ፋንታ ወሳኝ ናቸው በተባሉት የታሪክ ማጋጣሚያ ላይ ስጋታቸው ብቻ ሳይሆን በመጋጠሚያ ላይ ቆም ብለን ወርቃማውን እድል ሳንጠቀም እንዳያልፍብን የማሳሳቢያ ደወል ነበር ያሳሙት፣ እነዚያ ሓሳብ አፍላቂዎቹ።በእኛ እድሜ እንኳን ያሁኑ ሦስተኛው ጊዜ ነው መልካም እድሉን ሳንጠቀምበት ሊያመልጠን ተብሎ ማሳሳቢያው ከየአቅጣጫው በመሰማት ላይ ነው። 1974 (ስድሳ-ስድስት)በመስቀለኛ በመንታ መንገድ ላይ ናትም ተባለ። እንደ ገና 1992 (ሰማኒያ ሦስት) አሁንም 2012 መጨረሻ ላይ። በሦስቱም ጊዜያት ሃገሪቷ በታሪክ መጋጣሚያ ላይ ተገኛለች ብቻ ሳይሆን በሦስቱም የታሪክ መጋጠሚያዎች ኢትዮጵያ መስቀለኛ መንገድ ላይ ተገኛለት መባሉ ሲደጋገም ሰምነተናል፣ ተመልክተናልም።

በሦስቱም ጊዜ ቆም ተብሎ ማሰብ ሰለተሳነን እድሉን ሳንጠቀምበት ወይም መጠቀም ባለመቻላችን አምልጦናል ባዮች በርካታ ናቸው በመካከላችን 1974 (ስድሳ ስድስት) ላይ ተብሏል።በ 1992 (ሰማኒያ-ሦስት) ላይ እንደገና ተብሏል።በ 2005 (97 መርጫ) ወቅትም እንዲሁ ተብሎዋል። አሁንም በመጨረሻ የዛሬ 14 ወር ቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለሰ ዜናዊን ሕልፈት አስመልክቶ ቆም ብለን እናስብ ጥሪ ላለፈው አንድ ዓመት ከየአቅጣጫው እየተስተጋባ ነው ።ሰሚ ጆሮ አላገኝም እንጂ ልበል። ከእነዚህ ሦስቱ የታሪክ ማጋጠሚያዎት ትንሽ ወደ ኋላ ሄደት ብለንም 1953 "የተህሳስ ግርግር" በባድሜ የወያኔና የሻዕቢያ ግጭት ጊዜም እንዲሁ ያልተጠቀምንበት መልካም እድል አምልጦናል ባዮች ከመሓከላችን አሉ።ኣመለጡኝ የሚንላቸው ታላላቅ መልካም
እድሎች አምስት አደረስናቸው።ያውም ባንድ ጎልማሳ እድሜ።

እንዲያም በያንዱንዱ መሰቀለኛ መንገድ ላይ ቆም ብለን መቆዘም ስንጀምር ያሁኑ መሰቀለኛ የታሪክ ማጋጠሚያ ካለፈው ይበልጥኑ አሳሳቢ ነው መባሉም አልቀረም።በእዚህ ምክንያትም ለሃገሪቷ እጣ ፋንታ ይብልጠኑ ወሳኝ ብቻ ሳይሆኑ በዚያው ምክንያትም የባሰ አስፈሪ ናቸው መባሉም የተለመደ ነው። የሚገረመው እያንዳንዱ መስቀለኛ መንገድ ለሀገረቷ ሕልውና ከደቀነው ስጋት አንፃር ማጋጣጠሚያው አሳሳቢነቱ፤አስቸጋርነቱ አደገኛነቱ አስፅነኦት ሲሰጠው መስካሪዎች ነን። በሦስቱም የታሪክ መጋጠሚያ ላይ ማምለጥ ያልነበረብት ወርቃማው እድል አምልጦናል ባዮች ብቻ ሳይሆን በያንዱንዱ ታሪክ ማጋጠሚያ ላይ ቆመን ያሁኗ እድል ማምለጥ አልነበረበት እንላለን።በቁጭት እንብሰከሰካለን።ይህን ወራቃማ እድል "ያስመልጠከን አንተ ነህ ፣አንተ ነህ " እየተባባለን እርስ በርሳችን እንካሰሳለን፤ ጣቶቻችንም እንቀሳሰራለን። በአመዛኙ በኤሊቶች መሃል።አሁንም ያለፈው መከራ መክሮን በታሪካዊው መጋጠሚያ ላይና መንታ መንገዱ ላይ ተመሳሳይ ታሪክ ስንደግም እንጂ ካለፈው ትምህርት ቀሰመን ልብ ገዘተንና በተመክሮ በልፅገን በመልካም እድሉ ስንጠቀም ግን አልታየንም። «ወርቃማው እድል በማስመለጥ ማኛውም እድል አናስመልጥም ብለን ከራሳችን ጋር ቃል የገባን ይመስል እንደጋግመዋለን» ብሎ ወገኖቹ በሆኑት ዓረብ ኤሌቶች ላይ በምፀት የቀለደው ማሕበራዊ ተቺ ስሙን ለጊዜው ዘነጋሁት። በተተረተባቸው ያልታደሉ ኤሌቶች ተራ ውስጥ እኛም አለንበት።አንድ ሌላ አስገረሚው ትዝብት አለ። በሌላ በኩል ተደጋግሞ የታየው በነዚህ አጋጣሚዎች በሥልጣን ማማ ላይ ለመቆናጠጥ አመቺ ሆኔታ የተፈጠራላቸው ኤሊቶች ደግሞ እነሱ ለሥልጣን የበቁበት መልካም አጋጣሚ እንጂ ከእጅ ያፈተለከ መልክም እድል አድርገው አይመለከቱትም።በተቃራኒው ላንዱ ከእጅ ያመለጠ ወርቃማ እድል፣ ለሌላው የእሱ ቡደን ወይም ስብስብ ሃገሪቷን ከገደል አፋፍና መበታተን አደጋ እሱ ያዳነበት መልካም አጋጣሚ አድርጎ ይመለከተዋል እንጂ።

የሚደጋገም ጥያቄ፣ አዳዲስ ኩነቶች

ጥያቄው አዲስ አይደለም።ነገር ግን የሚነሰው ተመሳሳይ ሁኔታዎች መሠረት አድርገው ኣይደለም።ጥያቄው አንድ ቢሆንም ቅሉ በያንዳንዱ መስቀለኛ ማጋጠሚያው የነበረው ሁኔታ ተመሳሳይ አልነበረም።እያንዳንዱ መጋጣሚያው በባሕርዩ፣ በተዳፋቱ፣ በአቅጣጫው ይለያል። አዳዲስ ተግዳሮች፣ተጨባጩ ሆኔታዎቹ ካለፈው ልዩ ያደርጉታል።ደርግ ከሥልጣን የተወገደበት መንገድ የአፄ ሃይለ ሥላሴ መንግሥት ከተወገደበት አኳኋን ከሥር መሠረቱ የተለየ ነበር።በሥልጣን ያለው መንግሥትም አወዳደቁ ከሁሉትም ውግደቶች እንደሚለይ አጠያያቂ ልሆን አይችልም፣ መቼም።አሁን በሥልጣን ያለው መንግሥት የሚወገድበት ሁኔታ ከየአፄውም ከደርግ ከተወገደበት ሆኔታ መለየቱ ከቶ አያነጋግርም።

አንድ የግብፅ ቀልድ ልንገራችሁ፣ትንሽ ለማብራራት። የግብፅ ቀለድ (ጆክ) እንዲህ ይሄዳል።ፕረዘዳንት ሙባራክ ሞቶ በዚያኛው ዓለም ሁለት ከእሱ ቀደሞ የግብፅ ፕረዘዳንቶች ማለት ጃማል ዓብዱል ናስርና አንዋር አል-ሳዳት ያገኛል። ቀደመው መንግሥት ሰማያት (ጀነት?) የነበሩት ሟዋቾቹ ሮጠው ወደ እሱ ይመጡና ናስር " በመርዝ ነው የገደሉህ?” ብሎ ይጠይቀዋል።ሙባራክም "አይደለም " ብሎ ይመልስለታል።የቀድሞ ፕረዝዳንት ሳዳትም ቀጠል አድርጎ "በሰገነቱ አመፀኛ ወታደሮች ተኩስ አርከፍክፎብህ ነው የገደሉህ? ብሎ ይጠይቀዋል።አሁንም "አይደለም" ይለዋል ሙባራክ ።ሁለቱ ባንድ ላይ "ታዲያ በምን ድነው ለሞት ያበቁህ" ብለው ያፍጥጡታል።ሙባራክም " ፋይስ-ቡክ" ብሎ ባንድ ቃል መለሰላቸው ይላል ጆኩ።

በስልሣ-ስድስትም ሆነ በሰማኒያ-ሦስት ፋይስ ቡክ የሚባል ነገር አልነበረም። ትዌተርም አልተፈጠርም። የኤሊክቶሮኒክስ ማገናኛ ብዙሓን በሃገራችንም ሆነ በዓለም አልነበሩም፣በዚያን ዘመን ያልነበሩ በርካታ ኩነቶች አሉ።ብዙ ብዙ አዳዲስ የሕዝብ መቀስቀሻ መሣሪያዎች ብቻ ሳይሆኑ በዚያን ዘመን ያልነበረው በርካታ ኩነቶችና አዳዲስ ክስተቶች አሉ ዛሬ።በ የካቲት 1966 ሕዝባዊ መነሳሳትና አብዮቱ ዋዜማ ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ፖሎቲካ ፓርቲም አልነበረም።አንድ በሕቡዕ ከተደራጀ በስተቀር ማለቱ ሊኖርብኝ ነው መሰለኝ።በ አለፉት ሁለቱ የለውጥ ዋዜማ ላይ ያልነበሩና ዛሬ ወሳኝ ሚና ካላቸው ጥቂቶችን ብቻ ለመጠቃቀስ ፌስቡክ፣ትዌተር፣ፓልቶክ ግንቦት
20 ቀን 1983 አልነበሩም። ወያኔው አዲስ አበባ በተቆጣጠረ ዕለት።በ 66 ላይ 3 ሚልዩን የሚጠጉ መኖሪያቸው በውጭ ሃገራት አራቱ የዓለም ማዕዘናት ያደረጉ ዲያስፖራ የሚባል ጫና አሳዳሪ ስብስብ በኢትዮጵያ ፖሎቲካዊ መሕዳር ውስጥ ከቶ አልነበረም።በ ግንቦት 1983 የደርግ መንግሥት ለውጥ ዋዜማ ላይ ደበብ ሱዳንና ኤርትራ የሚባሉ ሉዓላዊ ጎሮቤት ሃገራት አልነበራት ኢትዮጵያ።በ 66 የካቲቱ መነሳሳት ላይ ጀቡቲ የሚትባል ነፃ ሃገር አልነበረችም።ዛሬ ሃገሪቷ ሦስት አዳዲስ ጎሮቤት ሃገራት አፍርታለች።ኢትዮጵያም ባህር በር መውጫ አለባ ሃገር ናት።ዛሬ 90 በላይ ፓርቲዎች አሉ። አብዛኞቹ ብሔረሰብአደረጃጀትን መሠረት ያደረጉ። ደጋግመን እንደምንለው የራሱን የሥልጣን ዕድሜ ለማራዘም ብሔረሰብአደራጅቶ የሚያናክሳቸው ባንድአውራ ፓርቲፊተወራርነት የሚተነፍሱ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በሃይማኖት አደራጅቶ የሚያተረማምስ መንግሥት ሥልጣን በተቆጣጠረበት ሃገር።

እነዚህ ሁላ አዳዲስ እድገቶች ናቸው።ያውም ጫና አሳዳሪ ክስተቶች ናቸው ።አዳዲስ አንደርዳሪ ግፊቶቹን (ዳይናሚክስ) የሚፈጥሩ ክስተቶች።በ የካቲት 66 ኢትዮጵያን ሙስሊሙ ሕብረተሰብ ከሁለተኛው ዜግነት ያልተላቀቀ እዚህ ግብ የማይባል የፖሎቲካ ተሳትፎም ሆነ ጫና የማሳደር አቅም የሌለው ሃይል ነበር።ይህ ምንም ማጋነን የለበትም። 1966 ከዚህ ለመላቀቅ ከክርስትያን ወገኖች ልክ እንደ ሌሎች ብሶት ያነሳሳቸው ክፍሎች ለእኩልነት መብት ድል እና ደመቅ ያለ ትዕይነተ-ሕዝብ ካደረጉት የሕብረተሰብ ክፍሎቹ አንዱ ነበር። ያለ ጥርጥር፣ ዛሬ በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ከሥር መሥረቱ ተለውጦዋል።የዛሬዬቷ ኢትዮጵያ የካቲት 66 ም፣ የግንቦት 83 አይደለችም።ለክፉም ለደጉም።

  1991 (ሳምኒያ ሦስት) ላይ ከሰሜን በኩል የተረዳዱና በአጎራባች ሃገራት ድጋፍ የሕዝብን ድጋፍ ያጣውን የደርግ መንግሥት በቀላሉ ለማሸነፍና እነሱ የፈቀዱትን ወገኖች ብቻ ለሽግግሩ ሂዴት የጋበዙበት ሁኔታ ነበረ።ያልፈቀደቱንም ከሽግግሩ ሂዴት ያገለሉበት ሁኔታ ነው፣የተመለከትነው።1966 በግብታውነት የፈነዳውን ሕዝባዊ አመፅ ማን መራው?የሚል ጉንጭ-አልፋ ክርክር በሰማኒያ ሦስት ላይ አልነበረም።መሪውና አሸናፊው "ብሶት የወለደው" በሕወሕት የሚመራው ኢሓዴአግ ነበር ጠርናፊው።ብዙ፣ ብዙ በዚያን ዘመን ያልነበሩ ፣አሁን ያሉ አዳዲስ ኩነቶች በሰፊው መጠቃቀስ ይቻላል። አጼ ሃይለ ሥላሴን ከሥልጣን ለማውረድ ከአካባብያዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ አስገዳጅነት የትግል ሥልት አማራጮችንና፣ የሽግግር ንድፎችን የሚያወጣና የሚያወረድ ሃይል በትግል ሜዳም አልነበረም።በከተማም አልነበረም።በሃገር ቤትም በውጭ ሃገራትም አልተደራጀም ዛሬ እንደምናደረገው በትግል ሥልት አማራጮች ዙሪያ የሓሳብ መንሸራቸሮች አልተደረጉም። አፄው ሥርዓትም ሆነ ወታደራዊ በደርግ ውድቀት ዋዜማ ላይ በሰለማዊና የትጥቅ ትግል አማራጮች ላይ በተቃዋሚ ፖሎቲካ ሃይሎች መካከል ውይይት ሲደረግ አልተመለከትንም። ማስገደድ ወይስ ማስወገድ በሚባሉት አማራጮች ዙሪያም የሓስብ ልውውጥ አላነታረክም።ሁለቱም መንግሥታዊ ሥርዓቶች የተወገዱበትን ስልት አካባቢያውና ዓለማቃፋዊ ሁኔታ የሚያሳርፉት ጫናም እንደምታ እንደ ራሱን የቻለ ታሳቢ ሲተነተኑ አላየንም።

በተደጋጋሚ መልካም እድሎች አምልጡን ብለን ብንቆጭም ቅሉ ካለፉት የታሪክ ማጋጠሚያዎች ኢትዮጵያውን ፖሎቲካ አክቲቪስቶች ከእነጭራሽ ምንም ትምህርት አልተመርንም ማለት አይቻልም።እነዚህ የተመለከትናቸው አዳዲስ ኩነቶች፣ ፈተነዎችና ተግዳሮቶች በግምት ለማስገባት እየተሞከረ ነው ፣በአቅምቲ።አዳዲስ አንደርዳሪ ግፊቶችም የራሳቸውን አሻራዎች እያሳደሩ ናቸው።

በተለያዩ ተለዋዋጭ ተጫባጭ ሆኔታዎች አስገዳጅነት፣ አዲስ የትግል ስልቶች መንደፍ የግድ ሆኖዋል። የትግል ስልት ክርክርም አንዱና ዋነኛው መወያያ ርእስ ነው ልክ እንደ ዛሬው።በሥልጣን ያለው መንግሥት ወደ ክብ ጠረጴዛ እንዲደራደር እንስገደደው ወይስ ከእናካቴው እንስወግደው ሙግትና እሰጣ-ገባ በእዚሁ ምክንያት ይጧጧፋሉ።ሁሉገብ የትግል እስተራተጂ ከተመረጠ በኋላም ሁለቱን የትግል አማራጮች የመቀየጡ ጉዳይ ማነታረኩ አልቀረም። የአስወጋጅና አስገዳጅ አማራጮቹም ሆኑ ሰለማዊ የትጥቅ ትግል ምርጫ ዙሪያም አወሳሳቢ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ ናቸው። ሁሉግብ ትግል የሁለት ቅልቅል ሰለተባለ ብቻ ከዬተኛው በምን ያህሉ ምጥጥን፣ ቅመማ ራሱን የቻለ ጠበብም ሳይንስም እየሆነ የማዳቀሉ ተግባር ቀላል ሆኖ አልተገኘም።

በምን ምጥጥን፣ ተቀይጦ ሲቀመም ነው ትክክለኛነቱና የፋዋሽነቱ ፍቱንነት ዋስትና ማረጋገጫው አስቸጋሪ ጥዳንጥድ ነው።በከሜስትሪው ላብራቶሪ የማይጣድ ነገር። እንኳን የትግል ቅመማ ምጥጥንና ዶዜጅ ይቅርና የቤት እመቤቶች ያንዱ ምግብ አሰራር በግምት እንጂ በትክክል ስንት የሻሂ መንኪያ ጨው፣ ስንት ሚሊግራም ዱቄት ባንድ ላይ እንደምጣድ እምብዛም በማይታወቅበት ባህል ላደግን ሰዎች። የሃገር-ሰብ መድሓኒቶቻች ቅመማም ወደ ፈዋሽ እንክቢሎች እንዳይቀየሩ ጋት አላነቃንቅ ያለውም ይህው ትክክለኛው ምጥጥን ቅመመ ጉዳይ ነው ቢባል ማጋነን አለበትም።ሁሉም ድስት ጥዶ በነሲብ ይጨምራል።ያማረላት ሽር ጉድ ትላለች።ያረረባት "ድስት ጥዳ ታለቀሳለች" ከእነ ተረቱ።

በተለይም በሰለማዊ ትግሉ አቶ ግርማ ሞገስ በቅርቡ " ይሁን እንጂ የአልበርት አነስታይን ሰላማዊ ትግል ምርምር ተቋም ባልደረቦች እነ ጅን ሻርፕ የመሳሰሉት የዘመናዊ ሰላማዊ ትግል የፖለቲካ ሳይንስ ጠበብቶች እነዚህን 200 ሰላማዊ ትግል ማራመጃ መሳሪያዎች ጥናት እንዲቻል ለማድረግ በሶስት አብይ ክፍሎች ከፍለዋቸዋል" በማለት ብዛቱን እንዳስገነዘቡት።እነዚህ 200 በላይ ዓይነቶቹን መቀየጡም እጅግ አስቸጋሪ ነው። በሰለማዊ የተጀመረው ትግል ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ወደ ደም-አፋሳሽ መተላለቅ እንዳይሸጋገር ስጋትም እንዳለም ሳንዘነጋ። ዛሬ ሦስት ዓመቱን ለማስቆጠር የተቃረበው የሶሪያ ደም-አፋሳሹ ትርምስ የተቀየረው ለሰባት ወራት ሰለማዊና ሕዝባዊ አል-ገዛባይነት አመፅ ሆኖ ከዘለቀ በኋላ መሆኑን ማስታወስ ብቻ በቂ ነው።ዓለም አቀፍ ጂሃዳዊ ሃይሎች የአካባቢያዊና ዓለም አቀፍ መንግሥታት እጆቻቸውን በሶሪያ የውስጥ ጉዳይ ከዶሉ በኋላ ነው።መፈትፈት ከጀመሩ ወዲህ ነው።እነዚህ ሁላ ተጨማሪ አወሳሳቢ ኩነቶችና ናቸው።

 1983 ላይ የተመለከትነው መሸነጋገል ወይም 2005 ከምርጫ በኋላ የተመለከተነው አንዱ የሌለኛውን ጥረት መና ማድረጉና የማምከኑ ጠረቶች በብሄረሰብ ኤሊቶች መካካል ያለውን ያለመተማመን መገለጫዎች ናቸው።ዛሬም ባንድ ሃገር ልጅነት ላይ የተመሠረት የሃገር የጋራ ባለቤትነትን ያሰናከሉ ጥርጣሬዎች አንዳሉ ናቸው።

  ተሰነጣጣቂ የኤሊቶች አንጃነት (Factionalized Elite) ለጨንጋፍ ወይም ውሉ ለተፈታ መንግሥትነትና ለላበሩ መናቆሮች ብቻ ሳይሆን ለሀገር ሕልውና ጭምር ጠንቅ ነው ይለል 2005 ጀምሮ የተጨነገፉ ሃገራት ሊስት በየዓመቱ የሚያወጣው ፎሪን ፖሎሲ (Foreign Policy) የተባለው በአሜሪካ የሚታተመው ጆርናል። የሚገረመው ለኢትዮጵያ የመጨረሻው ጠንቅ ተደረጎ የተወሰደውም እሱ ነው። እንደ አንድ ምክንያት በስሌት መግባቱ ብቻ ሳይሆን ዋሳኝ ስፍራ ተቆናጥጦዋል። በዘንድሮው ሊስት ኢትዮጵያ 20 ስፍራ ተገኘለች።ለብዙ ዓመታት ሶማሊያ ባንድ ቁጥር ሊስቱን ትመራ ነበር።

ማጠቃሊያ

በኤሊቶች መካከል መግባባት የሚያስፈልገው በሥልጣን ያለውን መንግሥት ለማስወገድ ብቻ ሳይሆን በረጅሙ አብዛሕነታችንን ለማስተናገድ የሚያስችል ለነገ የማይባል ቀዳሚ ተግባር ነው።በእዚያኑ መጠን የሽግግሩ ጊዜ በስኬታማ አኳኋን እንዲጠናቀቅ የአብዛኛዎቹ ሃይሎች ይሁንታ የተካለበት መግባባት ወሳኝ ነው።ተቃዋሚዎች ገዢ ፓርቲውን ከሥልጣን ለማስወገድ የሚያደርጉት ግብግብ ላይ ብቻ ከማተኮር ጎን ለጎን በቦታው መመሥረት ሰለለበት ሥርዓት ላይም በቅድሚያ የጋራ መግባባት መድረስ ይኖረባቸዋል።እስከ ተቻለ ድረስ የብዙዎቹ ይሁንታ የታከለበት ሁሉን አቀፍ ሃገራዊ መግባቢያ ጉባኤ ተጠርቶ የአብዛኛው ሕዝብ ፍላጎትና ምኞት፤ ህዝባዊና ሃገራዊ መግባባት የሚገልጽበና የአብዛኛዎቹ የፖሎቲካ ሃይሎችና ቡድኖች ተሳትፎ የታከለበት የሽሽግሩ ቃል ኪዳን ላይ ስምምነት መደረሱ ሽግግሩን ይብልጥ አስተማማኝና ሰንካ-አልባ ያደርገዋል ተብሎ ይታመናል።በመሸነጋገሉና አንዱ ለሌላው ወኪልና ወካይ ብሔረሰብ ድርጀት በመጠፍጠፉ ምትክ በመጨራሻው የዛሬ አንድ ዓመት ሁሉን በእጁ ቀፍድዶ ከያዘው ጠቅላይ ሚኒስትር ከመደረኩ የተሰናበተበት ጊዜ ያባተው መልካም አዲስ እድል አለማስመለጥ ብቻ መልካም እድሎችን የመባከንም ሆነ ከመለጡ በኋላ በቁጭት ከመበሰከሱ ፋታ የእጣ-ፋንታችን ወሳኞች እኛው ራሳቸን እንሆናለን። ኢትዮጵያ ወዴት የሚለው ወጣሪ ጥያቄ እንቅልፍ አያነሳንም። ያን ጊዜ አቅጣጫችን ጦቃሚ ካርታ በጋራ የመንደፉ ቀዳሚ ተግባር በምር ተያይዘናል ማለት ነው።ወዴት እንደምትመራ በውል እናውቆዋለን ምክንያቱ ያን ጊዜ የጀልባ እርፉ በእጃችን ይሆናልና።

(ዩሱፍ ያሲን) 

No comments:

Post a Comment